1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"የአፋር አርብቶ አደር ሁለት ሞት እየሞተ ነው" - አቶ አሎ ያዮ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2 2012

የክረምቱ ዝናብ በመጠንከሩ በአፋር ክልል የተከሰተ ጎርፍ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ነው። እስከ ትናንት አርብ ድረስ በትንሹ ከ400 በላይ ሰዎች ጎርፍ ካጠቃቸው ሁለት ቀበሌዎች ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወሩን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሑሴን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

Äthiopien | schwere Überschwemmung in Afar
ምስል Allo Yayo

አቶ መሐመድ ሑሴን 20 ሺሕ ገደማ ሰዎች መፈናቀላቸውን ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል

This browser does not support the audio element.

ባለፈው አንድ ሳምንት በአፋር ክልል እየበረታ በመጣው ጎርፍ የተፈናቀሉ ሰዎች የቀንድ ከብቶቻቸውን እና ንብረቶቻቸውን ጥለው ከመኖሪያ ቀያቸው እየሸሹ መሆናቸውን የክልሉ ነዋሪዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የዐይን እማኞች እንደሚሉት የክረምቱ ዝናብ እየበረታ በመምጣቱ የተከሰተው ጎርፍ በተለይ በአሳይታ፣ አፋምቦ፣ ዱብቲ እና ሚሌ ወረዳዎች በርትቷል።

የጎርፍ አደጋው በክልሉ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በቦታው እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ አሎ ያዮ ጎርፍ ከቀያቸው ያፈናቀላቸው ነዋሪዎች "ፍየሎቻቸውን፣ ላሞቻቸውን በቆሙበት ትተው ነው እየወጡ ያሉት። ከላይ ዝናብ ከታች ጎርፍ ውስጥ ሆነው ማሕበረሰቡ ወደ ከተማ እየተጓጓዘ ያለው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የፌድራል መንግሥት ነዋሪዎችን ጎርፍ ካጠቃቸው አካባቢዎች ለማውጣት አንድ ሔሊኮፕተር ወደ አካባቢው መላኩን የገለጹት አሎ "እሱም አስራ አምስት ሰው ነው የሚጭነው፤ ፌስታል መያዝ አይችሉም፤ ሻንጣ መያዝ አይችሉም። ሌላ ቋሚ የሆነ ንብረት ይዘው መውጣት አይችሉም" ሲሉ ኹኔታውን አስረድተዋል።

በአሳይታ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ አሕመድ አብዱልቃድር "በጣም ብዙ ሰው ተፈናቅሏል፤ በሔሊኮፕተር እየወጡ ነው። ቤታቸው፣ ልብሳቸው፣ እህላቸው በሙሉ ጠፍቷል፤ ወድሟል። እነዚህ ሰዎች ሕልውና በጣም አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል" ሲሉ የአቶ አሎን ሐሳብ አጠናክረዋል።

"ከገለአሎ እና ካርቡዳ ቀበሌዎች አሳይታ ወደሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሔሊኮፕተር የተጓጓዙ ወደ 400 የሚደርሱ ናቸው" አቶ መሐመድ ሑሴን ምስል Allo Yayo

እስከ ትናንት አርብ ድረስ በትንሹ ከ400 በላይ ሰዎች ጎርፍ ካጠቃቸው ሁለት ቀበሌዎች ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወሩን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሑሴን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። አቶ መሐመድ "ከገለአሎ እና ካርቡዳ ቀበሌዎች አሳይታ ወደሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሔሊኮፕተር የተጓጓዙ ወደ 400 የሚደርሱ ናቸው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ባለፈው ሰኔ ይፋ ባደረገው ብሔራዊ የጎርፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያ "የጎርፍ ስጋት ሊኖርባቸዉ ይችላል" ብሎ ከለያቸው አካባቢዎች መካከል የአፋር ክልል ወረዳዎች ይገኙበታል።

በዞን አንድ የሚገኙት ዱብቲ፣ አፋምቦ፣ አሳይታ እና ጭፍራ፤ በዞን ሁለት የሚገኙት አብአላ፣ በርሃሌ፣ መጋሌ እና ኮነባ፤ በዞን ሶስት የሚገኙት አሚባራ፣ ገላሌ፣ ገዋኔ፣ አዋሽ ከተማ፣ ዱለቻ፣ አዋሽ ፈንታሌ፤ እንዲሁም በዞን አራት የሚገኙት ያሎ እና ያዋ ናቸው።

በአፋር ክልል አደገኛ ጎርፍ ሲከሰት የዘንድሮው የመጀመሪያ አይደለም። በክልሉ በሁለት ምክንያቶች ጎርፍ ይከሰታል። አንደኛው አስር የክልሉን ወረዳዎች የሚያቋርጠው የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ሲፈስ የሚከሰት ሲሆን ሁለተኛው ከአማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ከፍተኛ አካባቢዎች ወደ አፋር በሚፈስ ደራሽ ውኃ አማካኝነት የሚፈጠር መጥለቅለው ነው። "በተለይ ከአዋሽ ወንዝ ግራ እና ቀኝ የሚገኙ እነ አሳይታ፣ ሚሌ ላይ ደግሞ አዲስ ወረዳ አለች ሐሮካ የምትባል እነዚህ ወረዳዎች ላይ ጎርፍ ተከስቷል። ከዚያ ውጪ ዳሎል ላይም ተመሳሳይ ጎርፍ ይከሰታል" ብለዋል አቶ መሐመድ ሑሴን።

ኃላፊው በዚህ አመት በክልሉ "ወደ 63 ሺሕ ሕዝብ በዚህ ጎርፍ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 44 ሺሕ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብለን የመጠባበቂያ ዕቅድ አዘጋጅተናል" ብለዋል። ባለፈው ሳምንት የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሒስ ያሲን የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰሱ 32 ሺሕ ሰዎች መፈናቀላቸውን ለመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረው ነበር። አቶ መሐመድ "የተፈናቀሉት አሳይታ ከተማ ላይ ያሉት 400 የሚደርሱ ናቸው። ሌላ አካባቢ ላይ 44 ሺሕ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብለን ገምተናል። በጎርፍ የተጎዱ እና ውኃ የነካቸው አሉ። ነገር ግን የተፈናቀሉ እና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው አዲስ ቦታ ላይ የሰፈሩ በትክክል 400 የሚደርሱ ናቸው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።  

የክልሉ መንግሥት በዘንድሮው ክረምት በሚፈጠር ጎርፍ 44 ሺሕ ሰዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለውምስል Allo Yayo

አቶ መሐመድ ሑሴን ዛሬ ቅዳሜ 20 ሺሕ ገደማ ሰዎች በክልሉ በጎርፍ ምክንያት መፈናቀላቸውን ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። አቶ መሐመድ እንዳሉት በውኃ የተከበቡ ሰዎችን ለማውጣት ሁለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሔሊኮፕተሮች ተሰማርተዋል።

"ካሁን በፊት በታሪክ እንዲህ አይነት ጎርፍ ይኸ አካባቢ አስተናግዶ አያውቅም" የሚሉት አቶ አሎ "የጎርፉ መንስኤ ዝናብ ብቻ አይደለም" የሚል አቋም አላቸው።  "ከቆቃ እስከ ተንዳሆ ግድብ፤ የበሰቃ [ሐይቅ] እና የከሰምን [ግድብ] ጨምሮ ውኃ እየለቀቁ ነው ያሉት። ብዙ ያከማቹት ውኃ አላቸው። እነዛ ውኃዎች ወደ አፋር ከሚፈሱ ገባር ወንዞች በተለይ ከሎጊያ ጀምሮ እስከ ወንዙ መስረጊያ ድረስ ያለውን አካባቢ ውኃው እንዳለ ይዞ ነው እየመጣ ያለው። ወንዙ በየቦታው እየፈነዳ ማሕበረሰቡን መግቢያ መውጪያ መንገዱን እያሳጣ ነው ያለው" ሲሉ ገልጸዋል።  

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሑሴን ከግድቦቹ የሚለቀቀው ውኃ ለጎርፍ መጨመር አስተዋጽኦ እንዳለው ይስማማሉ። ተቋማቸው "ከግድቦቹ ግርጌ የሚገኙ ማሕበረሰቦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፤ ወደ ከፍታ ቦታ እንዲወጡ፤ እንዲዘጋጁ" ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ መሐመድ ዋናው ምክንያት ግን እየጣለ የሚገኘው ዝናብ ከፍተኛ መሆኑ ሲሉ ተናግረዋል።

"በአጠቃላይ በአገሪቷ ብሎም በአፋር ክልል ካለፉት አስር አመታት በተለየ ኹኔታ ከፍተኛ ዝናብ እየጣለ እንደሆነ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በአካባቢው በሚጥለው ዝናብ ደራሽ ውኃ በብዛት እየተከሰተ ነው። የአዋሽ ወንዝ ደግሞ መሸከም ካለበት አቅም በላይ እየተሸከመ ነው። ምክንያቱም ወደ አዋሽ የሚፈሱ የተለያዩ ወንዞች አሉ። [ጎርፍ የጨመረው] ቀጥታ በግድቦች ምክንያት ብቻ አይደለም። አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይችላሉ። ነገር ግን ያ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ዝናብ በመኖሩ ጭምር ነው ይኸ እየተከሰተ ያለው" የሚል ማብራሪያ አቶ መሐመድ ሰጥተዋል።

"በአፋር ክረምቱ አሁን ነው እየጀመረ ያለው። የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ነው ያለንው። የውኃ ሙላቱ በከፍተኛ ኹኔታ የጨመረው በዚህ አራት ቀናት ውስጥ ነው" ያሉት አቶ አሎ በበኩላቸው የጎርፍ አደጋው ነዋሪዎችን በማፈናቀል ብቻ እንዳልተገታ አስረድተዋል። "በአሁኑ ሰዓት የአፋር አርብቶ አደር ሁለት ሞት ነው እየሞተ ያለው። አንደኛው በኤኮኖሚ እየተጎዳ ነው። ሁለተኛ መንግሥት ከፍተኛ ገቢ ሲያገኝበት የነበረው፤ ግብር የሚከፍሉ፣ የሀገር ተወላጆች፣ እዚያው የበለጸጉ ሰዎች ያረሱት የጥጥ መሬት እንዳለ ተወስዷል" ብለዋል።  በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ባለወረቶች "ትራክተሮችን ጨምሮ ንብረቶቻቸው ቀርተዋል፤ የደረሰ የጥጥ ምርት በውኃ ተወስዶባቸዋል። ለመዝራት የተዘጋጁ መሬቶች ባዷቸውን ቀርተዋል" ይላሉ አቶ አሎ በመዋዕለ ንዋይ ላይ የደረሰውን ጥፋት ሲያስረዱ።

አቶ አሎ ያዮ በቀሪዎቹ የክረምት ወራት ጎርፍ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ያሰጋቸዋልምስል Allo Yayo

የጎርፍ አደጋው የእርሻ ማሳቸውን ካጠፋባቸው ባለወረቶች መካከል አንዱ አቶ አሕመድ አብዱልቃድር ናቸው። አቶ አሕመድ በአሳይታ ወረዳ ኮሮዶራ ቀበሌ የነበረ የእርሻ ማሳቸው ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ተውጧል። "የበቀለ ጥጥ 35 ሔክታር ነበር። ያልበቀለ 670 ሔክታር ነበረ። ዘር ልገባ ማረሻ እና መከስከሻ አድርጌ ውኃ አጠጥቼ ልዘራ ስል ይዞብኝ ሔደ። ሰራተኞቼ የነበሩ ወደ 336 ሰዎች ነበሩ። እነዛ በሙሉ ተፈናቀሉ" ሲሉ አቶ አሕመድ በእርሳቸው ላይ የደረሰውን ኪሳራ ተናግረዋል።

"አሁንም ጎርፉ እየጨመረ ነው። የከፋ አደጋ እየመጣ ነው። እስካሁን ምንም የቀነሰ ነገር የለም፤ መንግሥት ማድረግ የሚገባውን ነገር እያደረገ አይደለም" የሚሉት አቶ አሕመድ በነሐሴ ወር ይበረታል ተብሎ የሚጠበቀው ዝናብ ሊያስከትል በሚችለው ጎርፍ የከፋ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

ይኸ የአቶ አሎ ጭምር ሥጋት ነው። "ገና ሁለት የክረምት ወራቶች አሉ። ስለዚህ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአንድ ወረዳ ሶስት አራት ቀበሌ እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ የእነዚህን ማሕበረሰብ [መፃኢ] እጣ ፋንታ መገመት ይቻላል" ሲሉ ተናግረዋል።  

እሸቴ በቀለ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW