1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2015

የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው። በዓለም የሚታየውን የአየር ንብረት መዘዝ እንዳስከተለ ለሚነገርለት የሙቀት አማቂ ጋዝ ክምችት ያላት አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ የሆነው አፍሪቃ በድርቅ እና በጎርፍ ክፉኛ እየተጎዳች፤ ሕዝቦቿም ለሞት ለመፈናቀል ብሎም ለስደት መዳረጋቸው እያነጋገረ ነው።

ፎቶ፤ የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ
ከትናንት ጀምሮ በኬንያ በዋና ከተማ ናይሮቢ ላይ የተጀመረው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ለዓለም አቀፉ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP በመባል ለሚታወቀው መዘጋጃ በክፍለ ዓለም ደረጃ ከሚደረገው አንዱ ጉባኤ ነው። ፎቶ፤ የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ

This browser does not support the audio element.

የያዝነው ሳምንት የአፍሪቃ የአየር ንብረት ሳምንት ተብሏል። ከትናንት ጀምሮ በኬንያ በዋና ከተማ ናይሮቢ ላይ የተጀመረው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ለዓለም አቀፉ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP በመባል ለሚታወቀው መዘጋጃ በክፍለ ዓለም ደረጃ ከሚደረገው አንዱ ጉባኤ ነው። ለአምስት ቀናት የሚዘልቀው የናይሮቢው ጉባኤ ለከባቢ አየር ብክለቱ ድርሻው ጥቂት ሆኖ ሳለ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች የተጋለጠውን የክፍለ ዓለሙን  1,3 ቢሊየን ሕዝብ ከባሰ ጉዳት ለመከላከል መሪዎቹ ጠንካራ ድምጽ የሚያሰሙበት ነው ተብሎ ተገምቷል። ጉባኤው በዋናነት ስለሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ የሚነጋገር ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአየር ንብለት ለውጥን መዘዝ በመጋፈጥ ላይ የምትገኘው አፍሪቃ ቀውሱን ተቋቁማ ስለምትዘልቅበት ስልትም እንደሚወያይ ይጠበቃል። በርካታ የሃገራት መሪዎች በጉባኤው የሚሳተፉ ሲሆን የተለያዩ በአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ተቋማትና ሲቪል ማኅበራት እንዲሁም የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችም በብዛት ተገኝተዋል። በጉባኤው በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት አንዱ የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም የአፍሪቃ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ከበደ፤ እንደሚሉት የመጀመሪያው ቀን ውሎ በብዙዎች ቀን የተሻለ ግንዛቤን ማሳደር የቻለ ነው። ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ድምጻቸውን ያሰሙበት፤ ሲቪክ ማኅበረሰቦች ጠንካራ መልእክቶች ያስተላፉበት፤ እንዲሁም የአካባቢ ማኅበረሰቦች ተወካዮች በጥሩ መልኩ ሃሳባቸውን የገለጹበት እንደነበርም ገልጸውልናል።

በኢንዱስትሪው ያደጉት እና ለከባቢ አየር ብክለቱ ታሪካዊ ተጠያቂዎች የሚባሉት ሃገራት የአፍሪቃ መንግሥታት ያላቸውን አቅም ሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ የሚያስችል ዘርፍ ላይ በማዋል እንዲሠሩ ግፊት እያደረጉ ነው። ጀርመን የኃይል ምንጭዋ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከብክለት የጸዳ ነው ለሚባልላት ኬንያ ዘርፉን ይበልጥ ለማልማት የ65 ሚሊየን ዶላር ብድር ለመስጠት ቃል ገብታለች። የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችም እንዲሁ ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ለሚደረገው የካርቦን ሽያጭ 450 ሚሊየን ዶላር መመደቧን አሳውቃለች። እንዲህ ያለው ተነሳሽነትም እስከጎርጎሪዮሳዊው 2030 ድረስ የአፍሪቃን የካርቦን ሽያጭ በ19 እጥፍ ሊያሳድግ እንደሚችል የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ጉባኤውን በከፈቱበት ንግግር አመላክተዋል።

ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ በጉባኤው ላይ ባሰሙት ንግግር አፍሪቃ በታዳሽ የኃይል ምንጭ አይነቶች ራሷን የምትችል ባለ እምቅ አቅም ባለቤት ነች ነው የሚሉት። ፎቶ ዊልያም ሩቶ የኬንያ ፕሬዝደንት ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

«ያሉት ዕድሎች ተስፋ ሰጪዎች ብቻ ሳይሆኑ መለወጥ የሚችሉ ናቸው። አፍሪቃ የሚያስፈልገንን ኃይል በሙሉ ከታዳሽ የኃይል ምንጭ ማግኘት ትችላለች። ክፍለ ዓለሙ ከነፋስ፣ ከፀሐይ፤ ከመሬት ውስጥ እንፋሎት፤ በዘላቂነት እጽዋት እና ውኃ ኃይል ጋር ተደባልቆ ሙሉ በሙሉ ራሱን ለመቻል አቅም አለው። አፍሪቃ ሌሎች ክፍለ ዓለማት በ2050 የብከለት መጠናቸው ዜሮ የማድረግ ዕቅዳቸውን እንዲያሳኩ የሚያስችል የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ማዕከል መሆን እንችላለን።»

ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ በጉባኤው ላይ ባሰሙት ንግግር አፍሪቃ በታዳሽ የኃይል ምንጭ አይነቶች ራሷን የምትችል ባለ እምቅ አቅም ባለቤት ነች ነው የሚሉት።

«መጠነ ሰፊ የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅም እና የተፈጥሮ ሀብት፤ እንዲሁም የምንጠቀምበት አረንጓዴ ጥሬ ሀብት አለን። በዚኽ አቅምም የዓለምን ኤኮኖሚ ከካርቦን የጸዳ ለማድረግ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማድረግም እንችላለን። በደፈናው የአየር ንብረትን ብቻ ሳይሆን አፍሪቃም ሆነች ዓለም ሊያተኩሩበት የሚገባ፤ አረንጓዴ እድገትን እና ያለውን በርካታ ሚሊየን ዶላር ማፍለቅ የሚችለውን የኤኮኖሚ ዕድልም መመልከት አለብን።»

የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው። ፎቶ የአፍሪቃ አየር ንብረት ጉባኤ ናይሮቢ ኬንያ የመክፈቻ ሥርዓትምስል Shisia Wasilwa/DW

የተመድ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም በዓለም ግሩም የተባለውን 60 በመቶ ከፀሐይ ኃይል የሚያመነጭ አቅም የሚገኘው አፍሪቃ ውስጥ ነው። የዓለም ባንክ በበኩሉ ከፀሐይ ኃይል የትናንሽ ማመንጫዎች ቁጥር አፍሪቃ ውስጥ እየጨመረ መሄዱን ነው ያመለከተው። ለኢንዱስትሪው ግብአት ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን በብዛት ሲጠቀም የኖረውና ኤኮኖሚውንም በዚሁ ላይ ተመርኮዙ ያበለጸገው ምዕራቡ ዓለም በዚህ መዘዝ በመጣው የአየር ብክለት ላለበት ታሪካው ኃላፊነት የብክለት መጠንን ከመቀነስ ጎን ለጎን ለጉዳት ለተዳረጉ አዳጊ ሃገራት የ100 ቢሊየን ዶላር ድጎማ ለመስጠት የገባው ቃል አሁንም ተግባራዊ አለመሆኑ አነጋጋሪ እንደሆነ ነው። የኬንያው ፕሬዝደንት ብቻም አይደሉም ስለታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚናገሩት፤ በተለይም ከካርቦን ንግድ ጋር በማያያዝ ጉዳዩ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል። ለመሆኑ ብዙ የሚወራለት የካርቦን ንግድ በተጨባጭ ለአፍሪቃ የሚኖረው ጠቀሜታ ምን ያህል ነው? ለዓመታት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት አቶ አየለ ከበደ ባለሙያዎች ጥያቄ ያቀርቡበት ጀምረዋል ነው የሚሉት።

የአፍሪቃ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተሳታፊዎች ምንም እንኳን ስለታዳሽ የኃይል ምንጮች ቢነጋገሩም ለድርቅ እና ለጎርፍ የተዳረጉ ተራ ዜጎቻቸው ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ መሆናቸውን ኬንያዊቱ የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቿ ኢካል አንጌሊስ ይናገራሉ።

«ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተጋፈጥናቸው ግዙፍ ችግሮች መካከል ድርቅ ዋነኛው ነው። በዚህም ሰዎች ከብቶቻቸውን ማጣት ብቻ ሳይሆን መኖሪያ ቤታቸውንም እየተው ለመሰደድ፤ ንብረታቸውን ማጣት፤ አልፎ ተርፎም በመሰደዳቸው ምክንያት ማንነት እና ባህላቸውን ሁሉ አጥተዋል።»

ከዚህ በመነሳት ያደረሰባቸው ኤኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊም መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ። በተጨማሪም ሰዎች ውኃ ፍለጋ ረዥም መንገድ ለመጓዝ መገደዳቸውንም ከዋናዎቹ ችግሮች መካከል ያነሳሉ። እንደ እሳቸው ሁሉ ለአፍሪቃውን ገበሬዎች ተፈጥሯዊ የእህል ዘር መጠበቅ የሚቆረቆሩ የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራትም በዚህ ጉባኤ ተገኝተው ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። ኬንያዊቱ ካሪን ንኬሳ የአየር ንብረት ለውጡ በገበሬው እና በአርብቶ አደሩ ላይ ያደረሰውን ዘርፈ ብዙ ችግር እንዲህ ገልጸውልናል።

በርካታ የሃገራት መሪዎች በጉባኤው የሚሳተፉ ሲሆን የተለያዩ በአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ተቋማትና ሲቪል ማኅበራት እንዲሁም የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችም በብዛት ተገኝተዋል። ፎቶ የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

«በቀውስ ውስጥ ነን፤ በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የሚገኙ ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮች አርብቶ አደሮችን ሰዎች ድምጽ መደመጥ አለበት፤ በተለይም በአፍሪቃው ቀንድ ከፍተኛ ረሃብ አስከትሏል፤ ድርቁ የጾታ ጥቃት ሳይቀር አስከትሏል፤  ሰዎች ሥራ አያጡ ነው፤ መሪዎቻችን እጅግም ለዚህ ጉዳይ ቁብ የሰጡት አይመስልም። እንዲህ የምልበት ምክንያት የአካባቢውን የአየር ንብረት ፖሊሲ ስንመለከት፤ 12 ሃገራት ይኽ ይመለከታቸዋል፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር  እንደ ድርቅ፤ ጎርፍ፣ የግጭት ጉዳዮች የመሳሰሉት ማንሳት ይኖርባቸዋል። ግጭት ስል፤ አርብቶ አደሮች አሉ ፤ እነዚህ ሰዎች ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፤ በድርቅ ጊዜ ወደሌላ ቦታ ሲጓዙ ከባድ ግጭቶች ይነሳሉ። ሌላው ቀርቶ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር የሚሄዱ አርብቶ አደሮች አሉ፤ ይኽ ደግሞ ሀገር ከሀገር የሚያላትም ግጭት ነው። ለዚህ ነው የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት እንዲወስዱ ጥሪ የምናቀርበው።»

መሪዎቹ በአዳራሽ ተሰባስበው ሲነጋገሩ በርካቶች አደባባይ ወጥተው «ሕዝባዊ ሰልፍ» አካሂደዋል። ሰልፈኞቹ ከያዟቸው መፈክሮች መካከል «የአፍሪቃን ዘይት እና ጋዝ ለመቀራመት ያለመ የአዲስ ቅኝ አገዛችሁን አቁሙ» የሚለው ይገኝበታል።

 የአየር ንብረት ለውጥ ያባባሰው የዝናብ እጥረት እና ድርቅ፤ እሱን ተከትሎ ከሚከሰተው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው። ጉባኤው እንዲህ ላለው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ያስገኝ ይኾን የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም መልስ አላገኘም። በመጪው ዓመት ኅዳር ወር መገባደኛ ዱባይ ላይ ዓለም አቀፉ ዓመታዊ ጉባኤ COP 28 እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

 ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW