1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ

ሐሙስ፣ ጥር 16 2016

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ «ግልጽ ወደሆነ ጦርነት ይገባሉ የሚል ሥጋት» እንደሌላቸው አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ለዶቼ ቬለ ተናገሩ።

ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ
ሶማሊላንድ በርበራ ወደብምስል Brian Inganga/AP/picture alliance

የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ 

This browser does not support the audio element.


ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ «ግልጽ ወደሆነ ጦርነት ይገባሉ የሚል ሥጋት» እንደሌላቸው አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። የኢትዮጵያ መንግሥት በስምምነቱ በተቀመጠው ቀነ ገድብ መሠረት በቀጣይ የሚወስደው እርምጃ የቀጣናውን እጣ ፋንታ እንደሚወስነው የገለፀት እኒሁ ተንታኝ ልዩ ልዩ ንግግሮች ይኖራሉ ብለው እንደሚያምኑ እና «ባንድም ይሁን በሌላ መልኩ ሁሉንም አካላት በተወሰነ መልኩ ፍላጎታቸውን የሚያረካ ስምምነት ይፈጠራል» ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።

አካባቢው «ተፃራሪ እና ተደጋጋፊ» ፍላጎት ያላቸው አገሮች መራኮቻ መሆኑን የገለፁት እኒሁ ስማቸው እንዲገለጽ የማይፈልጉ የዘርፉ ተንታኝ «ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብም ሆነ ሃገራት በቀጣናው የፀና ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ወደ ጦርነት መገባቱን አይፈቅዱትም» ብልዋል። 
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ ኢትዮጵያን እና ሶማሊላንድን ያደረጉት ስምምነት «አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ብሎም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ» በማለት ውድቅ የሚያደርግ ሕግ በፊርማቸው አጽድቀዋል። ሰሞኑን በሰጡት ቃለ ምልልስ ደግሞ የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት እንደሚገነዘቡ ሆኖም አዲስ እበባ ስምምነት ማድረግ ካለባትም ከሞቋዲሾ ጋር መሆኑን አመልክተዋል።

ወትሮውንም በጦርነትና ግጭት፣ ባለመረጋጋት ፣ በድህነትና ኋላቀርነት ፣ በድርቅና ስደት የሚታወቀው ግን ደግሞ የዓለም የመርከብ ምልልስ እና የንግድ ማሳለጫ ሁነኛ መስመር መገኛ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር አካባቢ ይህ አዲስ ስምምነትን ትከትሎ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን የሚለው ትኩረት ሳቢ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው በኢትዮጵያእና በአፍሪካ ሕብረት የሶማሊላንድተወካይ አቶ አብዱላሂ ሞሃመድ በቀጣይ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀው ለጊዜው ከመናገር ተቆጥበዋል። የሶማሊላንድ መንግሥት ማንኛውንም የውጭ ጣልቃገብነት በጽኑ እንደሚቃወም በተለይ የግብጽ መንግሥት ጉዳዩን እያራመደ ያለበትን አካሄድ እንዲያስተካክል ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW