1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምን ያህሉ ወጣቶች በግብርና መስክ ተሰማርተው ለመስራት አስበው ይሆን?

ዓርብ፣ ሐምሌ 16 2013

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የዝናብ ወቅት ነው። በዛ ላይ ደግሞ  ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች እረፍት ላይ ናቸው። ታድያ ምን ያህሉ ወጣቶች በግብርና መስክ ተሰማርተው ለመስራት አስበው ይሆን? አስተያየታቸውን ያላከሉን አሉ። ከዚህም በተጨማሪ በግብርና የተሰማሩ የሌሎች አፍሪቃውያን ወጣቶች ተሞክሮን በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንቃኛለን።

The 77 Percent I Hikimatu Kediri
ምስል Thomas Klein/DW

ምን ያህሉ ወጣቶች በግብርና መስክ ተሰማርተው ለመስራት አስበው ይሆን?

This browser does not support the audio element.

አፍሪቃ ውስጥ 20% የሚሆነው ህዝብ ዕድሜው ከ 15 እስከ 24 ዓመት ነው። አብዛኞቹም የሚኖሩት በገጠራማ አካባቢዎች ነው ። ለመሆኑ ወጣቶች ለግብርና ምን አይነት አመለካከት አላቸው? በዚህ የስራ መስክ ተሰማርተው ለመስራትስ ፍላጎት አላቸው?  ዮናስ « አባቴ በዚህ መስክ ይሰራ ስለነበር እኔም በበጎ ፍቃደኝነት እሰራ ነበር » በጣም ትርፋማ ስራ ስለሆነ ወጣቱ ሊበረታታ ይችላል የሚል አስተያየት አለው። ማስተዋል የግብርና ምጣኔ ሃብት (አግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ) የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ናት። « ወደዚህ ፊልድ ስንገባ ደስተኛ አልነበርም ነበር። ስለ ስራው እና ስለምናገኘው ጥቅም መጀመሪያ ላይ በደንብ ቢገለፅልን ጥሩ ይመስለኛል።» ደረጀ ጎዳም አካባቢ ነው የሚኖረው» ለገጠሩ ቅርብ ስለሆንኩኝ እንደዚህ አይነት ስለማይ አስባለሁ። ከሰራሁ ግን በዘመናዊ መንገድ ነው መስራት የምፈልገው» ይላል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይም የ ዶይቸ ቬለ 77 ከመቶው ዝግጅት የሌሎች አፍሪቃውያን ወጣቶች አስተያየትን አሰባስቦ ነበር። የካሜሮን ወጣቶች እንዲህ ይላሉ « እኔ አሁን በግብርናው መስክ ተሰማርቻለሁ። ምክንያቱም በእኛ አካባቢ ያሉ ብዙ ሰዎች ወደግብርናው አዘንብለዋል። በፊት ግብርና ብዙም በህይወት ላልተሳካላቸው እና በገጠራማው አካባባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ነው የሚል ዕምነት ነበር። » « ግብርና መስራት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም በጣም ትርፋማ ያደርጋል። በዛ ላይ እራሴ የማመርተው ነገር ከገበያ ከምንገዛው ይልቅ አርኪ ነው» «  አዎ! ከተመረኩኝ በኋላ በግብርናው መስክ ተሰማርቼ መስራት እፈልጋለሁ። ይህ ደግሞ ግብርናን ስለምወድ ነው። እንዲህ ስል ለግል ፍጆታ ብቻ የሚውል አይደለም። ብዙ ገቢ ያስገኛል። በርካታ ሀገሮች ህዝባቸውን የሚመግቡት ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ በግብርና ላይ ብሰራ ወደ ውጪ ሀገራትም መላክ እችላለሁ።» 
የጥቂት ካሜሮናውያን ወጣቶች አስተያየት ይህን ይመስላል።  ቀጥለን ደግሞ ወደ ጋና መዲና አክራ እናመራለን።  አዲዴላፖ፤ ለግል ፍጆታ የሚውል አምራች ገበሬ ናት። እንዴት ወደ ግብርና እንደገባች ስትናገር « የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያገኘሁት በግብርና ነው። ከዛ ደግሞ ለድህረ ምረቃ ያተኮርኩት በግብርና ንግድ ላይ ነበር። ከዛ ትምህርቱ ካለሽ ለምን ወደ ተግባር አትቀይሪውም ብዬ ተነሳሳሁ። የግብርና ጥሩው ጎኑ ትርፋማ ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ፈተናዎች አሉት።» 
ሌላው ጋናዊ ገበሬ  ፊሊክስ ይባላል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ይሰራል። « ወደ ግብርና የገባሁት አስፈላጊነቱን ተረድቼ ነው። ከትምህርት ቤት በኋላ የሚስማማኝን ስራ እየፈለኩ ሳለሁ አንድ ፣ የኮንትራት ግብርና ስራ አገኘው። እና የድሮ ገበሬዎች ስለ አዲሶቹ የቴክኖሎጂ ስልቶች እውቀቱ የላቸውም። ከዛ እኔ ደግሞ ትንሽም ቢሆን የቴክኖሎጂው እውቀት አለኝ ፣ ብዙ ሰዎችም የሚሳተፉበት መስክ አይደለም ስለዚህ ስኬታማ እሆናለሁ የሚል እምነት አደረብኝ። 
ፊሊክስ የአፈሩን ርጥበት የሚመዘግብ መሣሪያ ይጠቀማል። ይህም መሣሪያ እንደየአስፈላጊነቱ ውኃ ማግኘት ያለባቸውን ቦታዎች ይጠቁመዋል። ከዚህም በተጨማሪ  ድሮንስ የሚባሉትን ሰው አልባ በራሪ መሳሪያዎች መድሀኒት ለመርጨት ይጠቀማል። ይህም ስራውን በእጅጉ አቃሎለታል። « ይህም 10 ሄክታር መሬትን በአንድ ሰዓት ይጨርሳል። ምክንያቱም 16 ሊትር የሚይዝ ድሮውን ነው የምንጠቀመው። ይህም በአንድ ሰዓት ውስጥ ትዕዛዙን ይጨርሳል። ይህን አይነት ቴክኖሎጂ የማይጠቀሙት ግን 1 በመቶ ያህሉ በቀን አንድ ሄክታር መስራት ቢችሉ ነው። » 
ፊሊክስ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የሚሰራበት የግብርና መስክ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም« በር ከፋች ሆኖዋል» ይላል። 
ጊውበርት ገና ተማሪ ነው። በግብርናው መስክ ስለመሰማራት ከዚህ ቀደም አስቦበት አያውቅም። አሁን ግን አመለካከቱ ተቀይሯል። « ስለ እርሻ ስናወራ ባህላዊ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚመረተው ነው አዕምሮዋችን ውስጥ የሚመጣው። ነገር ግን አዲስ ጥናቶችን እና የቴክኖሎጂ መንገዶችን የምንጠቀም ከሆነ ሰዎችን ሊስብ ይችላል። ምክንያቱም በዛሬ ጊዜ ማንም በሬዎችን እና ባህላዊ መሳሪያዎችን ተጠቅሞ መስራት የሚፈልግ የለም።» ቻርሲ፤ የጋና ገበሬዎችን የሚያበረታታ ተቋም ሰራተኛ ናቸው። ጋና ውስጥ በርካታ ወጣቶች በግብርናው መስክ እንዳልተሳተፉ ነው የሚናገሩት። « ግብርና የተመረቁ ተማሪዎች እንኳን ኃላ ላይ በመስኩ ተሰማርተው መስራት አይፈልጉም። ይህም በዘርፉ በሚያዩት ፈተናዎች የተነሳ ነው። ከእነዚህም ፈተናዎች አንዱ የከባቢ አየር ሁኔታው ተቀይሯል። ቀደም ሲል ለስድስት ወራት እንጠቀመው የነበረው የዝናብ ውኃ ለምሳሌ አሁን ለሶስት እና አራት ወራት ዘንቦ ያበቃል።» 
ታድያ ወጣቶች ይበልጥ በግብርናው መስክ እንዲሰማሩ እንዴት መገፋፋት ይቻላል? ከመንግሥትስ ምን ይጠበቃል? በቅድሚያ በርካታ ወጣቶች ወደ ግብርና ወደተሰማሩባት ዝምባዌ እንውሰዳችሁ። 6000 የሚሆኑ ወጣት ገበሬዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ተሰባስበው ተሞክሯቸውን ይለዋወጣሉ። አንዳንዶቹ ገበሬዎች እንደውም የፖለቲካ ሳይንስ፤ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚክስ ተማሪዎች ናቸው። የ26 ዓመቱ ቴሬንስ ዛሬ በግብርናው መስክ ተሰማርቶ ዶሮ ያረባል።  ቴሬንስ በሳምንት በአማካይ 400 የአሜሪካን ዶላር ያገኛል። የፖለቲካ ሳይንስ ያጠናው ቴሬንስ ሌሎች ልክ እንደሱ ሌላ ሙያ ተምረው ስራ ያላገኙ ወጣት ዝምባብዌያውያን ገበሬ እንዲሆኑ ያበረታታል። « የግብርና ስራ ለኔ  አሁን ያለሁበት ቦታ ለመድረስ ብዙ ማሰብ የጠየቀኝ ሙያ ነው። ወጣት ሲኮን ጠንካራ የሆነ ነገር ፣ ጠንካራ የፋይናይስ መሠረትም ያስፈልጋል።» 
በተለይ ቴክኖሎጂ በርካታ ወጣቶችን ለግብርና እንዳነቃቃቸው ይናገራሉ። ሴት ወጣት ዝምባብዌያውያን ወደዚህ የስራ መስክ የገፋፋቸው ደግሞ ስራ አጥነት ነው። ፊሊፕ ኤዌራ  የዝምባዌ ወጣት ገበሬዎች ክበብ ኃላፊ ናቸው ። ወጣቱ በግብር እንዲሰማራ ይመክራሉ ለዚህም  ምክንያት አላቸው።« ወጣቱ ዘንድ ትልቅ ኃይል እና ፍላጎት አለ ። ባለፉት ጥቂት አመታት በርካታ በተለያየ ሙያ የተመረቁ ወጣቶች ኃይላቸውን በግብርና ላይ ቢያውሉ ብዙ ትርፋማ እንደሚሆኑ ስናሰለጥናቸው ነበር።  » 
ወጣቶች በራስ ተነሳሽነት ይህንን ካደረጉ በመንግሥት ደረጃስ ምን ሊሰራ ይገባል? ጋናዊቷ አዲዴላፖ መፍትሄ የምትለው አለ። « ወጣቶችን ወደ ግብርና ማበረታታት ለአህጉራችን ለውጥ የሚያመጣ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በርካታ ገጠራማ አካባቢዎች አሉን ፤ የወጣቱም ቁጥር ከፍተኛ ነው። እነዚህን ነገሮች አጣምረን ትልቅ ነገር መስራት እንችላለን። » 
ከዚህም በተጨማሪ አዲዴላፖ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም  ግብርናን ማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አላት። እሷ እንደምትለው ስለ ግብርና ስናወራ በበሬ የሚያርስን ሰው ምስል ከሆነ ሁሌ የምንጠቀመው ወጣቱን በዚህ ልናበረታታው አንችልም።  ሌሎች ጋናውያን ገበሬዎችስ ከመንግሥት ምን ይጠብቃሉ? « በርካታ መንግሥታት በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት ላይ የማይውል ብዙ መሬት አላቸው ። ግብርና ገቢን ለመጨመር የሚረዳ ዋንኛ መንገድ ስለሆነ ወጣቶች ሊሳተፉበት ይገባል የሚል ዕምነት አለን» « መንግሥት በግብርናው መስክ ሊሰራ ገንዘብ ሊመድብ ይገባል። ገንዘቡ አላቸው። ማሽን፣ አዲስ ቴክኖሎጂ የመሳሰሉትን። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ግብርናን ሳቢ እንዲሆን ያደርጋሉ። » 
ኢትዮጵያውያን ወጣቶችስ በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ደረጀ የግንባታ ስራ ባለሙያ ነው። እሱ በሚኖርበት ጎጃም አካባቢ ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ የሚሰማሩበት ሁኔታ እንደተፈጠረ እና መበረታታት እንዳለበት ይናገራል።  ማስተዋል፤ ምንም እንኳን ትምህርቱ የመጀመሪያ ምርጫዋ ባይሆንም ወደፊት በዚሁ መስክ ተሰማርታ እንደምትሰራ ታስባለች። ዮናስ ከዚህ ቀደም፤ለአራት ዓመት ያህል ቲማቲም እና ሽንኩርት ያመርት ነበር። አሁን ደግሞ  ከጓደኛው ጋር ከብት ለማርባት በዝግጅት ላይ ነው።  

ልደት አበበ 

ምስል DW
ምስል DW

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW