1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአፍሪቃ መሪዎች ሩሲያና የክሬንን ሊያደራድሩ ነው

ረቡዕ፣ ግንቦት 9 2015

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በስድስት የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች የሰላም እቅድ መቅረቡን ገልፀዋል።የሩሲያ እና የዩክሬን አቻዎቻቸውም የአፍሪቃን የሰላም ዕቅድ ተቀብለው ለመወያየት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

Präsident Ramaphosa empfängt den Premierminister von Singapur, Hsien Loong, in Kapstadt
ምስል፦ Esa Alexander/REUTERS

የአፍሪቃ የሰላም እቅድ ለዩክሬን እና ለሩሲያ ጦርነት

This browser does not support the audio element.


በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ መሪዎች የልዑካን ቡድን  ወደ ሩሲያ እና ዩክሬን እንደሚጓዝ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ትናንት ማክሰኞ አስታውቀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ  የአፍሪቃ መሪዎችን በሞስኮ እና በኪየቭ ለማስተናገድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ራማፎዛ ከሁለቱ መሪዎች ጋር በተናጠል አደረኩት ባሉት የስልክ ውይይት ማረጋገጣቸውን በደቡብ አፍሪቃ ጉብኝት ከሚያደርጉት የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሲየን  ሉንግ  ጋር በጋራ  በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
«ከሁለቱ መሪዎች ጋር ባደረግኩት ውይይት የአፍሪካ መሪዎችን ለመቀበል እና ይህ ግጭት እንዴት ሊቆም እንደሚችል ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን አሳይቷል።ይህ መሳካት አለመሳካቱ  በሚደረጉት ውይይቶች የሚወሰን ነው።»
ሴኔጋል፣ ኡጋንዳ፣ ግብፅ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ  የሽምግልና ጥረቱ አካል ይሆናሉ ተብሏል።
ሞስኮ እና ኪየቭ ስለ ራማፎሳ መግለጫ ወዲያውኑ አስተያየት አልሰጡም።የአፍሪካ መሪዎች የሰላም ውይይት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ለዩክሬን ግጭት በአሁኑ ወቅት የሰላም ድርድር እንደማይቻል ከገለፁ በኋላ የመጀመሪው ሽምግልና ነው።
ራማፎሳ እንዳሉት ጉቴሬዝ እና የአፍሪካ ህብረት በእቅዱ ዙሪያ ገለጻ ተደርጎላቸው በደስታ ተቀብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና ብሪታንያም ለእቅዱ ጥንቃቄ የተሞላበት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል። በሩሲያና ዩክሬን መካከል ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን የተለያዩ የሽምግልና ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ ቢሆንም አንዳቸውም አልሰመሩም። ያ ከሆነ የአፍሪቃውያኑን ሽምግልና የተለየ እና የተሻለ  የሚያደርገው ምንድነው?የDW የኬፕታወን ዘጋቢ ፕሪቪሌጅ ሙስቫንሄሪ ማብራሪያ አለው።
«የብሪክስ አባል ከሆኑ  አንዳንድ ቻይናን ከመሳሰሉ ሀገሮች ቅርበት አንፃር ያላቸውን  ሀይል ሊጠቀሙበት ይችላሉ ።ቻይና ብሪክስ ውስጥ ዋና ተዋናይ ስትሆን ከአፍሪቃ ጋርም ጠንካራ ግንኙነት አላት። ቻይና ምናልባት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ለሰላም ውይይት እንዲቀመጡ ተፅዕኖ ከማድረግ አንፃር ትልቅ ሚና ልትጫወት ትችላለች። ፕሬዚዳንት ዘሌንስኪ የአፍሪቃን ልዑካን ለመቀበል ያላቸውን ፈቃደኝነት ስንመለከት፤ይህንን የሰላም ስምምነት ለማደራደር ከሚሞክሩት የአፍሪካ መሪዎች አንፃር ተስፋ ያለ ይመስለኛል።» 
ለጉብኝቱ ምንም አይነት የጊዜ ገደብ ያላስቀመጡት የደቡብ አፍሪካው መሪ ፤የሁለቱ ሀገራት ጦርነት "አውዳሚ" በመሆኑ  የአፍሪካ ሀገራትን በእጅጉ የጎዳ መሆኑን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።  
ራማፎዛ ፤የሰላም ውይይቱን ዕቅድ ይፋ ያደረጉት  ባለፈው አመት ኬፕታወን በሚገኘው የባህር ሀይል፤ የሩሲያ መርከቦች የጦር መሳሪያዎችን ጭነዋል በሚል  ከአሜሪካ የቀረበባትን ክስ ካስተባበለች እና ገለልተኛ መሆኗን ከገለፀች ከአንድ ቀን በኋላ ነው። 
ፕሬዚዳንቱ  ከመግለጫው ከአንድ ቀን በፊት በሰጡት ማስተባበያ ሀገራቸው ደቡብ አፍሪካ ምንም እንኳ ጫና እየደረሰባት ቢሆንም፤በዓለም አቀፍ ኃይሎች መካከል በሚደረግ በዚህ መሰሉ ፉክክር ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ ገልፀዋል።ያም ሆኖ አሁንም ድረስ ደቡብ አፍሪቃ ጦርነቱን በተመለከተ ገለልተኛ አይለችም በሚል በአሸማጋይነቷ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አሉ።የዶቼቬለው ፕሪቪሌጅ ሙስቫንሄሪ  ግን ደቡብ አፍሪቃ «ቢሪክስ» የሚባለው ሩሲያ፣ቻይና፣ህንድ እና ብራዚልን ያካተተው የኢኮኖሚ ጥምረት አባል ሀገር መሆኗ ለድድርሩ ሚዛን ይደፋል ባይ ነው ።
«በእርግጥ ክሱ አሁንም ድረስ ምርመራ እየተካሄደበት ነው። በተናገሩት መሰረት ደቡብ አፍሪቃ የጦር መሳሪያዎች ለሩሲያ መሸጥ አለመሸጧን ለማረጋገጥ ምርመራ ላይ ናቸው።,ነገር ግን ደቡብ አፍሪቃ ብሪክስ ውስጥ ዋና ተዋናይ አባል ነች። ስለዚህ እኔ እንደማስበው የአፍሪቃ መሪዎች ደቡብ አፍሪካን እየወሰዱ ያሉት ከሩሲያ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው ተፅዕኖ መፍጠር እና የአፍሪቃ ሀገራትን ድምጽ ማስተላለፍ  እንደሚችል ትልቅ  ተዋናይ ነው።» 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 2022 ዓ/ም ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን እንድታወጣ በሰጠው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምፀ ተአቅቦ ካደረጉ 17 የአፍሪቃ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ነች።

ምስል፦ Mikhail Metzel/ITAR-TASS/IMAGO
ምስል፦ DW/Phoenix
ምስል፦ Wu Hong/AP Images/picture alliance
ምስል፦ Federico Gambarini/AFP/Getty Images

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW