የአፋር ክልላዊ መስተዳድር «የህወሓት ቡድን» ድንበር ተሻግሮ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 27 2018
የአፋር ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር «የህወሓት ቡድን» የክልሉን ድንበር ተሻግሮ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ ። የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ መገናኛ ገጹ ባወጣው መግለጫ የህወሓት ታጣቂዎች የክልሉን ድንበር ተሻግረው በመግባት ስድስት ያህል ቀበሌዎች በቁጥጥራቸው ስር ማድረጋቸውን ገልጿል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ ቢሮ ለቀረበበት ክስ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ይፋዊ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጠም። ዶቼ ቬለ ለክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን እና የሰላም እና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
በትግራይ እና የአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች ከሰሞኑ ውጥረት አይሎ መቆየቱን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ። የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ወደ አፋር ክልል ዘልቀው መግባታቸው ከተሰማ በኋላ በአካባቢው የለየለት ጦርነት እንዳይቀሰቀስ በርካቶች ስጋታቸውን በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ገጾቻቸው እያካፈሉ ነው።
የትግራይ የውስጥ ፖለቲካ እንዲሁም ላለፉት ዓመታት የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ከፌዴራል መንግሥቱ እና ተጣማሪ ኃይላት ጋር ሲደረጉ የነበሩ ጦርነቶችን በቅርበት ሲከታተሉ እንደነበሩ የነገሩን አቶ ዳንኤል ብርሃነ እንደሚሉት በአፋር ክልል የተፈጠረው ግጭት ከትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ተነጥለው በወጡ ታጣቂዎች እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ነው።
« ከቅዳሜ እና እሑድ እንደሚመስለን ከእሑድ ጀምሮ ሃራ መሬት ባሉ ልጆች እና በትግራይ ሠራዊት መካከል የተፈጠሩ ግጭቶች ትግራይ ውስጥ ባለው ፖለቲካም አንጻር እንደገናም ደግሞ በመቀሌ ወይም በሕወሃት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ባለው ግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው የማያቸው። መጀመሪያ ህወሓት ራሱ በፈጠረው ችግር ምክንያት ትግራይ ውስጥ የፖለቲካ ልዩነት እንዲሰፋ እና ወደ ሃራ መሬት ልጆች እንዲወጡ አድርጓል። እንደገና ይህ ደግሞ ከፌዴራል ጋር ካለው ፍጥጫም ጋር ደግሞ ስለተቀላቀለ ያው አንጻራዊ መደጋገፍ እንዳለ ደግሞ ማሰብ ይቻላል።»
አቶ ዳንኤል እንደሚሉት ትናንት ምሽት የአፋር ክልል በይፋ ያወጣው መግለጫ ኹነት ገና ትናንት የተፈጠረ ሳይሆን ያለፉትን ጥቂት ቀናት ሲካሄድ የቆየ ነው። በታጣቂ ቡድኖቹ መካከል የተፈጠረው ግጭቱ በቀጥታ ወደ ጦርነት የመግባት ዓላማ ያለው አይመስለኝም ያሉት ተንታኙ ኃይላቱ በየጎራቸው አቅም ለመፈታተሽ እየሞከሩ ሳይሆን አይቀርም ባይ ናቸው።
« የአሁኑ ግጭቶች ረቡዕ እና እንደገና እሑድ ላይ ነበር። እና በተደጋጋሚ የሚደረጉ እና እነዚህ እስካሁን ግፊት ሲደረጉ ከነበሩ የመፈታተሽ እና የመጎነታተል ፣ የመሞካከር ነገር አድርጌ ነው የማየው። ከፌዴራል ጋርም እንደዚያው በንግግር መተነኳኮሶች አሉ፤ በትግራይ በኩል ያሉ ጄነራሎች ፣የፖለቲካ አመራሮች የተለያየ ነገር ይናገራሉ ፤ ከፌዴራል በኩልም እንደዚያው ንግግሮች አሉ። እና እነዚህን ነገሮች ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ለማምጣት ሳይሆን በየራሳቸው በኩል ያለውን ዝግጅት እና መነቃቃት ለማሳየት እና በሌላኛው ወገን ላይ ጫና ለማሳደር ይመስለኛል። »
የአፋር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው የህወሓት ቡድን ብሎ የገለጻቸው ታጣቂዎች በክልሉ በዞን ሁለት መጋሌ ወረዳ ቶንሳ ቀበሌ ፣ ዋራአ እና ሚልኪ በሚባሉ አካባቢዎች በመግባት በአርብቶ አደሮች ላይ የከባድ መሣሪያ በመተኮስ የፕሪቶሪያ ስምምነትን «በግላጭ አፍርሷል» ሲል ከሷል።
በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል የፖለቲካ እና የጸጥታ ኃይሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግላጭ የሚደረጉ መወነጃጀሎች ውጥረት እንዲነግስ እያደረጉ ነው፤ የሚሉት አቶ ዳንኤል ሰሞነኛው ግጭት በፍጥነት በቁጥጥር ስር ካልዋለ ከሀገሪቱ ባለፈ የቀጣናውን ሃገራት ያሳተፈ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል በአጠቃላይ ወደ ለየለት ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
« የራሳቸው ዕድገት ይኖራቸዋል። አንዴ ጎማውን ማሽከርከር ከጀመርክ በኋላ በምን ዓይነት ፍጥነት ይሽከረከራል የሚለውን አካባቢያዊ ሁኔታዎች ናቸው የሚወስኑት። ይህን በአጠቃላይ ከቀጣናዊ ጉዳዮች ጋር ሳያይዘው አጠቃላይ ኢትዮጵያዉያን ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ማስተዋል ይፈልጋል። ሌሎች የውጭም ኃይሎች ከትግራይም ከፌዴራልም በሃራ መሬትም ከዚያ ውጭ ባሉትም ማለት ነው ሌሎች ኃይሎች እጃቸውን ሊከቱበት ስለሚችሉ ባለቤትነት ራሱ የምናጣበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እና በዚያ አግባብ ማሰቡ ጥሩ ይመስለኛል።»
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የባሕር በር ጥያቄ እና የአሰብ ወደብ መሻት ጎልቶ እየተሰማ ባለበት ባሁኑ ወቅት የኤርትራ ባለሥልጣናት ወደ ግብጽ የመመላለስ እና ግብጽ በይፋ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ሚና ሊኖራት እንደማይገባ ይፋዊ አቋም መያዟ ቀጣናዊ ውጥረት አስከትሏል።
ኢትዮጵያ በውስጧ በአማራ ክልል በርካታ የጸጥታ መዋቅሮች እየተሳተፉበት የሚገኙ ግጭቶች አሁንም እንደቀጠሉ ነው። በኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ በመንግሥት እና በተለያዩ የታጣቂ ቡድን አደረጃጀቶች መካከል የሚካሄዱ ግጭቶች ጥፋት እያስከተሉ ነው።
በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት እና በሕወሃት መካከል ግጭት የማቆም ስምምነት ከተፈረመ ሦስት ዓመት ቢሻገርም ጦርነትም ሰላምም ካልነበረበት ጊዜ አሁን ጦርነት ጦርነት ወደ ሚሸት ሁኔታ መጠጋቱ እየታየ ነው። የአውሮጳ ሕብረት ለህወሓት እና የፌዴራሉ መንግሥት ከምርጫ በፊት የተነጋገሩ ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን ግን ምላሽ ያገኘ አልመሰለም። የአፍሪቃ ሕብረት እና አሜሪካን ጨምሮ የፕሪቶሪያ አሸማጋይ ወገኖች ስምምነቱ መጣሱን በተመለከተ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሠ