1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች “ከባድ ጉዳት” እንደደረሰባቸው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ገለጹ

እሑድ፣ ሰኔ 15 2017

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግሴትዝ “የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር አውድመናል” ብለዋል። የአሜሪካ ጦር በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ “ምሽግ ደርማሽ” በተባሉ 14 ጂቢዩ-57 ቦምቦች ጥቃት እንደፈጸመ ፔንታጎን አስታውቋል። አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር ጥሳለች ሲሉ የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰዋል

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግሴትዝ
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግሴትዝ “የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር አውድመናል” ብለዋል። ምስል፦ Alex Brandon/AP Photo/picture alliance

ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ የተፈጸመው ጥቃት የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር “አውድመዋል” ሲሉ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ተናገሩ። በፔንታጎን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር አውድመናል” ያሉት መከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሔግሴትዝ የአሜሪካ ጥቃት “የኢራን ወታደሮችን ወይም የኢራንን ሕዝብ ዒላማ አላደረገም” ብለዋል። 

ዶናልድ ትራምፕ “ሰላም ይፈልጋሉ። ኢራን እሱን መንገድ መምረጥ አለባት” ሲሉ ፒት ሔግሴትዝ መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። አሜሪካ በኢራን የኑክሌር ተቋማት ላይ ውድመት ያስከተለ ጥቃት ጥቃት መፈጸሟን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ትላንት ቅዳሜ ነበር። አሜሪካ ጥቃት የፈጸመችው “ምሽግ ደርማሽ” ተብለው በሚጠሩ 14 ግዙፍ ጂቢዩ-57 (GBU-57) ቦምቦች እንደሆነ ፔንታጎን አስታውቋል።

መሬት ሰርጎደው በመግባት የሚነጉዱት ግዙፍ ቦምቦች በሁለት የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ መጣላቸውን የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዳን ኬይን ተናግረዋል። የአሜሪካ ጥቃቶች በኢስፋሐን፣ ናታንዝ እና ፎርዶ በሚገኙ የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። 

አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመችባቸው የኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች መካከል ፎርዶው ተብሎ የሚጠራው በተራራማ የሀገሪቱ ክፍል ከመሬት ውስጥ የሚገኝ እንደሆነ ይነገርለታል። ምስል፦ Planet Labs/dpa/picture alliance

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለህዝባቸው በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ጥቃቱን “አስደናቂ ወታደራዊ ስኬት” ብለውታል። ተሒራን የሰላም ስምምነት ካልለፈጸመች እና የአጸፋ ርምጃ ለመውሰድ የአሜሪካን የጦር ሰፈሮችን ዒላማ ካደረገች የበለጠ “የከፋ  ጥቃት” ይከተላታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርግሐቺ አሜሪካ ጥቃቱን በመፈጸም የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር ጥሳለች ሲሉ ወንጅለዋል። ጥቃቱን “አጸያፊ” ያሉት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ዘላቂ ዳፋ” እንደሚኖረው አስታውቀዋል። የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የአሜሪካ እስራኤል  የተቃናጀ ጥቃት “ኢራን ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ያሏትን አማራጮች ሁሉ የመጠቀም መብት አላት” ብለዋል።

የሌሊቱን የአሜሪካን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ ርምጃ ወስዳለች። ኢራን በእስራኤል ላይ ባስወነጨፈችው የሚሳኤል መዓት በቴል አቪቭ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት ሲዳርግ በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል የሚገኙ የንግድ ማዕከላትን የያዙ ህንጻዎች ብርቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። 

ከጥቃቱ አስቀድሞ አሜሪካ ግጭቱን የምትቀላቀል ከሆነ በቃጣናው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች እና ጥቅሞች ሁሉ ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ኢራን በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች ። 
የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጥቃቱን ተከትሎ በሰጧቸው መግለጫዎች ኢራን ለደረሰባት ጥቃት በእጇ የሚገኙ ማናቸውንም የአጸፋ አማራጮች ሁሉ ልትጠቀም እንደምትችል አስታውቀዋል። 

ኢራን በአሜሪካ ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ ከእስራኤል በተጨማሪ በአካባቢው ባሉ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ከማድረስ ባሻገር የዓለማችን አንድ አራተኛውን የነዳጅ ዘይት ማጓጓዣ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥ ልትዘጋ እንደምትችል ተንታኞች እያስጠነቀቁ ነው።
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW