1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የአገልግሌት ክፍያ ዋጋ ማሻሻያ ላይ የሕዝብ አስተያየት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2016

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል። ተቋሙ አዲስ ፓስፖርት በመደበኛ ጊዜ ለመስጠት አምስት ሺህ ብር እንደሚያስከፍል፣ በሁለት ቀናት ለሚደርስ አስቸኳይ ፓስፓርት 25 ሺህ እንዲሁም በ5 ቀን ውስጥ ለሚደርስ ደግሞ 20 ሺህ ብር የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቅ ትናንት ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ፓስፖርት
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል።ምስል DW/S. Wegayehu

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የአገልግሌት ክፍያ ዋጋ ማሻሻያ ላይ የሕዝብ አስተያየት

This browser does not support the audio element.

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል። ተቋሙ አዲስ ፓስፖርት በመደበኛ ጊዜ ለመስጠት አምስት ሺህ ብር እንደሚያስከፍል፣ በሁለት ቀናት ለሚደርስ አስቸኳይ ፓስፓርት 25 ሺህ እንዲሁም በ5 ቀን ውስጥ ለሚደርስ ደግሞ 20 ሺህ ብር የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቅ ትናንት ይፋ አድርጓል።

በተመሳሳይ በመደበኛ ጊዜ እድሳት ለማድረግ አምስት ሺህ ብር፣ በሁለት ቀን ለሚደርስ አስቸኳይ እድሳት 25 ሺህ ብር እንዲሁም በ5 ቀን ውስጥ ለሚደርስ አስቸኳይ እድሳት 20 ሺህ ብር እንደሚጠይቅ ገልጿል።

ተቋሙ የፓስፖርት ገጽ ያለቀባቸው፣ እድሳት የሚፈልጉ እና እርማት የሚያስፈልጋቸው፣ ፓስፖርቱ ቀን ያለው ሆኖ የተበላሸ፣ እርማት የሚያስፈልገው ብሎም የጠፋ ፓስፖርት ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቅ ግልጽ አድርጓል። ከፓስፓርት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቅሬታ እና አቤቱታ የሚቀርብበት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን እያዘመነ፣ ቅሬታዎችንም ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ከሰሞኑ አስታውቋል።

የፓስፖርት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች


ከዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አድርጎ ያፀደቀው መሆኑንም አስታውቋል።

የሰዎች አስተያየት 

"ከዛሬ ሁለት ወር በፊት ነው ያመለከትኩት ፓስፖርቴን ለማሳደስ። በዚያን ወቅትም ክፍያው የነበረው ሁለት ሺህ ብር ነው። አሁን ከሁለት ወር በኋላ ፓስፖርቴ ታድሶ ተቀብያለሁ። ከዚያ በፊት በነበረው በስድስት መቶ ብር ነበር የመጀመርያው ፓስፖርቴ የአገልግሎት ጊዜው ሲያበቃ ያሳደስኩት። አሁን ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ከዚህ ጋር ይገናኝ አይገነኝ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፤ የፓስፖርት ዋጋ በዚህ ደረጃ መጨመሩ መንግሥት ራሱ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እርምጃዎችን እወስዳለሁ እያለ ባለበት ወቅት መሆኑ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል"።

የክፍያ ጭማሪው የተለያየ ምላሽ አስተናግዷል። ምስል Reuters/T. Negeri


"ማሻሻያው እኔንም አስደንግጦኛል። ግን ተገቢ ነው ብየ ነው የማስበው። ኢሚግሬሽን በተገልጋዮች ብዛት የሚጨናነቅ ፣ በዚያ ምክንያት ለሙስና የተጋለጠ ተቋም ነበር። አሁን ላይ ክፍያው በዚህ መልክ ማደጉ አንዳንድ ተቋማዊ ግድፈቶችን ያርማል ብየ አስባለሁ"።

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሥራ እንቅስቃሴ


"ፓስፖርት ሁል ጊዜ ያለው፣ የተሳካለት ብቻ አይደለም ወደ ውጪ የሚወጣው። ተማሪዎች አሉ ፣ ለአስቸኳይ ጉዳይ ለሕክምና ወደ ውጪ የሚወጡ ሰዎች አሉ እና ከዛሬ ነገ አሳድሳለሁ እያለ ባለበት ሰዓት ነው ይሄ የተፈጠረው እና አምስት ሺህ ብር ለመንግሥት ሰራተኛ፣ ለደሞዝተኛ በጣም ብዙ ብር ነው"። 


"ለሙስና የተጋለጠ [ተቋሙ] ዜጎችን ለእንግልት ለሮሮ ፣ለከፍተኛ ወጪ የዳረገ ነገር ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስተካክለናል ይላሉ። ይህ ሆኖ ሳለ እንደገና አስቸኳይ ከሀገር መውጣት ያለበት አንድ ዜጋን ሃያ ፣ ሃያ አምስት ሺህ ብር መጠየቅ ምን ማለት ነው? መንግሥት ለዜጎቹ የዜግነት አገልግሎት እየሰጠ ነው ወይስ ደግሞ በዜጎቹ ላይ እየነገደ ነው? የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው።"የፓስፓርት ለማግኘት እና ለማደስ ያለ ችግር በኢትዮጵያ


የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ ለዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት ሳይሰጥ በመቆየቱ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት እና ሮሮ ተዳርገው መቆየታቸውን ከሳምንታት በፊት መግለጫ የሰጡት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ተናግረው ነበር። አክለውም በቀን ይታተም ከነበረው 200 ፓስፖርት አሁን ቁጥሩን ወደ 14 ሺህ ማሳደግ ስለመቻሉ አብራርተው ነበር።


ባለፈው ዓመት 1.1 ሚሊዮን ፓስፖርት መታተሙን ያስታወቀው ይሄው ተቋም፤ ያም ሆኖ ግን "የሕዝቡ ለቅሶ ቆሟል" ወደሚባል ደረጃ አለመደረሱንም አመልክቶ ነበር። 

ሰለሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW