“የአፍሪቃ ቲንከታንክ” ጉባኤ
ሐሙስ፣ መስከረም 29 2018
የአፍሪቃ አገራት መሰብሰብ ከሚገባቸው ግብር እጅግ ዝቅተኛውን የግብር መጠን ብቻ እንደሚሰበስቡ ተገለጠ ፡፡ «የአፍሪቃ ቲንክ ታንክ» በሚል ትናንት ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ውስጥ መካሄድ በጀመረው 11ኛ ጉባኤ ላይ አህጉሪቱ ውስጥ ለሚታየው አነስተኛ መሰረተልማት አንዱ ምክንያት የግብር አሰባሰብ ድክመት መሆኑ ተገልጧል ።
ባራሱ ጃዋራ የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን (ACBF) ቲንክ ታንክ ኔትዎርክ ከፍተኛ ባለሞያ እና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የ11ኛ ጉባኤው አስተባባሪ ናቸው፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የተጀመረው የአፍሪቃ ቲንክ ታንክ ጉባኤ የአህጉሪቱ እያንዳንዱ ጋር ያለውን ጥንካሬ ወደ አንድ መድረክ በማምጣት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቿን ለመቅረፍ እንዲያስችል ዓላማው ልምዶች የሚጋሩበት ነው ይላሉ፡፡
«ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የአፍሪቃ ቲንክታንክ ጉባኤ የዕውቀት አመንጪዎችን ከፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በማገናኘት እንዲወያዩ ሃሳብ እንዲለዋወጥ እናደርጋለን፡፡ በዚህም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ያላቸው ሃብት ማሰባሰብ ላይ የሚገጥማቸው ተግዳሮትን እንዲቀርፉ ማድረግ ነው፡፡ ያንን ወደ ውስጥ ለመመልከት በጥናት ላይ የተመሰረተ ቲንክታንኮችን በውይይት በማዳበር ለፖሊሲ አውጪዎቹ መፍትሄን ማቅረብ ነው” ብለዋልም፡፡
‘ግብር አሰባሰብን ማሳደግ'
በፖሊሲዎች እና ትግበራዎች መካከል ያለውን የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት ውይይት የሚደረግበት የተባለው 11ኛው የአፍሪካ ‘ቲንክ ታንክ' ጉባዔ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ መደረግ ሲጀምር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ አመራር ልዕቀት አካዳሚ ፕሬዝዳት ሳዲቅ አብርሃ፤ "አፍሪካን በብድር ገንዘብ ልንገነባት አይቻለንም፡፡ በአፍሪካ ሀብት ለውት ማምጣት አለብን» ብለዋል ።
አክለውም፦ «ዜጎች በታክስ አከፋፈል እምነት ሲኖራቸው፤ መንግስትም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ግብር የመሰብሰብ ኃላፊነቱን ሲወጣ አገርን የመገንባት ተግባር ያኔ ይከወናል» ብለዋል ። «አውሮፓ በአዋቂዎቻቸው ስልት ኤሲያም በጠንካራ ስነምግባር ያለፉበትን መንገድ በማሰብ አፍሪካውያንም በተናጥል ከመጋፈጥ ይልቅ ከፖለቲሲ ወደ ትግበራ መግባት አለባቸው፡፡ ከገቢ ንግድም ተላቀው ወደ አገር በቀል ምርት መሸጋገርም አለባቸው» ሲሉም ግብር አከፋፈል እና በአገር ውስት ማምረት የአፍሪካ ትልቁ ችግር መሆኑን አመለከቱ፡፡
ግብር ለነጻ ኢኮኖሚ ግንባታ
በመድረኩ የኢትዮጵያን ልምድ በማካፈል በአፍሪካ ሉዓላዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት ፖለሲን ወደ ተግባር መለወጥ በእጅጉ አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስትር ዓናለም ንጉሴ ናቸው፡፡ "ባለፌት ስድስት ዓመታት በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ በግብር አሰባሰብ ላይ ስርነቀል እርምጃ ወስዳለች፡፡ በዚህም የተገኘው ከታክስ ገቢ ከ700 ቢሊየን የላቀ ሃብት ማሰባሰብ መቻሉ ነው፡፡ ባለፈው
በጀት ዓመት የታክስ ገቢያችንን በ80 በመቶ ከፍ አድርገናል፡፡ በዚህ የታክ ገቢውን አገሪቱ ስልታዊ በሆኑ ማህበራዊ አገልግሎት እና የመሰረተልማት ግንባታ ላይ እንዲውል ነው የሚሰራው” ብለዋልም፡፡
ዝቅተኛው የአፍሪካ ግብር አሰባሰብ
በአፍሪካ በአማካይ ልሰበሰብ ከሚገባው የግብር መጠን ከ12-14 በመቶ ብቻ እንደሚሰበሰብ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡ ይህ በማደግ ላይ ባሉ የኤሲያ እና ላቲን አሜሪካ አህጉራት የ22 በመቶ አማካ ስሌት አንጻር እንኳ እጅግ ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን (ACBF) ከፍተኛ ባለሙያ ባራሱ ጃዋራ ለዚህ ብዙ ምክንቶችን ዘርዝረዋል፡፡ "አንደኛው ችግር ግብር ከፋዩ ማን ሊሆን እንደሚገባው እንኳን አናውቅም፡፡ ዳታቤስ በማዘመን ማን ከፍሏል ማን አልከፈለም የሚለው የምንከታተልበት ስልት ደካማ ነው፡፡ ሌላው ግብር ከፋዮቹም ለምን እንደሚከፍሉ አለማወቃቸው ነው፡፡ የመንግስታት ያላቸውን የሚሰበሰብ ግብር አቅም አለማወቅም ሌላው ችግር ነው፡፡ እናም በትክክለኛ ጥናት እነዚያን አቅሞች በእውቀት መለየት ያስፈልጋል” ነው ያሉት፡፡
"ከግብር ወደ ተግባር” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የሚቆየው የአፍሪካ ቲንክ ታንክ ጉባኤው፤ በመረጃ በተደገፈ ትንተና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማምጣትም ያለመ ነው ተብሏል።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሓይ ጫኔ