የአፍሪካ ልማት ባንክ እርምጃ ፣ የሚያስከትለው አሉታዊ መዘዝ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 11 2016
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕጓ አካል ባደረገችው የ1961 ዱ የቪየና ስምምነት መሠረት ተቀባይ ሃገራት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት መወጣት ያለባቸውን ከለላ እና ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ያልተወጣችበት በመሆኑ እንድምታው ጎጂ ነው። እርምጃው ኢትዮጵያ በባንኩ በኩል ልታስፈጽም የምትፈልጋቸውን ጉዳዮች ለተንዛዛ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድም ያጋልጣልም ብለዋል።
ሌላኛው ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኝ በባንኩ ሠራተኞች ላይ ተፈፀመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ የተወሰደው አቋም የአንድን ሀገር ብሔራዊ ኢኮኖሚን ከሚወስኑ ጉዳዮች መካከል የማይጨበጥ ሀብት የሚባለውን «መልካም ስምን» የሚጎዳ ስለመሆኑ ገልፀዋል። ይህም በሀገሪቱ በቀጣይ ለሚኖሩ የልማት ሥራዎች የሚያስፈልግ ገንዘብ እንዳይገኝ እክል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት የተላለፉት ሕግ ምንድን ነው ?
ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጽሕፈት ቤቱ ሁለት ሠራተኞች ላይ በመንግሥት የፀጥታ አካላት እሥር፣ አካላዊ ጥቃት እና የመብት ጥሰት ደርሶባቸዋል በሚል አቤቱታ አቅርቦ የነበረው የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት የደረሰውን ጥፋት መርምሮ፣ በአጥፊዎች ላይም የወሰደውን እርምጃ በግልጽ እስከሚያሳውቅ ድረስ አዲስ አበባ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን በአስቸኳይ ወደ ሌላ ሀገር ለማስወጣት መወሰኑን አስታውቋል።
አንድ ሀሳባቸውን ብቻ እንድንጠቀም የገለፁ ስማቸውን ያቆዩ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ በዚህ ክስተት ኢትዮጵያ ተቀብላ እና ፈርማ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 ሥር የሕጓ አካል ያደረገችውን የ1961ዱን የቪየና ኮንቬንሽን ተላልፋለች።
በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥርዓት ጥቅሞችን፣ መብቶችን፣ ግዴታዎችን እና ግንኙነቶችን ከሚመሩት የቪየና ሁለት ኮንቬንሽኖች የዲፕሎማቲክ ተቋማትን እና ሠራተኞችን የሚመለከተውንና ኢትዮጵያ ተቀብላ እና ፈርማ በሕገ መንግሥቷ አንቀጽ 9 ሥር የሕጓ አካል ያደረገችውን 1961ዱን ስምምነት ጥሳለች ብለዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ እርምጃ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ምን መልእክት ይኖረዋል ?
ኢትዮጵያ 123 ኤምባሲዎች፣ 600 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና 67 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙባት ሀገር ስትሆን አዲስ አበባም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ከተማ ናት። ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከፍተኛ ዓለም አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥባት ከተማ እንደመሆኗ የተቀባይ ሀገርነቷ ኃላፊነት በዚያው ልክ ነው።
የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሀ ሽታሁን እንደሚሉት ደግሞ የሀገራት መልካም ስምን የማስጠበቅ ብቃት የብሔራዊ ኢኮኖሚ መሠረታዊ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ከክስተቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው።
እርምጃው ሊፈጥር የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጫና
«ብሔራዊ ኢኮኖሚን ከሚወስኑ በርካታ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ መልካም ስም ራሱን የቻለ የማይጨበጥ ገንዘብ ነው። እና ይህንን ማጣት በቀጣይ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩ የልማት ሥራዎች የሚያስፈልገንን ገንዘብ እንዳናገኝ እክል ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ተደርጎ የሚታይ ነው።» አቶ ሽዋፈራሁ የባንኩ እርምጃ የልማትድጋፍ አማራጮችን የሚጎዳ ነውም ብለዋል።
የሦስት ቢሊየን ዶላር ምርት ለውጭ ገበያ እያቀረበች ፣ የ18 ቢሊየን ዶላር ምርት ከውጭ የምታስገባው እና የ 500 በመቶ የንግድ ሚዛን ጉድለት ላለባት ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ነው። የውጭ ምንዛሪ ድርቀትም ያስከትላል ብለዋል። የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኙ «ግንኙነትን ወደሚገድብ» አዝማሚያ ሊያመራ ስላለመቻሉ መናገር እንደማይቻልም አብራርተዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ተሳትፎ
ኢትዮጵያ ውስጥ በውኃ፣ በኃይል እና መሰል የልማት ዘርፎች ላይ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚገመቱ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚሳተፍ የሚነገርለት የአፍሪካ ልማት ባንክ በመላው አፍሪካ በልማት እና ድህነት ቅነሳ ላይ የሚሠራ ትልቅ ተቋም ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ