የአፍሪቃ ኅብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባና የኢትዮጵያ ተቃውሞ
ዓርብ፣ የካቲት 10 2015
የአፍሪቃ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት እየተከናወነ ያለውን ጥረት "ወደ ጎን በመተው ብቻውን ሊያከናውን ያሰበውን ምርመራ ማቆም አለበት" ሲሉ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ። አቶ ደመቀ ይህንን የተናገሩት በ42 ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ ላይ ነው። ኮሚሽኑ የአፍሪካ መር የሰላም ስምምነቱን እና አተገባበሩን ዝቅ እድርጎ ሊመለከት አይገባም ያሉት አቶ ደመቀ ሥራውን ሲያከናውን የአባል ሀገራቱን የግንኙነት መርህ ተከትሎ ሊሆን ይገባል በማለት የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን በተናጠል ምርመራ ለማድረግ መቋቋሙ ኢትዮጵያን እንዳሳዘነም ገልፀዋል። ይህ የአቶ ደመቀ መኮንን ንግግር ሥራቸውን ያስተጓጉላል ብለው እንደማያስቡ የገለፁት የኮሚሽኑ የበላይ ኃላፊ ግን ሥራቸውን ገለልተኛ ሆነው እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል። ነገ እና እሁድ አዲስ አበባ የሚካሄደው 36 ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን በማፋጠን እና በአህጉሩ ደህንነት ዙሪያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከ 51 ሀገሮች የተውጣጡ ልዑካን ቡድኖች በጉባኤው ላይ እንደሚሳተፉ ቀደም ብሎ ተገልጿል። በዚህ መድረክ የህብረቱ አባል ያልሁኑ ሀገራት ማለትም ፖርቱጋል፣ ስፔን፣ ካታር ፣ ኖርዌይ እና ጃፓን በከፍተኛ ባለሥልጣናት ተወክለው የሚሳተፉ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ እና የአውሮጳ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ የሕብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
ከመሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ በተደረገው በ42 ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን "የዚህኛው ዓመት የሥራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ለኢትዮጵያ የተለየ ጠቀሜታ ያለው ነው።" ብለዋል። ደቡብ አፍሪካ ላይ መንግሥታቸው ከሕወሓት ጋር ያደረገውን የሰላም ስምምነት ለመፈፀም በሂደት ላይ መሆናቸው ለዚህ ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። አፍሪካ ሕብረት የመራው የሰላም ጥረት "ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" የሚለውን መርህ በተግባር የተመለከትንበት ነውም ብለዋል። የስምምነቱ አተገባበር በመልካም ሂደት ላይ እንደሆነም ገልፀዋል። የሕብረቱ የሥራ ኃላፊዎች ለዚህ ስኬት ያደረጉት ከፍተኛ ያሉትን ጥረት በአድናቆት ገልፀዋል።
ከሕብረቱ ኃላፊነት ተረክበው የሰላም ስምምነት እንዲከናወን ብርቱ ጥረት ላደረጉትም ምስጋናም አቅርበዋል። ሚኒስትሩ አክለውም ያለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥታቸው በአፍሪካ ኅብረት ላይ ያለውን እምነት ያረጋገጠበት መሆኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ ሲደረግላት ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል ሀገራት ግን ያልተፈለገ የፖለቲካ ጫና ሲደርስባት እንደነበርም አልሸሸጉም። አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት ኢትዮጵያ የሕብረቱን ሥራ አሥፈፃሚ ድጋፍ በሌላ መሰረታዊ ጉዳይ ትሻለች ብለዋል።
"የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ራሱን የቻለ መርማሪ ኮሚሽን አቋቁሟል። ኮሚሽኑ ይህንን አካል ያቋቋመው መንግሥት ከብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማችን ጋራ በጋራ የምርመራ ሥራ ለማከናወን ያቀረበውን ጥሪ ወደ ጎን በመተው ነው። መንግሥት በሰላም ስምምነቱ መሰረት በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን ጥረት እያደረገ ነው። እየተከናወኑ ያሉ የተጠያቂነት እርምጃዎችም አሉ። ኢትዮጵያ መርማሪ ኮሚሽኑ በመቋቋሙ አዝናለች። የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን
የአፍሪካ መር የሰላም ስምምነቱን እና አተገባበሩን ዝቅ እድርጎ ሊመለከት አይገባም። ኮሚሽኑ ሥራውን ሲያከናውን የአባል ሀገራቱን የግንኙነት መርህር ተከትሎ ሊሆን ይገባል። ኮሚሽኑ እየተከናወነ ያለውን ብሔራዊ ጥረት ወደ ኋላ በማለት ብቻውን ሊያከናውን ያሰበውን ምርመራ ማቆም አለበት።"
የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሬሚ ንጎይ ሉምቡ ለዚህ ለአቶ ደመቀ መኮንን ንግግር የአህጉሩን የሰብዓዊ ሁኔታ ዘገባ ሲያቀርቡ ቀጥተኛ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከማውገዛችን በፊት መጀመርያ የምርመራ ሥራውን እናከናውናለን። ይህ የምርመራ ሥራ መረጃው ተጣርቶ እስካልወጣ ድረስ አሁን እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብለን መረጃ ልንሰጥ አንችልም። ምስጢራዊ ሥራ ነው ፣ ሥራውም እየተከናወነ ይገኛል። ገለልተኛ ሆነን ሥራውን በጥብቅ ምስጢር ማከናወናችንን እየቀጠልን ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሰጡትን መግለጫ ማድመጣቸውን የገልፁት ሬሚ ንጎይ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋማቸው ተባባሪ መሆኑን እና ኮሚሽናቸውም ከመንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
"ይህ መግለጫ የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽንን ሥራ ያስተጓጉላል ብየ አላስብም። ከመንግሥት ጋር እንተባበራለን ፣ የአፍሪካ የሰብዓዊ ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ጥያቄዎችን እንከተላለን። ሁለቱም የተቋማችን አጋሮች ናቸው። የራሳችን ሥልጣን፣ የራሳችን ሥራ አለን። ምናልባትም አንድ ቀን ሁለቱ በጋራ ይሰሩ እና በትክክል ትግራይ ላይ የተፈፀመው ምን እንደሆነ ታውቁ ይሆናል። ስለዚህ ቀደም ብየ እንዳልኩት የአፍሪካ መርማሪ ኮሚሽን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች መርማሪ ኮሚሽን እንዳደረገው መግለጫው ሥራውን እንዳያከናውን የሚከለክለው አይሆንም። ማንንም እየከሰስኩ አይደለም። ሥራችንን ግን ገለልተኛ በሆነ መልኩ ነው እየሰራን ያለነው።"
አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስር እንዲኖራት ፣ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን፣ ድህነትና ድርቅ እንዲቀንሱባትና ከአስከፊ ስደትም እንድትላቀቅ በየ አመቱ በመሪዎቹ ቢመከርም ውጤቱ በተቃራኒው ሲሆን ይስተዋላል።
የእርስ በርስ ጤርነት፣ የመንግሥት ግልበጣ፣ ግጭት ስደት፣ ድርቅና ድህነት አህጉረን አሁንም ሊላቀቁ አልቻሉም።
ነገ ቅዳሜ የካቲት 11 እና እሁድ የሚደረገው የመሪዎቹ ጉባኤ በእነዚሁ ጉዳዮች ዙሪያ በዋናነትም ነፃ የንግድ ቀጣናን እንዴት መተግበር እንደሚቻል ይወያያሉ ተብሏል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ