የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበርና አዲሱ የህብረቱ ባለስልጣን
ማክሰኞ፣ ጥር 26 2001ከዚሁ ጎን፡ የአፍሪቃ መንግስት ምስረታን ጉዳይ የሚከታተል አንድ የአፍሪቃ ህብረት ባለስልጣን ለማቋቋምም ወስኖዋል። ስለአዲሱ ባለስልጣን እና የጋዳፊ ሊቀመንበርነት በህብረቱ ስራ ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽዕኖ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ሉድገር ሻዶምስኪ የጀርመናውያኑን የዓለም አቀፍና ያካባቢ ጥናት ተቋም ባልደረባ ዶክተር ሮልፍ ማየርን አነጋግሮዋል፡ አርያም ተክሌ የቃለምልልሱን ከፊል ይዘት እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች።
የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽንን የሚተካው አዲሱ ባለስልጣን የተባበረው የአፍሪቃ መንግስት ገሀድ ሊሆን የሚችልበት መንገድ መኖር አለመኖሩን ይፈትሻል። ይሁንና፡ የዚሁ ባለስልታን መቋቋም ለህብረቱ በርግጥ የተፈለገውን ጠቃሚ ውጤት ማስገኘቱን ለዶይቸ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት የቀድሞ የጀርመናውያኑን የዓለም አቀፍና ያካባቢ ጥናት ተቋም ባልደረባና ተንታኝ ሆፍማን ማየር ተጠራጥረውታል።
« አዲሱ አካል ግራ መጋባት ሊፈጥር ይችላል ብዬ አስባለሁ። የአፍሪቃ ህብረት ከተመሰረተ በኋላ እንዳዲስ የተ ቋቋመው የህብረቱ ኮሚስን እንደሚታወቀው የተዋቀረው በአውሮጳ ህብረት መልክ ነነው። ቋሚ ክፍሎች ያሉት ይኸው ኮሚሽን ተጨባጭ መዋቅር እስኪይዝ ድረስ ጥቂት ጊዜ ወስዶ ነበር። ምንም እንኳን አፍሪቃውያቱ ሀገሮች ብሄራዊ ሉዓላዊነታቸውን ለመተው ዝግጁ ባይሆኑምና የተባበረ የአፍሪቃ መንግስት የሚለውን አጠራር ሆን ብለው ባያነሱትም፡ አዲስ መጠሪያ የያዘውን ባለስልጣን አንድ ርምጃ ወደፊት ለማራመድ እንደሚያስችል መልካም ራዕይ ሊመለከቱት ይችሉ ይሆናል። እና፡ በተለይ ጋዳፊ በሚቀጥለው አንድ ዓመት ህብረቱን በሊቀመንበርነት በሚመሩበት ሁኔታ በመጠቀም ከሌሎች መሪዎች ጋር ሳይነጋገሩ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ መሞከራቸው እንደማይቀር ሳስብ፡ የባለስልጣኑ መቋቋም በአዲስ አበባ ለሚገኘው ህብረት ዕለታዊ ስራ ከግራ መጋባት አልፎ በተጨባጭ የሚያበረክተው ድርሻ የሚኖር አይመስለኝም።የመምራት ስራቸውን በትናንቱ ዕለት ጀመሩ። ህብረቱ አንድ የተባበረ በተግባር ለማስተርጎም ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ስራቸውን በተረከቡበት ስርዓት ወቅት ባሰሙት ንግግር አስታውቀዋል። »
እንደሚታወቀው፡ የሊብያ መሪ ኮሎኔል ጋዳፊ ከብዙ ጊዜ ወዲህ የሚታገሉለት የተባበረው የአፍሪቃ መንግስት ምስረታ ህልማቸውን ገሀድ ለማስደረግ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ የህብረቱን ሊቀመንበርነት ስልጣን ከታንዛንያዊው ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ በተረከቡበት ጊዜ ባሰሙት ንግግር አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ፡ ከተባበረው የአፍሪቃ መንግስት ምስረታ በፊት፡ ያካባቢ ድርጅቶች እንዲጠናከሩ ከሚፈልጉት ደቡብ አፍሪቃንና ናይጀሪያን ከመሳሰሉ ሀገሮች ዘንድ ብርቱ ተቃውሞ እንደገጠማቸውና የሊቀመንበርነቱ ስልጣናቸው ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ሀገሮች አቋም እንደማይስለውጥ ነው የጀርመናውያኑን የዓለም አቀፍና ያካባቢ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዶክተር ሮልፍ ማየር የሚገምቱት።
« ከስድስት ወራት በኋላ በሚካሄደው ቀጣዩ የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ አዲሱ ባለስልጣን በይፋ ተቀባይነትን ማግኘት ይኖርበታል። ከዚህ አልፎ ግን አዲሱ አካል ለህብረቱ መዋቅር የሚያመጣው ለውጥ በግልጽ አይታወቅም። ፕሬዚደንት ኪክዌቴ ባሰሙት የመሰናበቻ ዲስኩራቸውም ኤኮዋስ፡ ሳዴክ እና የምስራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብን የመሳሰሉ ያካባቢ ድርጅቶች እንዲጠናከሩ በግልጽ ያስታወቁበት ድርጊት በገሀድ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የሚያምኑትን ወገኖች አባባል ይበልጡን አጉልቶዋል። ምንም እንኳን፡ ጋዳፊ በዚሁ ስልጣናቸው ወቅት የራሳቸውን ሀሳብ ለማስተጋባት ቢጠቀሙበትም፡ ብዙ አፍሪቃውያን መሪዎች አይከተሉዋቸውም። በመሆኑም ከአንድ ዓመት በኋላም በህብረቱ ውስጥ ብዙ ለውጥ አይኖርም። »
አንዳንድ ሀገሮች የጋዳፊን ሊቀ መንበር ሆነው መመረጥ አልደገፉትም። ሆኖም፡ በአፍሪቃ ህብረት ደምብ መሰረት፡ የህብረቱ ሊቀመንበርነት ስልጣን በያመቱ በተለያዩት የአህጉሩ አካባቢዎች መካከል የሚዛወር እንደመሆኑና የዘንድሮ ስልጣንም ለሰሜን አፍሪቃ እንደመመደቡ መጠን፡ በምርጫው ስነስርዓት ላይ የተገኙት ብቸኛው የሊብያ መሪ ኮሎኔል ለዚሁ ስልጣን በቅተዋል። የደቡባዊ አፍሪቃ መንግስታት መሪዎች ግን ቀጣዩ የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በማዳጋስካር የሚደረግበትን ውሳኔ ምክንያት በማድረግ የህብረቱ ሊቀመንበርነቱ ስልጣን ለነርሱ እንዲሰጣቸው ነበር የፈለጉት።
Quellen: DW
AA,NM