የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ
ቅዳሜ፣ መስከረም 24 2018
ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በደማቅ ስነስርዓት አዲስ አበባ ውስጥ በተከናወነው የኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ አከባበር ላይ በርካታ ታዳሚያን በመገኘት ለበዓል አከባበሩ ድምቀትን ፈጥረዋል፡፡ በበዓሉ መክፈቻ ላይ የምርቃት ስነስርዓት ያከናወኑት አባገዳዎችም ሁሉም እንደየስርዐቱና ማዕረጋቸው መርቀዋል፡፡ የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ በዚሁ ወቅት በምረቃ ስርዓቱ ላይ ባሰሙት መልእክት ስለሰላም አስፈላጊነት አብዝተው ተጣርተዋል፡፡ “ኦሮሞ ሰላም ላንተ ይሁን፤ ሰላም ይደርብህ፤ ያለሰላም ምንም የለምና ሰላምህን አስቀድም” ሲሉ ስለሰላም አጉልተው ተጣርተዋል፡፡
ሰፊ እሴት ያለው ኢሬቻ ኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖችን ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በመጡ እንግዶችም ነበር የደመቀው፡፡ የበዓሉ አከባበር ለህዝቦች አንድነት እና አገር ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንደምኖረው የገለጹት አስተያየት ሰጪ የበዓሉ ታዳሚያን አስተያየቶቻቸውን ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንደኛው በመላው ክልሉም ይሁን በአገሪቱ ፍጹም ሰልም ይስፈን ዘንድ ሁሉም ወገን ለሰላም ተገዢ እንዲሆኑ ነው፡፡
ኢሬቻ እና ሰላም
ከባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ በመምጣት ኢሬቻ ላይ የታደሙት መኮ ሀጂ አደም ከአስተያየት ሰጪዎቹ ናቸው፡፡ “እንደ እናት እኛ በወለደው አንጀታችን ተማጽእኖ እያቀረብን ልጆቻችን ወደ ሰላም ተመልሰው ህይወታቸውን እንዲመሩ ብሎም መንግስትም ለዚህ ሆደ ሰፊ እንዲሆን ጠይቀናል” ሲሉ ስሰላም አንስተዋል፡፡
አባገዳ ታምሩ ደገፋ የተባሉት ከሰበታ አከባቢኢሬቻላይ የታደሙት ሌላው አስተያየት ሰጪ በፊናቸው፤ “እንደ አባገዳዎች እኛ ከሁልም በላቀ መልኩ የምንሻው ሰላምን ነው” ያሉት አባገዳ ታምሩ ደገፋ ሰው ደም መፍሰስና እገታው የሚቆምበት ዓመት እንዲሆንም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻን እንደ አገራዊ መግባቢያ መድረክ
አበበ በሪ የተባሉት ከሚኖሩበት አሜሪካ ሜሪላንድ መጥተው ለመጀመሪያ ጊዜ ኢሬቻ ላይ የታደሙት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፤ “ኦሮሞ የራሱን ባህል ትሩፋቱን እያሳበት” ያለው ኢሬቻን በጣም በማድነቅ እንደ አገር የሚታየውን የሰላሙን እጦት ግን ዜጎችም የበኩላቸውን በመወጣት ማስተካከል እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ “በርግጥ ባሁኑ ጊዜ ህዝቡ መሃል የመከፋፈል ነገሮች ስስተዋል ይታያል፤ ደግሞ የመጣው ካለመረዳዳት ይመስለኛል፡፡ በእንዲህ አይነት መድረክ ህዝቡ በሚገናኝበት ጊዜ ልዩነቶቹ እየመነመኑ ነገሮች እየተሻሻሉ ይመጣሉ” የሚለውን ተስፋቸውን አስረድተዋል፡፡ እናም አሉ በሰላም ግንባታውም ሆነ ለሁሉም የሚበጅ ያሉትን አንድነት በመፍጠሩ ረገድ ህዝቡ ራሱ የሚጠበቅበትን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ህዝቡ እርሰበራሱን መዋደድ ደግሞ ከነዚህ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው ነው የተባለው፡፡
ኢሴቱን ጠብቆ የተከበረው ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ፍጹም ሰላማዊና የተረጋጋም ነበር፡፡ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ጎብኚነት በዓሉ ላይ ስታደሙም ታይተዋል፡፡ በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀትና ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር የከተማው ነዋሪን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች አስተዋፅኦያቸውን ተወትተዋል ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር