የአፍሪቃ ዴሞክራሲ ጋሬጣዎች
ቅዳሜ፣ መስከረም 14 2015
የዴሞክራሲ ዓይነቶች የተሰኘዉ ተቋም በቅርቡ ይፋ በደረገዉ ጥናት መሠረት አፍሪቃ ዉስጥ ነፃ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በትክክል የተመሰረተባቸዉ ሐገራት ሁለት ብቻ ናቸዉ።ቦትስዋናና ስሼልስ።ሌሎች 13 ሐገራት የምርጫ ዴሞክራሲ ተብለዉ ሲፈረጁ፣የተቀሩት 38ቱ የአፍሪቃ ሐገራት አንድም በተጭበረበረ ምርጫ፣ አለያም በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የያዙ መሪዎችና መንግስታት ይገዛቸዋል።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ፈጥርቀዉ የሚያቀጭጩ አለያም ተስፋዉን ራሱን ጨርሶ የሚያጨናጉሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ።ከብዙዎቹ፣ ብዙ አጥኚዎች የሚስማሙባቸዉ መፈንቅለ መንግስት፣ የተጭበረበረ ወይም ግልፅነት የጎደለዉ ምርጫ፣ ሁሉን ጠቅላይ ወይም አምባገነናዊ አገዛዝ፣ የሥልጣን ክፍፍል አለመኖር፣ ደካማ የፍትሕና የቁጥጥር ሥርዓት ናቸዉ።አፍሪቃዉያን ደግሞ እነዚሕ የዴሞክራሲ ነቀርሶች ሞልቶ ተርፏቸዋል። ከሁለቱ በስተቀር-Varieties of Democracy (V-Dem ሲያጥር) የተሰኘዉ ተቋም እንዳጠናዉ።ቦትስዋናና ሲሼልስ።
የነዚሕን ሐገራት ፖለቲካዊ ሥርዓት ነፃ ዴሞክራሲ ይለዋል አጥኚዉ ተቋም።ነፃ ያለበት ምክንያት ብዙ ነዉ።ምርጫዉ ነፃና ፍትሐዊ ነዉ።የሥልጣን ክፍፍል በግልፅ ይታያል፤የፍትሕ ሥርዓቱ ገለልተኛ ነዉ፤ ሁሉም ለሕግ ይገዛል ወይም ለሕግ ተጠያቂ ነዉ።ሰብአዊ መብትም በወጉ ይከበራል።
አጥኚዎቹ እንደሚሉት የአንዱን ሐገር ፖለቲካዊ ሥርዓት ከሌላዉ ጋር በማነፃፀር ይኸኛዉ ከዚያኛዉ በጣም ዴሞክራሲያዊ፣ያኛዉ ከወዲያኛዉ አነስ ያለ ዴሞክራሲያዊ ወዘተ እያሉ አይበይኑም።
«የምናዉቀዉ ሰሜን ኮሪያ ዴሞክራሲያዊ አለመሆንዋን ነዉ።ኖርዌና ቺሌ ባንፃሩ ዴምክራሲያዊ ናቸዉ።ሳዑዲ አረቢያና ሰሜን ኮሪያ ግን ዴሞክራሲያዊ አይደሉም።ይኸን እናዉቃለን።ይሁንና ለምሳሌ፣ ኢራን ምን ያሕል ዴሞክራሲያዊት ነች? ወይም ሳዑዲ አረቢያ ከሰሜን ኮሪያ የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ናት፣ ቺሌ ከኖርዌ ትሻላለች---እያልን እንዲሕ አይነት ጥናት አናደርግም።»
በአጥኚዎቹ መመዘኛ መሰረት ፣ ኬፕ ቬርዴ፣ጋና፣ጊኒ ቢሳዉ፣ሌሴቶ፣ላይቤሪያ፣ ማላዊ፣ሞሪሼስ፣ናሚቢያ፣ኒጀር፣ሳሆቶሜና ፕሬቺፔ፣ሴኔጋል፣ ሴራሊዮን እና ደቡብ አፍሪቃ-13 የምርጫ ዴሞክራሲ ናቸዉ።
እነዚሕ ሐገራት የሚደረግባቸዉ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ነዉ።ከዚያ ባለፈ ግን የመሪዎች ወይም የሹማምንት ስልጣን ገደብ የለሽ ነዉ፣ የተለያዩ ተቋማት የስልጣን ክፍፍል፣ የፍትሕ ስርዓትቱ ገለልተኝነት አንድም በጣም ጠባብ ነዉ-አለያም የለም።የእነዚሕን ሐገራት ፖለቲካዊ ሥርዓት የምርጫገዢዎች ሥልጣን የተቆናጠጡበት ይሏቸዋል።
ኢትዮጵያን ይዞ፣ ሶማሌ፣ ኬንያ፣ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ናጄሪያ እያለ የ38 የአፍሪቃ ሐገራትን የፖለቲካ ሥርዓት ለሚቃኝ አጥኚዎቹ እሁለት የሚከፈሉ ግን ተመሳሳይ አገዛዞችን ያመለክቱታል።የመጀመሪያዎቹ ገዢዎቹ እንደተመቻቸዉ ምክር ቤታዊ፣ ወይም ፕሬዝደንታዊ እያሉ ምርጫ ይጠራሉ።
ሕዝብን ያንጫጫሉ፣ የሕዝብ ገንዘብን ለምርጫ ማስፈፀሚያ እያሉ ይከሰክሳሉ፣ ልባቸዉ ሲራራ ከተቃዋሚዎቻቸዉ ጥቂት ቀየጥ ያደርጉና በምናምን ከመቶ አሸነፍን ይላሉ።ከአብዱልፈታሕ አልሲሲ፣ እስከ ፖል ካጋሚ፣ ከሙሴ ቬኒ እስከ ፖዉል ቢያ፣ ከቴኦዶሮ ኦቢያንግ እስከ ኢስማኢል ዑመር ጉሌሕ ያሉት ደግሞ አንድም በደፈጣ ዉጊያ፣ ሁለትም በመፈንቅለ መንግስት አለያም በዉርስ የያዙትን ሥልጣን በካርድ «እየቀባቡ» ህዝባቸዉን እንደረገጡ ለዓመታት ይኖራሉ።
በቅርቡ ማሊ፣ቡርኪናፋሶ፣ጊኒ፣ቻድና ሱዳን የተደረጉት መፈንቅለ መንግስታት ደግሞ ለአፍሪቃ አዳዲስ አምባገነኖች አፍርተዉላታል።የኤርትራ ከብዙዎቹ አይገጥምም።ሕገ-መንግስት የለም።ምክር ቤት የለም።ምርጫ የለም።ሁሉንም የጠቀለለ አንድ ሰዉ ግን አለ።31 ዓመት።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ