1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች ግጭቶች ከተከሰቱባቸው ቦታዎች ኃይሎቻቸውን ለማስወጣት ተስማሙ

እሑድ፣ ግንቦት 7 2014

የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች ተደጋጋሚ ግጭት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ኃይሎቻቸውን አንስቶ በፌድራል ጸጥታ አስከባሪዎች ለመተካት መስማማታቸውን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኢብራሒም ዑስማን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩ ተናገሩ። ክልሎቹ በግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ መስማማታቸው ተገልጿል።

Äthiopien | Ibrahim Usman | Vizepräsident des somalischen Regionalstaates
ምስል Messay Teklu/DW

የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች ግጭቶች ከተከሰቱባቸው ቦታዎች ኃይሎቻቸውን ለማስወጣት ተስማሙ

This browser does not support the audio element.

በሶማሌ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰቱ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁለቱ ክልሎች ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ገዳማይቱ ፣ እንዱፎ እና ገርበኢሴ በተባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ይከሰቱ ነበሩ ግጭቶች ሞት እና መፈናቀል ከማስከተል ባለፈ ሁለቱን ክልሎች የቃል እሰጣ አገባ ውስጥ ሲያስገባቸው ቆይቷል። የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ጅግጅጋ ተገኝተው ከሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ማጠቃለያም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል የተባለ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የተደረገውን ውይይት እና የተደረሱ ስምምነቶችን በሚመለከት ለዶይቼ ቬለ በስልክ አስተያየት የሰጡት የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን በስምምነቱ ቀዳሚው የታጠቁ ኃይሎች ከግጭት አካባቢዎች እንዲወጡ እና የፌደራል ፀጥታ ኃይሎች በነዚህ በተለዩ ቦታዎች እንዲገቡ የሚለው መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ኢብራሂም ለረዥም አመታት በጋራ በኖረው ህብረተሰብ መካከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በየደረጃው ውይይቶች ይካሄዳሉ። በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ የጋራ አቋም መያዙን የጠቆሙት አቶ ኢብራሂም  ዘላቂ ሰላም በማስፈን በኩል ሁሉም የበኩሉን የሚወጣበት መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

በሶማሌ ክልል መቀመጫ ጅግጅጋ በተካሄደው ውይይት የሰላም ሚንስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ጨምሮ የአፋር እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል። በሌላ በኩል ከውይይቱ ቀደም ብሎ በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ድርቅ የሚውል የአስር ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ለሶማሌ ክልል አስረክበዋል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW