1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ማስተናገድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ነው

ማክሰኞ፣ የካቲት 12 2016

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ወደሚካሄድበት ሥፍራ “እንዳልገባ ለመከልከል" ሙከራ አድርገውብኛል ያሉበት ክስተት "በአግባቡ እየሄዱ ያሉ ሥራዎችን ለማደናቀፍ የተደረገ ጥረት ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ ምስል Solomon Muchie/DW

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና አስተናጋጅዋ ኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ወደሚካሄድበት ሥፍራ “እንዳልገባ ለመከልከል" ሙከራ አድርገውብኛል ያሉበት ክስተት "በአግባቡ እየሄዱ ያሉ ሥራዎችን ለማደናቀፍ የተደረገ ጥረት ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ለመሪዎቹ ቀርቦ እንደነበር የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጉዳዩ ሶማሊያ በምታይበት ልክ ግዛት የመውረር እንዳልሆነ ገለፃ መደረጉን ተናግረዋል።

በ37 ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነትን ጉዳይ አቅርባ እንደነበር እና ሂደቱ በመሪዎቹ በበጎ የታየ መሆኑም ተገልጿል። ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታዎች ዛሬ በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን የማስተናገድ ኃላፊነት ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ነው ተብሏል።// 

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ውዝግብ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከሕብረቱ እገዳ ከተጣለባቸው ስድስት ሀገራት በስተቀር 49 የአፍሪካ ሀገራት በተለያየ ደረጃ ባላቸው  መሪዎች ተወክለው በጉባኤው መሳተፋቸውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ላይ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የተፈራረሙትን የባሕር በር መጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት "ሕገወጥ" እና "ኢ-ሕገመንግሥታዊ" ብሎም ቀባይነት የሌለው በማለት ውድቅ ያደረጉት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በ37 ኛው የአፍርካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመታደም አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይላት ወደ ጉባኤው ሥፍራ “እንዳልገባ ለመከልከል" ሙከራ ተደርጎብኛል ማለታቸው ይታወሳል። 

ሶማሊያ ከዚህም አልፋ "ኢትዮጵያ የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ በመኾኗ የተጎናጸፈችውን ክብርና ኃላፊነት ባግባቡ ካልተወጣች፣ ኅብረቱ ዋና መቀመጫው የት ሀገር መሆን እንዳለበት እንደገና ማጤን ይጠበቅበታል" በማለት ቅስቀሳ አድርጋለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዳሉት ኢትዮጵያ ይህንን የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በስኬት ማጠናቀቅ "ብሔራዊ ጥቅም" ነው። 

ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገር ግዛት ወስዳም ሆነ ወርራ አታውቅም 

የፕሪቶሪያው ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ጉዳይ በመሪዎች ጉባኤ ላይ ለውይይት ቀርቦ ጉዳዩ በመሪዎቹ በበጎ የታየ ስለመሆኑ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት በመሪዎች ጉባኤ ላይ ለውይይት ቀርቦ እንደነበርም ሚኒስትር ድኤታው ገልፀዋል። በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ብሎም ውህደት እንዲኖር የምንትሰራው ያሏት ኢትዮጵያ ለጎረቤቶች ችግር ሆና እንደማታውቅ ፣ ኢትዮጵያ የየትኛውንም ጎረቤት ሀገር ግዛት ወስዳም ሆነ ወርራ እንደማታውቅም ተናግረዋል። 

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ በአዲስ አበባ ምስል REUTERS

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼሕ ሞሐሙድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ውይይቱ ወደሚካሄድበት ሥፍራ እንዳይገቡ ለመከልከል ሙከራ ተደርጎባቸው እንደነበር የተናገሩት በአስተናጋጅ ሀገር ኢትዮጵያ በኩል "በአግባቡ እየሄዱ ያሉ ሥራዎችን ለማደናቀፍ የተደረገ ጥረት ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናግረዋል።  የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ይህንን ካሉ በኋላ ጉባኤው አቋርጠው የሄዱ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ትናንት ሰኞ ሁለቱ ሀገራት በገቡበት ውዝግብ ዙሪያ ተወያይቷል።

ኬንያ ስታስከፍል የነበረውን የጉዞ ሰነድ ማሟያ ክፍያ አነሳች

በሌላ በኩል ኬንያ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ወደ ግዛቷ ለሚገቡ ተጓዦች ከአንድ ወር በፊት ጀምራው የነበረውን የጉዞ ፈቃድ ማረጋገጫ ጥያቄ እና የ34 ዶላር ክፍያ ኢትዮጵያውያኑ ከክፍያው ነጻ እንዲሆኑ መወሰኗን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ አስታውቀዋል። አምባሳደር ባጫ በኤክስ ባሰፈሩት ጽሑፍ የኬንያ መንግሥት ኢትዮጵያውያንን ከአዲሱ የጉዞ ማረጋገጫ የክፍያ ሥርዓት ውጪ እንዲሆኑ የቀረበለትን ጥያቄ በአፋጣኝ ተቀብሎ በመወሰኑ ምስጋናየን አቀርበለሁ ብለዋል።

34 ዶላር የሚጠይቀው የድረገጽ የበይነ መረብ የይለፍ ሰነድ መጠየቂያ ቅጽ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ የሚጫንበት የቪዛ ካርድ በስፋት የመገልገል እድል ያላቸው ባለመሆኑ ወደ ኬንያ በሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከፍተኛ መጉላላት ፈጥሮባቸው ነበር። በበይነ መረብ የሚሞላው መጠይቅ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ይጠየቅ የነበረው 34 ዶላር መቅረቱን ግን ትናንት ምሽት ማመልከቻውን ከሞላ አንድ ኢትዮጵያዊ ለማረጋገጥ ችለናል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW