የአፍሪቃ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን
ሐሙስ፣ የካቲት 23 2015
በአፍሪቃ በምግብ እጦት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ለመቀነስ ያለመ የተባለው ዕለቱን አስመልክቶ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዶ በዋለው ስብሰባ የአፍሪቃ አገራት ተወካዮች፣ የህብረቱ ኮሚሽን እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ታዳሚ ሆነውበታል፡፡
በመድረኩም ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ደረጃ በጎ እምርታን ያሳየ ተግባር ብትከውንም በመላ ሀገሪቱ ግን የተንሰራፋው ግጭት፣ ድርቅ እና የምግብ አቅርቦት እጥረት የት/ቤት ምግባ ተደራሽ እንዳይሆን በማድረጉ በርካታ ትምህርት ቤት መሆን የሚገባቸው ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ናቸው ተብሏል፡፡
ተማሪ በእምነት ሞገስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዳግማዊ ሚኒሊክ 2ና ደረጃ ተማሪ ናት፡፡ ምንም እንኳ በእምነት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በመሆኗ አሁን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ለመላው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይሰጣል በተባለው የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ባትሆንም በታናናሾቿ በማየቷ ጥቅሙ የላቀ ነው ትላለች፡፡ “ምንም እንኳ እኔ የመርሃግብሩ ተጠቃሚ ባልሆንም አንደኛ ደረጃ የሚማሩ ታናሾቼ ምንም ስለሚቋጠር ምግብ ሳያስቡ ወላጆችም ያለምንም ሰቀቀን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ትላለች፡፡
ሌላዋ በዚሁ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የምትከታተለው ታዳጊ ኃይማኖት ቶሎሳ ደግሞ የምገባ መርኃግብር ጥቅም ስታስረዳ “ትኩረታችንን ትምህርት ላይ ብቻ እንድናደርግ አግዞናል” ትላለች፡፡
በአፍሪቃ ለስምንተኛ ጊዜ እየተከበረ ነው የተባለው የትምህርት ቤት ምገባ ዓለማውን የትምህርት ጥራት የሚረጋገጥበትና የተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ የሚገታበት ስልት መቀየስ ላይ አተኩሮ በዛሬው እለት አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪቃ ህብረት ውስጥ ተካሂዶ ውሏል፡፡ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዛሬው ስብሰባ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ይሰጣል የተባለው የት/ቤት ምገባ መርሃግብር በበጎ ምሳሌነትም ተነስቷል፡፡ የመዲናዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግርም ባሁን ወቅት ለ700 ሺህ ተማሪዎች በያመቱ 4.6 ቢሊየን ብር እየተበጀተ አገልግሎቱ ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
“የአፍሪቃ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በአህጉሪቱ ሀገር በቀል የትምህርት ቤቶች ምገባ እንዲኖር የፖለቲካ ድጋፍ ትኩረት እንዲሰጠውም በማሰብ በየዓመቱ የሚካሄድ ነው፡፡ የከተማችን የትምህርት ቤት ምገባ ተማሪዎች በትምህርት ቤት እንዳይራቡ በማድረጉ በዓለማቀፍ ደረጃም እውቅና ያገኘ ነው፡፡ መርሃግብሩን የጀመርነው በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆን ዓላማውም የምግብ እጥረት ችግርን በመቅረፍ የትምህርት ጥራትን ማሳደግ ነው፡፡ ይህ መርሃግብር የተመጣጠነና ጤናማ ምግብን ለታዳጊዎች ማቅረብ ለተሳናቸውም ወላጆች እፎይታን የፈጠረ ነው፡፡ ለተማሪዎች ምግባ በያመቱ 4.6 ቢሊየን ብር እየመደብን ለተማሪዎች ምግብ እያቀረብን እንገኛለን፡፡ ፕሮግራሙን ከአራት ዓመታት በፊት ስንጀምር 17 ሺህ ገደማ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን ተደራሽ በማድረግ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን በስፋት ተለምዶ በከተማዋ ባሉ ሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 700 ሺህ ተማሪዎችን ተደራሽ ሲያደርግ ለ16 ሺህ እናቶችም የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡”
ከንቲባዋ አክለውም የምገባ መርሃግብሩ ውጤት ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ፤ “እስካሁን የተገበርነው አገር በቀል የተማሪዎች ምገባ የተማሪዎች ተሳትፎን በማነቃቃት የተማሪዎች ከትምህርት ቤት የመቅረት ችግርን በእጅጉ ቀርፏል፡፡ ይህ ስራችንም አዲስ አበባ ከ133 ከተሞች ጋር ተወዳድራ በምግብ አቅርቦት ዘርፍ የሚላን-ፓክት የ2022 አሸናፊ እንድትሆን አስችሎአታል፡፡ ይህ ደግሞ በሰው ተኮር ፖሊሲ ቁርጠኛ ለመሆናች አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በታዳጊዎች ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ነገን መገንባት በመሆኑ ለግልና መንግስታዊ ተቋማትም ይህ ተግባር ይበረታታ እንላለን፡፡ ሌሎች አገራትና ከተሞችም ይህንኑን ልምድ በመውሰድ ለሁሉም ብሩህ የነገ ተስፋን እንዲገነቡ እንመክራለን፡፡”
በኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለትምህርት ጥራት አደጋ ደቅኖ መቆየቱን በማንሳት፤ ችግሮቹን ለመቅረፍ የት/ቤት ምገባን እንደ ስልት በፖሊሲ ደረጃ መቀረጹን ያወሱት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው፡፡ “ከፍተኛ ጥራት ያለውን ትምህርት ማቅረብና በሰው ሃይል ላይ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ጠንካራ አህጉር መፍጠር ተግዳሮቶቻችንን ለመፍታት ይረዳናል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ጥራት ያለው ትምህርት ለማቅረብ የማይናቅ ጥረት አድርጋለች፡፡ ነገር ግን በርካታ ታዳጊዎች አሁንም ድረስ በግጭት፣ ድርቅ እና በምግብ ዋስትና እጥረት ከትምህርት ቤት ውጪ ናቸው፡፡ ይህ እውነታ ዜጎች ከአገራቸው በፍትሃዊነት ሊያገኙ የሚገባቸውንም አሳጥቶአቸዋል፡፡ እናም ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ የተሻለ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ አይነተኛ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አርሶ አደሮች፣ እናቶች እና ህጻናትን ብሎም በሰንሰለቱ የሚጠቃለሉትን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን ቀጣይነት ያለውን የትምህርት ቤት ምገባ እውን ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር በአስር ዓመት ፍኖተ-ካርታውም ጭምር በፖሊሲ ደረጃ ቀርፆ እየሰራበት ይገኛል፡፡ ይህ ፖሊሲ በ2030 በአንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤቶች ሁሉም ተማሪዎችን ቢያንስ በቀን አንዴ የመመገብ ውጥን የያዘ ነው፡፡”
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 5.3 ሚሊየን ተማሪዎች የት/ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያከሉት ፕ/ሮ ብርሃኑ የአህጉሪቱ ህብረት ለውጤታማነቱ ልምድ እንዲለዋወጡም ጠይቀዋል፡፡“ዓለማቀፍ ልምድም እንደሚያሳየው ስኬታማ የት/ቤት ምገባ የሚመሰረተው ለአከባቢያዊ አቅርቦት ግብርናን በማጠናከር ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እና አጋሮቹ ዛሬ ላይ ለ5.3 ሚሊዮን ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ምግብ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ምግብ የሚቀርበው በአከባቢው ባሉ የአርሶአደሮች ህብረት ስራ ማህበራት በመሆኑ በርካታ ሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል ተከፍቶላቸዋል፡፡ በዚህ ላይ በአፍሪቃ ህብረት አባላት መካከል ልምድ ልውውጥ ማድረግ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም የኢትዮጵያ መንግስት ያምናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም አጋሮቻችን ጋር ለመስራት ዝግጁነታችንን ለማረጋገትጥ እንወዳለን” ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፡፡
ስዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሰ
ነጋሽ መሐመድ