1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡሩንዲ፤ ደቡብ አፍሪቃ እና ጋምቢያ ከአዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ለቀዋል

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 22 2009

የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ለደቡብ አፍሪቃው ጃኮብ ዙማ፤ ለዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ጆሴፍ ካቢላ እና በርካታ የአህጉሪቱ መሪዎች ፈታኝ ነበር። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በአፍሪቃ አገራት ዘንድ ወደ ጎን ተገፍቷል።

Ghana Präsidentschaftswahlen- Nana Akufo-Addo
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Alamba

Fokus Afrika I & II - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

በየጊዜው የሚያሻቅብ ሥራ አጥነት፤ ዝቅተኛ የትምህርት ጥራት፤ ፖለቲካዊ ምሥቅልቅል እና ሙሥና የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን ሥልጣን ሲገዳደሩ ይኸው የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም ሊሰናበት ነው። ደቡብ አፍሪቃ ከአፓርታይድ ሥርዓት መወገድ በኋላ አይታው በማታውቀው ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ውስጥ ትገኛለች። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና የሰራተኛ ማኅበራት ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች ኤኮኖሚያዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ሲወተውቱ በተለይም ገዢውን የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ሲገዳደሩ ከርመዋል። ፓርቲው በበኩሉ በዙማ ደጋፊዎች እና ነቃፊዎች ትንቅንቅ ከሁለት ተከፍሏል። ዙማን ከሥልጣናቸው ለማሰናበት ተቺዎቻቸው ቢሞክሩም የአገሪቱ ምክር ቤት የመተማመኛ ድምፅ አልነፈጋቸውም። የፕሪቶርያው ደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ ሳሞዶዳ ፊኬኒ አገሪቱ ለገባችበት አጣብቂኝ ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

ምስል AP

ጃኮብ ዙማን ምን አልባትም የቀድሞ ባለቤታቸው ድላሚኒ ንኮሳዛና ዙማ ይተኳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ከጃኮብ ዙማ አራት ልጆች ያፈሩት እና የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽንን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ድላሚኒ ዙማ በዚህ ዓመት ሥልጣናቸውን ያስረክባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ ቀርቷል። የአፍሪቃ ኅብረት አባል አገራት ዙማን በሚተካው እጩ ማንነት ላይ ሳይስማሙ ቀርተዋል። መጪው የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ከየትኛው የአኅጉሪቱ ክፍል ሊመጣ ይገባል የሚለው ጉዳይም አነጋጋሪ ሆኗል። 

የደቡብ አፍሪቃ ጎረቤት ዚምባብዌ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ውጥንቅጥም መፍትሔ አልተበጀለትም። ምዕራባውያኑ ልጣቸው የተራሰ ጉድጓዳቸው የተማሰ ሲሉ የሚተቿቸው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ለመቅረብ ቆርጠዋል። የሮበርት ሙጋቤ መንግስት ውጥረቱን ለመፍታት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተጨማሪ ብድር ፍለጋ ሲባዝን ከርሟል። መንግሥት ለሰራተኞቹ እና ለጦሩ አባላት የወር ደሞዝ መክፈል ተስኖት ሲባዝን ይኸ ሰንደቅ አላማ በተሰኘ መፈክር ፓስተር ኢቫን ማዋሪሬ የመሩት ተቃውሞ ተሳታፊዎች ግን ለውጥ እንፈልጋለን ሲሉ ተደምጠዋል። «በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የሥራ እድል የለም። በአገሪቱም ሙስና ተንሰራፍቷል። ከሥራ ገበታችን በመቅረት ለመንግስት ለውጥ እንደምንፈልግ እየተናገርን ነው። ለውጥ እንፈልጋለን። አንዳች መፍትሔ እንሻለን።»

ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Mukwazhi

ባለፉት ዓመታት በሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ ውስጥ የከረመችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ2016 ዓ.ም ብሶባታል። የፕሬዘደንት ጆሴፍ ካቢላ የስልጣን ዘመን ቢያበቃም ተቀናቃኝ ወገኖች መቼ ምርጫ እንደሚካሔድ አልተስማሙም። ሕገ-መንግሥቱ ካቢላ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ እንዲወዳደሩ ባይፈቅድላቸውም በተጠባባቂነት ግን በመንበሩ የመቆየት ፍላጎት እንዳላቸው ጥቆማ ታይቷል። የአገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ ካልተካሔደ ጆሴፍ ካቢላ በተጠባባቂነት ከአባታቸው በወረሱት ፕሬዝዳንታዊ ስልጣን ላይ ይቆያሉ። በጀርመን እና አፍሪቃ ተቋም ዋና ጸሐፊ እና የኮንጎ አጥኚው ኢንጎ ባዶሬክ እንደሚሉት ጆሴፍ ካቢላ እንደ ሌሎች የአኅጉሪቱ መሪዎች ሁሉ የተጣለባቸውን ተስፋ በልተዋል።

« ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ እና መንግሥታቸው የኮንጎ ሕዝብ እና የውጭው ዓለም ከነርሱ የጠበቀውን ተግባር ባለማሟላታቸው ብዙ ሰዎች ቅር የተሰኙ ይመስለኛል። ልክ እንደ ብዙዎቹ አፍሪቃውያን ርዕሳነ ብሔራት ካለፉት ዓመታት ወዲህ ይበልጡን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በመከተል ተቃዋሚዎችን እና የመገናኛ ብዙኃንን ጨቁነዋል። »

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቀውስ የቀሰቀሰው ተቃውሞ የበርካታ ዜጎችን ህይወት ነጥቋል። የአገሪቱ የጸጥታ እና የፍትኅ ተቋማት ግን ኹከት እና ግድያውን ለማስቆምም ሆነ ለመመርመር የሚያስችል ገለልተኝነት የላቸው እየተባሉ ይተቻሉ። በጥቅምት ወር ወደ አገሪቱ ብቅ ብለው የነበሩት የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ዋና አቃቢት-ሕግ ፋቱ ቤንሶዳ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብለው ነበር። አቃቢት-ሕጓ በአገሪቱ የሚፈጸሙት ወንጀሎች በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት ሊያስከስስ እንደሚችል እና ምርመራ ከጎርጎሮሳዊው 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ምርመራ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጠዋል።

ይኸንን ፕሬዘደንት ጆሴፍ ካቢላም ሆኑ የጦር ሹማምንቶቻቸው አይፈልጉትም። ካቢላም ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪቃ አገራት መሪዎች ፍርድ ቤቱ እኛን ለይቶ ያሳድዳል ብለው ያማርራሉ። ማማረር ብቻም አይደለም። ቡሩንዲ፤ ደቡብ አፍሪቃ እና ጋምቢያ አባልነታቸውን ሰርዘዋል። ሌሎች የፍርድ ቤቱ አባል አፍሪቃዊ አገራትም ዳር ዳር እያሉ ነው። የፍርድ ቤቱን መመሥረቻ ሰነድ 124 ሐገራት ቢፈርሙም በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሩሲያና ቻይና ግን አልፈረሙም። ዓለም አቀፍ ሥምምነት የተፈረመለት ዓለም አቀፍ ኃላፊነትም የተጣለበት የዘ-ሔግ ፍርድ ቤት አፍሪቃውያንን ለይቶ አሳዷል አላሳደደም የሚለው ክርክር ግን እንደ ተሟጋቾቹ አቋም የተለያየ ነው። ነገር ግን የአፍሪቃዉያንን ያክል አባላት የሌሉት ፍርድ ቤት እስካሁን ከአፍሪቃዉያን ዉጪ የከሰሰ፤ ያሳሰረ ወይም ያስፈረደበት አለመኖሩ እውነታ ነው። በ 1990ዎቹ ማብቂያ የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ የዳኘዉ የተባበሩት መንግሥታት ፍርድ ቤት ከፍተኛ አቃቤ ሕግ የነበሩት ዶክተር ያቆብ ኃይለማርያም ግን የአፍሪቃውያኑን ትችት አይቀበሉትም። ፍርድ ቤቱ ከአፍሪቃውያኑ ጋር ያለው ግንኙነት ቢሻክርም  በአህመድ አል-ማሐዲ ላይ ታሪካዊ የተሰኘ ውሳኔ አሳልፏል። ጢማሙ አህመድ አል-ማሐዲ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስ እና ባሕል ድርጅት በቅርስነት የተመዘገቡትን የማሊ ቅርሶችን በማውደም ተጠያቂ ነው የተባለው አንሳር ዲን የተባለ የቱዓረግ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አባል ነበሩ። 
ታጣቂዎቹ ካወደሟቸው ታሪካዊ ቅርሶች መካከል በቲምቡክቱ ከተማ የሚገኘው የሲዲ ያሃያ መስጂድ መስከረም 19 ቀን እንደገና ተከፍቷል። መስጂዱ ከስድስት ዓመታት በፊት በእስላማዊ ታጣቂዎች ድምጥማጡ ጠፍቶ ነበር። ለእድሳት አምስት ዓመታት የወሰደው የሲዲ ያሕያ መድጂድ በ15ኛው መ.ክ.ዘ. የተገነባ ነበር። ማስጂዱን ያወደመው የቱዓረግ አንሳር ዲን ታጣቂ ቡድን ማሊን እስከ አስቸኳይ አዋጅ ካደረሷት አምስት ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው። ታጣቂ ቡድኖቹ በማሊ በተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ፈፅመዋል። ሰላም አስከባሪው በማሊ ከተሰማራበት የጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከ100 በላይ ወታደሮቹ ተገድለዋል። ማሊን በሁለት እግሯ ለማቆም የምዕራብ አፍሪቃ አገራት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ጀርመንን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዛሬም ድረስ እየተረባረበ ነው። 
ኢትዮጵያን ጨምሮ በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም  ወደ ሶስት የአፍሪቃ አገራት ያቀኑት የጀርመኗ መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ማሊን ጎብኝተዋል። መራሒተ-መንግስቷ የማሊ ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪቃ መረጋጋት ለአውሮጳ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው ነበር።  ወደ አፍሪቃ የተጓዙት መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል በኒጀር የጦር ሰፈር በማቋቋም ማሊን ጨምሮ ለመላው የሳሕል አካባቢ መረጋጋት ሚና ለመጫወት እቅድ እንዳላቸው የተሰማው በዚሁ ዓመት ነበር። በኒጀር የሚቋቋመው የጦር ሰፈር በጎረቤት ማሊ የተሰማራውን እና የጀርመን ወታደሮችም የተሳተፉበትን የተ.መ.ድ. ሰላም አስከባሪ ኃይል የመደገፍ ሚና እንደሚጫወት በጀርመናውያኑ የአድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ፣ ከሰሀራ በስተደቡብ ያሉ ሀገራት መልካም አስተዳደርን እና ፀጥታ ጉዳይ ተመልካች ኦዝዋልድ ፓዶኑ ተናግረው ነበር።
«በሳህል አካባቢ የጀርመን ወታደራዊ ትሳትፎ የማጠናከሩ ድርጊት ጀርመን በአፍሪቃ ያላትን አቋም በማሳደጉ ረገድ ትልቅ መሻሻል ነው። ጀርመን በአፍሪቃ ይዛው የቆየችው አቋም ያን ያህል የጎላ አይደለም። ይሁንና። ጀርመን በአውሮጳ ጠንካራ የኤኮኖሚ ኃያል መንግሥት ብቻ ሳትሆን፣ ወደፊት በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መንበር የመያዝ ዓላማም እንዳላት ይታወቃል። በዚህም የተነሳ ጀርመን በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ፣ በተለይ የፀጥታ ጥያቄዎች ዋነኛ ቦታ በያዙባት አፍሪቃን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሚና መጫወት መቻል ይኖርባታል። »
ከጎርጎሮሳዊው መስከረም 10 ቀን ጀምሮ የሶማሊያ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አራት ጊዜ ተራዝሟል።  ይኸ አሁንም በአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ጥበቃ እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ የቆመችው አገር ጎዶሎ የምርጫ ሒደት ነፀብራቅ ነው ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ። ነገር ግን ቢያንስ ከሳምንታት ውስብስብ የድምፅ አሰጣጥ በኋላ ሶማሊያ የመረጠቻቸው የምክር ቤት አባላት ቃለ-መኃላ ፈፅመዋል። የድምፅ አሰጣጡ በርካታ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ወደ አምሳ ዓመታት በሚጠጋው የሶማሊያ ታሪክ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ነበር ተብሏል። በጎሳዎች መካከል በተቀሰቀሱ ውዝግቦች፤ ውንጀላዎች እና ተቋማዊ ፈተናዎች ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በተደጋጋሚ ተራዝሟል። የዓለም አቀፍ ጉዳዮች የጥናት ተቋም በሆነው ቻታም ሀውስ የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አህመድ ሱሌይማን ምርጫው ጊዜ መውሰዱ አስገራሚ አልሆነባቸውም።  “የእዚህን ምርጫ ደረጃዎች ከተመለከትህ፣ የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤት መቀመጫዎች ማሟላት ላይ ያሉ መጓተቶች፣ ጥያቄ የተነሳባቸው ለውድድር እንደገና የቀረቡ መቀመጫዎች ጉዳይ እና ፕሬዝዳንት ለመምረጥ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ምንድናቸው ለሚሉት መፍትሄ መስጠት ጊዜ መውሰዱ አይቀርም” 

ምስል Getty Images/S. Maturen
ምስል Reuters/M.Kappeler
ምስል picture-alliance/dpa/P.Post

የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲራዘም የጋምቢያ ደግሞ አስደናቂ ውጣ ውረዶች አስተናግዷል። ትንሺቷን ምዕራባዊት አገር ከፖለቲካ ምሥቅልቅል ውስጥ እንዳይጥላት ያሰጋው የምርጫ ውጤት ውዝግብ አሁንም መፍትሔ አልተበጀለትም። ያሕያ ጃሜሕ በምርጫው ማግሥት ሽንፈታቸውን በጸጋ ሲቀበሉ ዓለም ሁሉ ገርሞት ምናልባት አፍሪቃ ቀን እየወጣላት ይሆን? ብሎ ነበር። «ከዚሕ በፊትም ግልፅ አድርጌያለሁ።ምርጫ ከጀመርን ጀምሮ ያለናንተ ይሁንታ ይሕቺን ሐገር አልገዛም። ምርጫዉን አላጭበረብርም፤ ዉጤቱን ለመቀበል አላንገራግርምም። ምክንያቱም ይሕ ከመላዉ ዓለም በጣም ግልፅና የማይጭበረበር ምርጫ ነዉ። ሥርዓታችን ልዩ ነዉ። ምርጫ እንዲደረግ የወሰነዉም የሚመራችሁን ሰዉ ማንነት የምትወስኑት እናንት የጋምቢያ ሕዝብ በመሆናችሁ ነዉ። ከዚሕ ቀደም ተናግሬያለሁ። ተቃዋሚዬ በአንድ ድምፅ እንኳን ቢበልጠኝ ምርጫዉ ነግልፅ እስከሆነ ድረስ ዉጤቱን እቀበላለሁ።»

ምስል Reuters/C. Garcia Ralins

ይኸ አስደናቂ የጃሜሕ ንግግር ሊታጠፍ የወሰደው እጅጉን ጥቂት ቀናት ብቻ ነው። ጋምቢያውያን ያለፈ ታሪካቸው ከጃሜሕ ጋር አብሮ ያለፈ የተቀየረ መስሏቸው በደስታ ጮቤ ረግጠው ነበር። ግን ሁሉም ነገር እንደ አጀማመሩ ሁሉ ፍፃሜው አላማረም። «ጋምቢያዉያን ሆይ፤ የምርጫዉን ዉጤት ሙሉ በሙሉ እንደማልቀበለዉ አስታዉቃለሁ። በዚሕም ምክንያት ምርጫዉን ከነሙሉ ሒደቱ ዉቅድቅ አድርጌዋለሁ። ዳግም ምርጫ ይደረጋል። ምክንያቱም ጋምቢያዊዉ በሙሉ ድምፅ መስጠቱን ማረጋገጥ አፈልጋለሁ።» የጋምቢያ መፃኢ እጣ ፈንታ አሁንም ሥጋት ላይ ነው። የአካባቢው አገራት ያሕያ ጃሜሕ ሥልጣናቸውን በሰላም ካላስረከቡ የኃይል እርምጃን ጨምሮ አስፈላጊውን ጫና እንደሚያሳድሩ አስጠንቅቀዋል።  

እዚያው ምዕራብ አፍሪቃ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ያካሔደችው ጋና ግን ዛሬም የአፍሪቃ ዴሞክራሲን ከፊት ሆና እንደምትመራ በድጋሚ አረጋግጣለች። የጋና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ እና አኩፎ አዶ በሶስተኛ ሙከራቸው ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። ፕሬዝዳንት ጆን ማሕማ በበኩላቸው «ለአገራችን ፖለቲካዊ፤ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ እድገት የበኩሌን ተወጥቻለሁ። ከዚህ የበለጠ እድል ቢሰጠኝ ደስተኛ በሆንኩ ነበር። ቢሆንም የጋናውያንን ፍላጎት አከብራለሁ።» ሲሉ ሽንፈታቸውን በጸጋ መቀበላቸውን አረጋግጠዋል። 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW