1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃዉያኑ ስደተኞች ስጋት በእስራኤል።

ረቡዕ፣ መጋቢት 26 2010

እስራኤል በሀገሯ የሚገኙ  አፍሪቃዉያን ስደተኞችን በሚመለከት ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ  ድርጅት ጋር ያደረገችዉን ስምምነት ሰረዘች። ይህንን ተከትሎ በሀገሪቱ የሚገኙ ከ 37 ሺህ በላይ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ እየተገለፀ ነዉ።

Israel Afrikanische Migranten
ምስል picture-alliance/AP/T. Abayov

Israeli Cancelled an Agreement with UNHCR - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

 

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት በበኩሉ እስራኤል  ጉዳዩን እንደገና  ታየዋለች የሚል ተስፋ እንዳለዉ ገልጧል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ፣ ዩኤንቺሲአር  እና በእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትኒያሁ መካከል ባለፈው ሰኞ የተደረገዉ ስምምነት  በሀገሪቱ የሚገኙ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ወደሌላ ሀገር እንዲዛወሩና ገሚሶቹ በእስራኤል  የመኖሪያ ፈቃድ እድያዲያገኙ የሚያደርግ ነበር። ይሁን እንጅ  የሀሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ስምምነቱን የሰረዙት በሰዓታት ዉስጥ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ። ለስምምነቱ መሰረዝ በሀገሪቱ በሚገኙ የቀኝ ዘመም ተቃዋሚ ፓርቲወች ግፊት መሆኑ እየተገለፀ ነዉ።ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ የሚገኙ ከ37 ሽህ በላይ አፍሪቃዉያን ስደተኞች በስጋት ዉስጥ መሆናቸዉ እየተነገረ ነዉ።በእስራኤል ሀገር ለ10 ዓመታት በስደት የቆዩት  አቶ ደረሰ ሽኩር ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት  ስምምነቱ ስደተኞቹን ወደተለያዩ ምዕራባዊያን ሀገሮች እንዲሄዱ የሚፈቅድ ስለነበር አብዛኛዉ ስደተኛ ተስፋ አድርጎ  የነበረ ቢሆንም፣ መሰረዙ ከተሰማ ወዲህ በስጋት ላይ መሆናቸዉን ነዉ የሚናገሩት።
ስደተኛዉ ዛሬ ሲያለቅስ ነዉ የዋለዉ።በጣም በሀዘን ላይነዉ ያለዉ።ለምን መስራት አይችልም ተከልክሏል።የአንድ ወር ቪዛ ነዉ የሰጡት።ከአፕሪል 9 ጀምሮ አፈሳ እንጀምራለን ብለዋል።በስጋትና በጭንቀት ልጆችን ይዘዉ፤ ልጆች ትምህርት ቤት አይሄዱም ።በአሁኑ ስዓት ቤት ዉስጥ ነዉ አብዛኛዉ ወላጅ  ቁጭ ብሎ ነዉ ያለዉ።የሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነዉ ያለዉ።ትናንትና ወዲያ ተደስተን ነበር።ይህን ዉሳኔ  ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲያሳልፉ ተደስተን ነበር።ያ ደስታ በ ከ6 ስዓት በኋላ ወደ ሀዘን ነዉ የተቀየረዉ።»ብለዋል።

ምስል Getty Images/AFP/J. Guez

በአብዛኛዉ ከሱዳንና ከኤርትራ የሆኑት እነዚህ ስደተኞች በአንስተኛ የቀን ስራና በችግር ዉስጥ ለበርካታ አመታት በሀገሪቱ የቆዩ ናቸዉ።በአብዛኛዉም ርካሽ  የቤት ኪራይ ፍለጋ በደቡብ ቴልአቪብ  በኩል ሰፍረዉ የሚገኙ ሲሆን  በአካባቢዉ የሚኖሩ   የሀገሪቱ  ዜጎችም መኖሪያችንን አጣበቡ በሚል የስደተኞቹን በዚያ አካባቢ መስፈር እየተቃወሙ መሆናቸዉን ነዉ አቶ ደረሰ የገለፁት።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ ዊሊያም ስፒንድለር እንደሚሉት ስምምነቱ  ለሀገሪቱም ይሁን ለስደተኞቹ ጥሩ መፍትሄ ቢሆንም ባልጠበቁት ሁኔታ መሰረዙን መስማታቸዉ እንዳስገረማቸዉ ገልፀዋል። ያም ሆኖ ግን ሀገሪቱ ጉዳዩን እንደገና በማጤን ለስደተኞቹም  የተሻለ መፍትሄ ይገኛል የሚል ተስፋ አላቸዉ።                                             « ለእነዚህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ለሚገኙ ስደተኞች መፍትሄ ይገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።ስደተኞቹ ወደ 39 ሺህ ናቸዉ ተብሎ ይጠበቃል።ከእነዚህ ዉስጥ አብዛኛወቹ ከኤርትራና ከሱዳን የመጡ በመሆናቸዉ ወደ ሀገራቸዉ መመለስ አይችሉም።ምክንያቱም ክትትል፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወይም በሀገሮቻቸው አካባቢ የሚካሄዱ ውዝግቦች ያሰጓቸዋል።»
እንደ ዩኤንቺሲአር ቃል አቀባይ እስራኤል ብዙ የቴክኖሎጅ  አማራጭ ያላት ሀገር በመሆኗ እነዚህን ስደተኞች የተለያዩ ስልጠናወችን በመስጠት ወደ ስራ ልታሰማራና ልትጠቀም የምትችልበት እድል አላት።ቃል አቀባዩ አያይዘዉም ሀገሪቱ የእነዚህን አፍሪቃዉያን ስደተኞች ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ዓለም ዓቀፍ ግዴታዋን እንድትወጣ  ያስችላታል ብለዋል። አለም አቀፉ ህብረተሰብም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
«ስምምነቱ ጥሩ ነዉ ለነዚህ ሰወች መፍትሄ የሚሰጥና የእስራኤልን ፍላጎትም የሚያከብር ነዉ።ምክንያቱም ዓለም ዓቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት ያስችላታል። ለዚህም የሌሎች ሀገራትን ድጋፍ ታገኛለች ።  ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም  16 ሽህ የሚሆኑ ስደተኞችን በመቀበል ፣  መልሶ በማስፈር፣ የስራ ቪዛ በመስጠት፣ቤተሰብን መልሶ በማገናኜት፣ በስፖንሰርሽፕ ና በሌሎች መንገዶች ከእስራኤል ጋር በመተባበር  ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። » 
እስራኤል አፍሪቃዉያን ስደተኞች ሀገሪቱን ለቀዉ እንዲወጡ ስታስጠነቅቅ ቆይታ በኋላም  ወደመጡበት ለመመለስ ወይም ወደ ሩዋንዳ  ለመላክ  ወስና ነበረ። ይህንን በተመለከተም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተቃዉሟቸዉን ሲገልፁ ፣የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም  ዉሳኔዉን ዉድቅ አድርጎታል።

ምስል Reuters

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW