1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃን ዓለም አቀፍ ገፅታ እንዴት መጠገን ይቻላል?

ዓርብ፣ ሐምሌ 29 2014

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለ አፍሪቃ ሲዘግቡ ስለ ግጭት፣ ሙስና፣ በሽታ፣ የመሳሰሉ .. መጥፎ ርዕሶች ላይ ብቻ ያተኩራሉ ወይም በአጠቃላይ በጎ ታሪኮችን ይዘነጋሉ እየተባሉ ይከሰሳሉ። ታዲያ አፍሪቃውያን ወጣቶች ይህንን ገፅታ እንዴት ሊቀይሩ ይችላሉ? ማህበራዊ ሚዲያ መፍትሄ ሊሆን ይችላል?

Südafrika Kapstadt | Brand im Parlament
ደቡብ አፍሪቃምስል Rowan Spazzoli via REUTERS

This browser does not support the audio element.

በተለይ የምዕራቡን ዓለም መገናኛ ብዙኃን ቀልብ የሚስበው አፍሪቃ ውስጥ የሚከሰቱ መጥፎ ነገሮች ብቻ ናቸው ሲሉ በርካታ አፍሪቃውያን ይተቻሉ። ስለ ድርቅ፣ አምባ ገነን መንግስታት ፣ድህነት ወዘተ ነው የሚዘግቡት ይላሉ።  ጥቂት አፍሪቃውያን ወጣቶች ለዶይቸ ቬለ የሰጡትን አስተያየት ተከታዩ ነው፦    

« ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ይዘት ሲመርጡ  የተሻለ ነገር መስራት ይችላሉ።ስለአፍሪቃ ባህል እና ልምድ !  

«አሁንም ድረስ የቀኝ ገዢ አመለካከት አፍሪቃ ላይ ለማንፀባረቅ ይሞከራል። አፍሪቃ ላይ ብዙ የአሜሪካ ተፅዕኖ አለ»  

« ወደ አፍሪቃ መጥተው እየተከናወኑ ስላሉ ጥሩ ነገሮች በሙሉ ሊዘግቡ ይገባል። ስላለው ልማት ፤ ስላለው እድገት፤ ስላለው ለውጥ  አፍሪቃም እያደገች እንደሆነ ለዓለም ሊያሳውቁ ይገባል። »  

«አብዛኛውን ጊዜ አፍሪቃ የምትገለፀው በመጥፎ መንገድ ነው። ስለሆነም ይህንን ለመለወጥ ይረዳል የምለው  የአፍሪቃ መገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች  ወጣ ብለው የአፍሪቃን እውነተኛ ታሪክ ሊዘግቡ ይገባል። ያ ካልሆነ ግን የፈለጉትን ብቻ ነው የሚዘግቡት። »  

«ዘገባዎቻቸው አሉታዊ  ብቻ ሳይሆኑ ሚዛናዊም አይደሉም» ሲል ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን የሚተቸው ሌላው አፍሪቃዊ ወጣት እንዳልክ ነው።  « ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ሀገራቸው ላይ ያለው ተፅዕኖ፣ በሰሜኑ ጦርነት ብዙ ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎችን ታዝበናል።

  ለዶይቸ ቬለ DW በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መጣጥፎችን የሚያቀርበው በፍቃዱ ኃይሉ « ምዕራባዊ ብዙኃን መገናኛዎች አፍሪቃን የሚመለከቱበት መንገድ የተንሸዋረረ ነው» ሲል በበርካታ አፍሪቃውያን በቀረቡት ትችቶች ይስማማል። በፍቃዱ በአሁኑ ሰዓት መብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል ወይም በእንግሊዘኛ ምህጫሩ CARD የተሰኘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተባባሪ መስራች እና ዋና ዳሬክተር ነው።  « አፍሪቃን ማየት ወይም ማሳየት የሚፈልጉት፤ ከግጭት፤ ረሀብ ፣ሙስና አንፃር ነው። እና ከምዕራባውያን ሀገራት ሆነው የሚዘግቡ ጋዜጠኞች በተለይ የአፍሪቃ ተወላጅ ያልሆኑ... በተንሸዋረረው፣ አውሮፓውያን አፍሪቃውያንን በሚያዩበት መልክ ነው የሚያዩት ። እና ያንን አጋነው እና የበለጠ አዛብተው የማቅረብ ልምድ አለ። እና ክሱ ዝም ብሎ ከመሬት የተከሰተ አይደለም። 

ለአፍሪቃውያን ወጣቶች መድረክ የሚሰጠው የዶይቸ ቬለ 77 ከመቶው ዝግጅት ሰሞኑን በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዶ ነበር። አፍሪቃውያን ጋዜጠኞችስ ስለ አፍሪቃ ምን ይዘግባሉ? የአፍሪቃን ዓለም አቀፍ ገፅታን ለመጠገን ማህበራዊ ሚዲያስ ይረዳ ይሆን?  ከተወያዮቹ አንዱ የሆነው  የደቡብ አፍሪቃ SABC የቴሌቪዥን እና ራዲዮ ጋዜጠኛ ኦድሪያን የዜና ሽፋን ቢያገኝ የሚለው  « አሀዝ ከመጥራት ባሻገር ሰዎችን ሊስቡ ስለሚችሉ ታሪኮች፣ ጉዳዩ የሰው ልጅ ላይ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ ፣ ችግር ሊሆን ይችላል። ይሁንና ስለጥሩ ነገሮችም መዘገብ አለበት። ስለአስቀያሚ ሁኔታ ብቻ መሆን የለበትም። » ይላል።  

አዴንኬ የናይጄሪያ የአየር ንብረት ተሟጋች  ናት። በርግጥ አስደሳች ዜና ባይሆንም የሚያስጨንቃት የአየር ንብረት ቀውስ የዜና ሽፋን ቢያገኝ ትመርጣለች።  « የሰብዓዊ ቀውስ ምን ያህል  በየቀኑ እየተባባሰ እንደሆነ እናያለን፤ ለምሳሌ የቻድ ሀይቅ አካባቢ። ቅርብ ጊዜ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም IMF አንድ ዘገባ አውጥቶ ነበር  የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት የአፍሪቃን ሁኔታ እንደጋረደው። እና በሀገራት መካከል የሚሰጠው ክብደት ልዩነት አለው። ስለሆነም ስለዚህ ሰብዓዊ ቀውስ ትኩረት ቢያገኝ እመርጣለሁ።»  

ሞኪ ማኩራ «አፍሪካ  ፊልተር» የተሰኘ የጥናት ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው። ተቋሙ ለምሳሌ የአፍሪቃ መገናኛ ብዙኃን ለአፍሪቃ እንዴት የዜና ሽፋን እንደሚሰጡ ለመፈተሽ በ15 ሀገራት የሚገኙ 60 የዜና ማሰራጫ አውታሮችን ይዘት ገምግሞ ነበር።ተቋሙ ያገኘው ውጤት ግን ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ርዕሶች ብዙም የተለየ እንዳልነበረ ነው ስራ አስኪያጇ የሚያስረዱት  «አፍሪቃውያን ስለሌሎች አፍሪቃ ሀገራት ከሚያነበቡት 81 በመቶ ገደማ ያህሉ መጥፎ ዜና እንደነበረ ነው ልንረዳ የቻልነው። « ሀርድ ኒውስ » ወይም ከበድ ያለ የምንለው ዜና ነው።  ከባድ ዜና ደግሞ መጥፎ ነገር ይበዛዋል። ስለ ሰብዓዊ ቀውስ ነው የሚወራው፤ ስለዚህ ደግሞ የአፍሪቃ መገናኛ ብዙኃን በቂ ሽፋን ይሰጣሉ። የሚጎል ነገር ቢኖር ለስለስ ያለ ሰውን የሚስብ ነገር ነው። ስነ ጥበብ እና ባህል።  ስለ አፍሪቃ ስናስብ «አፍሮ ቢት » ሙዚቃን ወደ ውጪ ልናስተዋውቅ እንችላለን። ግን ያን ያህል ሽፋን አንሰጠውም ። ብዙ የሚጎሉ ነገሮች አሉ፤ ለዚህ ደግሞ ብዙ መሠራት ይኖርበታል»  

ታድያ ሚኪ ባነሱት ችግር ላይ የአፍሪቃውያን ጋዜጠኞች ምን ቢደረግ ጥሩ ነው ይላሉ? በምስራቅ አፍሪቃ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ጋዜጠኛ አግሪ ሙታንቦ ፈተና ነው የሚለው በቂ የአፍሪቃ የዜና ኤጀንሲዎች አለመኖራቸው ነው።  « የአፍሪቃ መገናኛ ብዙኃን አንድ ማድረግ አለብን ብዬ የማስበው ነገር መረጃዎችን የበለጠ መለዋወጥ ብንችል የሚል ነው። ይህ የአፍሪቃን ታሪክ በተሻለ መልኩ ለማቅረብ ይረዳን ይሆናል። » 

ከምዕራባውያን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አንዱ ዶይቸ ቬለ DW ነው። ዘገባዎቹ ምዕራብ ተኮር ናቸው፣ሲባልም ይተቻል። ሪቻርድ ዎከር የDW ዓለም አቀፍ ዝግጅት ኃላፊ ናቸው።አንድ ርዕሰ ጉዳይ የዜና ሽፋን የሚያገኘው መቼ ነው ሲል አወያዩ ጋዜጠኛ ቶሚ ጠይቋቸው ነበር፤ « አጣዳፊነቱ እና ወቅታዊነቱ ይወስነዋል። ምን ተከሰተ? ዜናው ምን ተፅዕኖ ይፈጥራል? ቀረቤታው ? ጣቢያው በብዛት የሚጠይቀው ነገር ነው። ለአንድ አካባቢ ወይም ለአንድ ሀገር ማህበረሰብ የምንዘግብ ከሆነ በርግጥ አንድ ነገር በቂ  ሊሆን ይችላል። DW ግን ዓለም አቀፍ ነው። ስለዚህ በርካታ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ግድ ይላል። ይህ ይመስለኛል አንዳንዴ የዜና ክፍላችን ያለው ፈተና። በርሊን ተቀምጠን አቅራቢያችን ያለው ነገር ምንድን ነው ስንል ፤ አውሮፓ ውስጥ ለምሳሌ የዩክሬን ጦርነት አለ። ለአስርተ ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ  እዚሁ አቅራቢያችን ተከስቷል። እና መሳብ ይጀምራል። » 

ምስል ISAAC KASAMANI/AFP/Getty Images

ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን ይበልጥ በአቅራቢያቸው ያለው ቀውስ ላይ አተኩረው ባሉበት በአሁኑ ወቅት ለአፍሪቃ ትኩረት እንዲሰጥ በተለይም የአፍሪቃን ዓለም አቀፍ ገፅታ ለመጠገን የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይረዳ ይሆን? በፍቃዱ ኃይሉ ማህበራዊ ሚዲያ ሙሉ አቅም የለውም ይላል፤ «ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተጣለው ተስፋ አሁን አሁን ይዘቱ እየጠፋ ነው።  ከጊዜ በኋላ መልሰው በጣም ኃይል ያላቸው አካላት ትርክቱን መልሰው በበላይነት እየተቆጣጠሩት ነው። ስለዚህ አሁንም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በአብዛኛው ስለ አፍሪቃ የሚናገሩት አፍሪቃውያን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ማህበራዊ ሚዲያ በጥቅሉ አይሆንም ሳይሆን ሙሉ አቅም የለውም። ትንሽዬ ግን የመልስ ምት ይሰጣል።» 

በጋና የጋዜጠኞች ተቋም የሚዲያ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤቼ ሲካንኩም ማህበራዊ ሚዲያ መፍትሄ ነው ብለው አያምኑም። ይልቁንስ ማናቸውም የማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ መገናኛ ብዙኃን ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር አለ።  «ዘገባዎቻችን ፌስ ቡክ፤ ትዊተር ወይም ዩ ቲውብ ላይ ቢሆኑ እንኳን ፤ የቃላት አገላለፃችን ስርዓቱን የጠበቀ መሆን አለበት፤ ትክክለኛነቱ ፤ አውዱ ወሳኝ ነው። ስለ አፍሪቃውያን አኗኗር፤ ተሞክሮ ስናወራ የሰዎችን ክብር በማይነካ መልኩ መሆን አለበት» 

ልደት አበበ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW