1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራንና የሳዑዲ አረብያ ዕርቅ

ሐሙስ፣ መጋቢት 7 2015

አሜሪካ ከሳዑዲ አረቢያና የባህረ ሰላጤው አገሮች ጋር ካላት የቆየና የጠበቀ የንግድ፣ የፖለቲካና ወታደራዊ ግንኑነት አንጻር ተፎካክሪዋ ቻይና በወዳጆቿ ሰፈር ያልተጠበቀና የተሳካ ሽምግልና ማክሄዷ ለሁሉም አነጋጋሪ ሆኗል።ዲፕሎማሲይዊ ክስተቱ፤ አለም ዓቀፍ ግንኙነቱ እየተለወጠና አዳዲስ የኃይል አሰላለፎች እይታዩ መሆኑን የሚያመለክት ነው ተብሏል።

China Treffen von Wang Yi, Ali Shamkhani und Musaad bin Mohammed Al Aiban
ምስል CHINA DAILY via REUTERS

ያልተጠበቀው የኢራንና የሳዑዲ አረብያ እርቅ

This browser does not support the audio element.

 
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቤጂንግ ላይ የረጅም ግዜ ባላንጣዎቹ ሳዑዲ አረቢያና ኢራን ሳይጠበቅ እርቅ አውርደው፤ ግንኑነታቸውን በማደስ ለየአገሮቻቸውና ለአካባቢው ሰላምና እድገት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። እርቁ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ግን ደግሞ ለአካባቢውና ለአለም ሰላም ጭምር ትልቅ አንደምታ ያለው እንደሆነ በሰፊው እየተገለጸ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ብዙዎችን ያስገረመውና ያስደመመው እነዚህ የቆዩ ባላንጣዎች ወደ እርቅ መምጣታቸው ሳይሆን አደራዳሪዋና አስታራቂዋ ቻይና መሆኗ ነው። 
አሜሪካ ከሳዑዲ አረቢያና ከባህረ ሰላጤው አገሮች ጋር ካላት የቆየና የጠበቀ የንግድ፣ የፖለቲካና ወታደራዊ ግንኑነት አንጻር ተፎካክሪዋ ቻይና በወዳጆቿ ሰፈር  ያልተጠበቀና የተሳካ ሽምግልና ማክሄዷ ለሁሉም አነጋጋሪ ሆኗል። ዲፕሎማሲይዊ ክስተቱ፤ አለማቀፍ ግንኙነቱ እየተለወጠና አዳዲስ የኃይል አሰላለፎች እይታዩ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነም እየተነገረ ነው። ባለፈው አርብ የተፈረመው የሁለቱ  አገሮች ስምምነት የሉዓላዊ ግዝቶችን ማክበርንና የጣልቃገብነትን ማስወገድን አስፈላጊነት መሰረት ያደረገ ነው። በሁለት ወር ግዜ ውስጥም ሁለቱም ኢምባሲዎቻቸውን በመክፈት የንግድና የፖለቲካ ግንኑነቶቻቸውን ለማሳለጥ መስማማታቸው ተገልጿል። ድርድሩን የመሩትና ለውጤት ያበቁት የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት ሚስተር ዋንግ ዪ  ድርድሩን የተሳካና የሰላም ድል ሲሉ ገልጸውታል።  
ይህን የሰላም ስምምነት ከአካባቢው አገሮች ከእስራኤል በስተቀር ሌሎቹ ደግፈውታል። አሜሪካ የቻይናን የአስታራቂነት ሚና ትኩረት ሳትሰጥ በሁለቱ አገሮች እርቅ መፈጠሩ ለአክባቢው መረጋጋትና የየመንን ጦርነት ላማስቆም ሊረዳ የሚችል በመሆኑ በበጎ እንደምታየው መግለጿ ተዘግቧል። 
የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ወደፊት የሚታይ ሆኖ፤ ከወዲሁ ግን ባለሙያዎችና የፖቲካ ተንታኖች ለሁለቱ አገሮች በተለይ በአሁኑ ወቅት ወደ ድርድርና ሰላም የመጡባቸውን ምክንያቶች በመጥቀስ ሲከራከሩ ይሰማሉ።።  በዶሀ ኢንስቲቲዩት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚስተር ኢብርሂም ፍሬሀይት ይህ ድርድር ሊሳካና እርቅ ሊወርድ የቻለው የሶስቱም ማለት ሁለቱ ተደራዳሪዎችና አስታራቂዋ ቻይና  ፍላጎቶች በመገናኘታቸው ነው። 
“ በመጀምሪያ ኢራንን በሚመለከት  በኒውክለር ፕሮግራሟ ምክንያት ከአሜሪካና እስራኤል ሊስነዘር በሚችል ጥቃት ተባባሪ ልትሆን የምትችለውን ሳዑዲ አረቢያን መነጠል ስለፈለገችና ኢራንም አሜሪካኖቹ እንደሚፈልጉት የተገለለች አለመሆኑን ለማሳየት ነው። በሳኡዲ አረቢያ በኩል፤ በተለይ ፕሪዝዳንት ባይደን ከመጡ ወዲህ  ዲፕሎማሲያዊ ግንንኙነቶችንና ወታደራዊ ትብብሮችን ከሌሎች አገሮች ጋር ጭምር የማድረግ ፍላጎቶች ሲታዩ ቆይተዋል። በመንግስታቱ ድርጅት በዩኪሬን ላይ በተሰጡ ድምጾች ይህ አቋም በግልጽ ታይቷል። ቻይና ደግሞ፤ ከሁለቱም አገሮች ጋር የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላት በመሆኑ፤ ሁለቱን አገሮች አቀራርቦና አስታርቆ መያዙ ተመራጭ በመሆኑ ነው፤ በማለት በነዚህ ምክንያቶች ቻይና ዋና አለም ዓቀፍ አደራዳሪ ለመሆን እንደበቃች ሲናገሩ ተሰምተዋል።  
 የቀድሞዋ የአሜሪካ ዲፕሎማት ወይዘሮ ሂላርይ ማን ግን ይህ ስምምነት አሜሪካ በአካባቢው የነበራትን ተሰሚነት በቻይና እንደተነጠቀች የሚያሳይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፤ 
“ ዓሜሪካኖች አገራቸው በዓለምና በመካከለኛው  ምስራቅ ዋናዋ አይተኬ ሀይል እንድሆነች አድረገው ነው የሚያስቡት። አሁን በቻይና አደራዳሪነት የተደረሰው ስምምነት የሚያሳየው ግን ያን ቦታና ተሰሚነት ቻይና የተካችውና የወሰደችው መሆኑን ነው” በማለት ሁኔታው በአለም ዓቀፉ የፖለቲካ  መድረክ ቻይና የአሜሪካ ዋና ተገዳዳሪ ኃይል ሆና የመውጣቷ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል 
የፖለቲካ ተንታኖችና ታዛቢዎች እንደሚሉት ይህ ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ፤ በሁለቱ የአካባቢው ባለጡንቻ አገሮች መካከል ያለውን ውጥረት ያረግበዋል፤ በየመን የሚካሂደው ጦርነት እንዲያበቃ ሊረዳ ይችላል፤ የቻይናንም አለም ዓቀፋዊ ሚና አጉልቶ  የሚያወጣ ይሆናል። 
ገበያው ንጉሴ 
ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW