የአፍሪቃውያን ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴ ጥያቄ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 12 2017
የአፍሪቃውያን ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴ ጥያቄ
የአፍሪቃ ሕብረት በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ.ም የሰዎችን ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴ ደንብ አጽድቋል። አላማው አፍሪቃውያን ከአንዱ ወደሌላው የሕብረቱ አባል ሀገር ተንቀሳቅሰው መኖርም ሆነ መሥራት እንዲችሉ የሚል ነው። ያም የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ነጻ የንግድ አካባቢን ለመፍጠር በቀጣዩ ዓመት ሕብረቱ አጽድቆ በ2021 ተግባራዊ ለማድረግ ያለመውን ደንብ እንዲያጠናክር የታሰበ ነበር። ሆኖም ግን እስካሁን አራት ሃገራት ብቻ ናቸው ይህን በየግላቸው ያጸደቁ። ማሊ፤ ኒዠር፣ ሩዋንዳ እና ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ። 32 ሃገራት የፈረሙት ይህ ውል ቢያንስ በ15ት ሃገራት እንዲጸድቅ ይጠበቃል።
የአፍሪቃ ሕብረት ባለሥልጣናት የክፍለ ዓለሙን ንግድ ለማመቻቸት ያለመው ውል በአባል ሃገራት ጸድቆ ተግባራዊ ለመሆን ማዝገቡ አሳስቧቸዋል። የአፍሪቃ ሕብረት የጤና፤ ሰብአዊ ጉዳዮች እና ማኅበራዊ ልማት ኮሚሽነር አማ አዶማ ቱውም አሞህ እንደሚሉት አፍሪቃውያን ከአንዱ አባል ሀገር ወደሌላው ያለ ይለፍ ፈቃድ መንቀሳቀስ ሳይችሉ የንግድ ትስስሩን ማሳካት የማይታሰብ ነው።
«ነጻ የሰዎች ሆነ የዕቃዎች እንዲሆም የአገልግሎቶች እንቅስቃሴ ከሌለ የሚታሰበውን የአፍሪቃ የእርስ በርስ ትስስር ማሳካት አይቻልም። አዎን ምክንያቱም መነገድ እንፈልጋለን። ነገር ግን የሰዎችስ ጉዳይ? በነጻነት መንቀሳቀስ ካልቻሉ ንግድ በእራሱ ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል። ገንዘብ ሊያጡ ይችላሉ የሚለው ሃሳብ፤ በመሠረቱ እኔ ይህን አልቀበለውም ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ያለ ይለፍ ፈቃድ የሚያስተናግዱ በርካታ አባል ሃገራት አሉን። አዎ፤ ለምሳሌ ሩዋንዳ፤ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ በመሠረቱ ቪዛ የማይጠይቁ ሃገራት ናቸው። »
ለምን ብዙዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት የነጻ ዝውውርን መወሰን አቃታቸው?
ምንም እንኳን ካለ ይለፍ ፈቃድ አፍሪቃውያን በክፍለ ዓለማቸው መንቀሳቀስ የሚለውን ሃሳብ ቢደግፉምደንቡን በየሀገራቸው ተቀብለው ለመወሰን የቻሉት በጣም ጥቂት ናቸው። ለዚህ ደግሞ በዋናነት የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ለበርካቶቹ ሃገራት ስጋት በመሆኑ ስምምነቱን ለማጽደቅ እንዲያቅማሙ እንዳደረጋቸው አፍሪካን ራይዚንግ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ ሃርዲ ያኩቡ ይገምታሉ።
የአፍሪቃ ሕብረት የሕግ አስፈጻሚ አካል የሆኑት ኬናዊቱ ሴናተር እና የፓን አፍሪቃ ፓርላማ አባል ማርግሬት ካማር በበኩላቸው የደኅንነቱ ስጋት ጎን ለጎን የተቀናጀ የድንበር አስተዳደር ሁኔታ አለመኖር ዋናው እንቅፋት ነው ባይ ናቸው።
«በአብዛኞቹ ተጓዳኝ ሃገራት መካከል ያሉት ብዙዎቹ ተግዳሮቶች ተመሳሳይ መሆናቸውን ተረድተናል። ሁሉም ስለደኅንነቱ ስርዓት እና የድንበር ጉዳዮች መጠነኛ ፍርሃት አላቸው፤ ድንበሮች ሲከፈቱ ከአውሮፕላን ማረፊያዎች እስከ አውቶብሶች ያሉትን ሥርዓቶች ገና እንዳላጣጣምናቸው ተገንዝበናል። ድንበሮች ሲከፈቱ ወደዚያ የሚገቡ አባል ተጓዳኝ ሃገራት ተጠያቂነት እንዳለባቸው መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ሰዎች ይመጣሉ፤ መታወቅ አለባቸው፤ ለዚህም ተጠያቂነት መኖር አለበት»
ሩዋንዳ፤ የክፍለ ዓለሙ አብነት
በሌላ በኩል ደግሞ የገቢ ጉዳይም አለ። በርካታ የአፍሪቃ መንግሥታት ከይለፍ ፈቃድ ማለትም ቪዛ የውጭ ምንዛሬ የማግኘት አጋጣሚው አላቸው። ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴን ተግባራዊ ማድረግ የገቢ መቀነስ ሊያስከትል ይችላል ብለው ይሰጋሉ። ቱውም አሞህ ግን ይህን አይቀበሉም። እንደውም የተሻለ ገቢያ ያስገኛል በሚል በምሳሌነት ሩዋንዳን ያነሳሉ።
«ሩዋንዳ በጣም ግሩም እማኝነት ሰጥታለች፤ እንደውም በራቸውን ለሌሎች ሃገራት ክፍት በማድረጋቸው እና ካለ ቪዛ ሰዎች እንዲገቡ በመፍቀዳቸው ተጨማሪ ገንዘብ ከሌላ አካባቢ አግኝታለች። እናም ሩዋንዳ በጣም ጥሩ ምሳሌ ናት፤ የሀገር ጎብኚዎችን ቁጥር ማሳደግ ሲጀምሩ፤ ለቪዛ 200 ዶላር ከሚያስከፍሉት ይልቅ፤ በሀገራቸው ውስጥ ቱሪስቶቹ ከሚያወጡት ገንዘብ ብዙ ማግኘት ቻሉ።»
ሩዋንዳ በዚህ ረገድ ውሉን ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ በመሆን እየተጠቀሰች ነው። እንደውም ኪጋሊ የአየር ሆነ የየብስ የድንበር አካባቢዋን አሰናስላ በስልት ማቀናጀቱም ገቢዎችን መቆጣጠሩ ተሳክቶላታል።
የአቻ ለአቻ ልምድ ልውውጥ
የአፍሪቃውያን በክፍለ ዓለማቸው በነጻ የመዘዋወርን ውል የማጽደቁ ርምጃ የተጓተተበት የአፍሪቃ ሕብረት በሃገራት መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ጥረቱን ጀምሯል። የመጀመሪያው መርኀግብር አክራ ጋና ላይ በያዝነው ወር ተካሂዷል። ሌሎች ቀጣይ የአቻ ለአቻ ልምድ ልውውጥ መድረኮችንም በተመሳሳይ ለመቀጠል አቅዷል። ቱውም አሞህ ሃገራት መፍትሄዎች እንዳሉ አንዳቸው ከሌላቸው መማር የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲሆን መታሰቡን ጠቁመዋል። ነጻ እንቅስቃሴ በተግባር ሥራ ላይ ሳይውል ስለ ነጻ ንግድ አፍሪቃ ውስጥ ማሰብ አይቻልም ያሉት ማርግሬት ካማርም እንዲሁ ይህን ውል በየግላቸው እንዲያጸድቁ የአፍሪቃ ሃገራትን ማስረዳትና ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በነገራችን ላይ በያዝነው ሳምንት ነው ኬንያ ከሶማሊያ እና ሊቢያ በቀር ለበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎች የይለፍ ፈቃድ መስፈርቷን ያነሳችው። አድማጮች በዚሁ በሁለት ርዕሰ ጉዳዮችን የቃኘው የዕለቱ ትኩረት በአፍሪቃ ጥንቅር አበቃ። ሸዋዬ ለገሠ ነኝ መልካም የሳምንት መጨረሻ
ሸዋዬ ለገሠ/አይዛክ ካላዲዝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ