1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፋር እና ሶማሊ-ኢሳ ጎሳዎች ግጭት

ዓርብ፣ ሐምሌ 12 2016

በአፋር እና ሶማሌ የኢሳ ጎሳ መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ግጭት ያስነሳው የሶስት ቀበሌያት አስተዳደር ውዝግብ ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ በፌዴራል መንግስት አመቻችነት የሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮች ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ፡፡ ይሁንና በግጭቱ መደጋገም የተሰላቹት የአከባቢው ነዋሪዎች ስምምነት የመጨረሻው ስለመሆኑ በጉልህ ይጠራጠራሉ።

Krieg betroffene Gebiete in der Afar-Region Äthiopien neu
ምስል Seyoum Getu/DW

የአፋር እና ሶማሊ ኢሳ ጎሳዎች ግጭት

This browser does not support the audio element.

የግጭቱ መንስኤ

ለዓመታት የዘለቀውና ባለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ በደም አፋሳሽነቱ ጎልቶ የቀጠለው በአፋር እና የሶማሊ-ኢሳ ጎሳዎች መካከል የቀጠለው የአስተዳደር ይገባኛል ውዝግብ ለበርካቶች መፈናቀል፣ ግድያ እና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለየም አዳይቱ፣ ገዳማይቱ እና እምቢቶኦ በተባሉ እስካሁን በአፋር ክልላዊ መንግስት ስር በሚተዳደሩ ቀበሌያት ውስጥ በተነሳው የአስተዳደር ይገባኛል ውዝግቡ በሁለቱም ወገን ያሉ ዜጎች ስጋጩ ቆይተዋል፡፡በአፋር ክልል አንድ የአከባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት አከባቢው ላይ ግጭት አስቀጥሏል ያሉትን አብይ ምክኒያት ሲያስረዱ፤ “እነዚህ ሶስት ቀበሌያት በአፋር ክልል ስር የሚተዳደሩ ቢሆንም በቀበሌዎቹ የሶማሊ-ኢሳ ጎሳ ከመብዛታቸው የተነሳ አስተዳደሩ በሶማሊ ክልል ስር ሊሆን ይገባል” የሚል ጉዳይ ውዝግብ ማስነሳቱን አስረድተዋል፡፡ በጅቡቲ በአፋሮች እና በሶማሌዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ ሶስት ሰዎች ተገደሉ

በግጭቱ የደረሱ ሰብዓዊ ቀውሶች 

ይህ ለዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ህዝብ መካከል ግጭት ቀስቅሶ የዘለቀው አወዛጋቢ ጉዳይ ለዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የህልውና ፈተናን የደቀነ መሆኑን የሰብዓዊ ተቋማት መረጃ ያስረዳል፡፡ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከአንድ ወር በፊት በሰኔ መጀመሪያ ባወጣው መግለጫም በአከባቢው ያልበረደው ግጭት የሚያደርሰው ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያሳስበው ገልጾ፤ የፌዴራልም ሆነ የሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮች ግጭቱ እንዲቆም አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቆ ነበር፡፡ በዚሁም ግጭት ምክንያት በአከባቢው ደረሱ ስለተባሉ ቀውሶች የተጠየቁት የኮሚሽኑ የአፋር ክልል እና አከባቢው አስተባባሪ አቶ መሀመድ አህመድ፤ “ጉዳቱ ይህ ነው ብሎ ለመናገር ምርመራ ያስፈልግ ነበር፡፡ በቂ ምርመራ በአከባቢው ለማድረግ ደግሞ አከባቢው ለመንቀሳቀስ ስለሚያስቸግር ምርመራ ማድረግ ባለመቻላችን ከአከባቢው አስተዳዳሪዎች ጋር ሰላም እነዲመጣ ስናሳስብ ነበር” ብለዋል፡፡በትግራይ አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢ ጥቃት
በኮሚሽኑ የሶማሊ ክልል አስተባባሪ ዶ/ር ሰዓድ ደመቀም፤ “በኮሚሽናችን በኩል በአከባቢው ግጭት ምን ያህል ሰብአዊ ውድመት ደርሷል የሚለውን በዝርዝር ለመመርመር በእቅድ ደረጃ ከያዝነው ሀሳብ ውጪ እስካሁን የምናውቀው የሰዎች መሞትና መፈናቀል ብቻ ነው፡፡ ግን አሁን ላይ በአከባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮች መስማማታቸውን ከሚዲያ ሰምተናል” ብለዋል፡፡

አፋር ምስል Mariel Müller/John Irungu/DW

የሁለቱ ክልሎች አዲስ ስምምነት

በሰላም ሚኒስቴር አመቻችነት ተወያይተው በትናንትናው እለት የደረሱበትን ስምምነት በማስመልከት አዲስ አበባ ውስጥ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የሁለቱ ክልሎች አስተዳዳሪዎች ክልሎቹ ችግሩን በሰላም ለመፍታት መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ “መግባባት ላይ የደረስንበት ጉዳይ ግጭት በማቆም እስከታች ህዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ በሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሰላም ማምጣት ነው” ብለዋል፡፡ የሶማሊ ክልል አቻቸው አቶ ሙስጠፌ መሃመድም “በመጀመሪያ ደረጃ የሰው ደም እንዳይፈስ ግጭቱ እንዲቆም ነው የተስማማነው፡፡ በቀጣይም ግጭቱ መልሶ እንዳይነሳ መሬት ላይ እንዲሰራ ከግጭት ነጻ በሆነ አኳን መስራትና ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው የተስማማነው” ብለዋል፡፡በጅቡቲ በአፋሮች እና በሶማሌዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ ሶስት ሰዎች ተገደሉ

የሰላም ስምምነቱ ቀጣይነት

አንድ የአከባቢው ነዋሪ በሰጡን አስተያየት በአከባቢው አሰለቺ ሆኗል ያሉትን ግጭት ለማቆም የተደረሰው ስምምነት በበጎ ጎኑ ብታይም አተገባበሩ ቀላል የሚሆን አይደልም ብለዋል፡፡ “መንግስት ግጭቱን እየተመለከተ ማለፉ አግባብ አልነበረም፡፡ አሁንም በፌዴራል መንግስት አነሳሽነት በሁለቱ ክልሎች መካከል በተደረሰ ስምምነት መሰረት ሰላም ቢመጣ ለሁሉም መልካም ቢሆንም ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ጥረቶች ተደርጎ ስለፈረሰ ገቢራዊነቱ ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም” ብለዋል፡፡ በዚሁ ዓመት ሚያዚያ ወር አከባቢ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአደራዳሪነት ተሳትፎበት በግጭቱ ተኩስ አቆም ተደርጎ ወደ ቀጣይ የሰላም ሂደቱ እንዲሸጋገር ከስምምነት ስለመደረሱ ቢገለጽም ግጭቱ ዳግም ቀጥሎ ማገርሸቱ ይታወቃል፡፡


ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW