1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአፍሪካ ኅብረት እና ኢኮዋስ በቤኒን የተሞከረውን መፈንቅለ-መንግሥት አወገዙ

እሑድ፣ ኅዳር 28 2018

የአፍሪካ ኅብረት እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በቤኒን የተሞከረውን መፈንቅለ-መንግሥት “በጥብቅ እና በማያሻማ ሁኔታ” አወገዙ። ራሳቸውን “የመልሶ ማቋቋም ወታደራዊ ኮሚቴ” ብለው የሚጠሩ የተወሰኑ ወታደሮች በቤኒን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ታሎን ከሥልጣን መባረራቸውን ገልጸው ነበር።

የቤኒን ወታደሮች የመፈንቅለ መንግሥት ማader።ጋቸውን በቴሌቭዥን ሲያውጁ
ራሳቸውን “የመልሶ ማቋቋም ወታደራዊ ኮሚቴ” ብለው የሚጠሩ የተወሰኑ ወታደሮች በቤኒን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ታሎን ከሥልጣን መባረራቸውን ገልጸው ነበር። ምስል፦ Benin TV/REUTERS

የአፍሪካ ኅብረት እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ወይም ኢኮዋስ በቤኒን የተሞከረውን መፈንቅለ-መንግሥት “በጥብቅ እና በማያሻማ ሁኔታ” አወገዙ። የሁለቱ ተቋማት ውግዘት የተሰማው ራሳቸውን “የመልሶ ማቋቋም ወታደራዊ ኮሚቴ” ብለው የሚጠሩ የተወሰኑ ወታደሮች በቤኒን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ታሎን ከሥልጣን መባረራቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።  

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማሕሙድ አሊ ይሱፍ “በመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው የተሳተፉ ሁሉም ተዋናዮች በአፋጣኝ ሁሉንም ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲያቆሙ እና ያለመዘግየት ወደ ሕጋዊ የጦር ሠፈሮቻቸው እና ሙያዊ ግዴታዎቻቸው እንዲመለሱ” አሳስበዋል።

የቤኒን መንግሥት ለሰዓታት የዘለቀውን መፈንቅለ-መንግሥት እንዳከሸፈ ዘግየት ብሎ አስታውቋል። የመፈንቅለ-ሙከራው መክሸፉን የገለጹት የቤኒን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አላሳኔ ሰይዱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ወታደሮቹ “መንግሥትን እና ተቋማቱን ለማተራመስ አመጽ እንደጀመሩ” ከሰዋል።

የቤኒን ጦር ለሪፐብሊኩ አሁንም ታማኝ እንደሆነ የቤኒን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አላሳኔ ሰይዱ ገልጸዋል። 

“የኮቶኑ የጥጥ ንጉሥ” በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የ67 ዓመቱ የቤኒን ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎን በመጪው ሚያዝያ ሥልጣን ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ምስል፦ Yanick Folly/AFP

ለፕሬዝደንቱ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጭ ፓትሪስ ታሎን ደሕና መሆናቸውን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ “የቴሌቭዥን ጣቢያ ብቻ በሚቆጣጠሩ ጥቂት ሰዎች” ተጠነሰሰ ያሉትን መፈንቅለ-መንግሥት እንዳወገዙ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

መደበኛው ጦር መልሶ በመቆጣጠር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የመረጃ ምንጭ ዋና ከተማዋ ኮቶኑ እና ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

“የኮቶኑ የጥጥ ንጉሥ” በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የ67 ዓመቱ ታሎን በመጪው ሚያዝያ ሥልጣን ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር። የቀድሞው ነጋዴ ቤኒን በመሩባቸው አስር ዓመታት ሀገሪቱ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብታሳይም የጂሐዲስቶች ግጭት ተስፋፍቶባታል። 

ባለፉት ዓመታት በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙት ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ጊኒ እና በቅርቡ ጊኒ ቢሳው እና ማዳጋስካር መፈንቅለ-መንግሥት አስተናግደዋል። 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW