1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢሰመኮ አዲስ የበላይ ኃላፊ ሹመት እና የተሰጡ አስተያየቶች

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ ጥር 23 2017

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም አቶ ብርሃኑ አዴሎን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟል። ተቋሙ በዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሥራ ዘመን ምን መልክ ነበረው? የሰብአዊ መብቶችን ጥበቃ በሚመለከት ምንስ ተጨባጭ ሥራ አከናወነ? የሚለውን እና ከአዲሱ ተሿሚ ምን ይጠበቅ ይሆን?

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም አቶ ብርሃኑ አዴሎን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የኢሰመኮ አዲስ የበላይ ኃላፊ ሹመት እና የተሰጡ አስተያየቶች

This browser does not support the audio element.

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የቀድሞ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሥራ ዘመን ባለፈው ዓመት መጠናቀቁን ተከትሎ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ በተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነርነት ሲመራ ቆይቷል።

ለዚሁ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ለመሾም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አስመራጭ ኮሚቴ አዋቅሮ ጥቆማ ሲቀበል እንደቆየ እና 50 ሰዎች ተጠቁመው እንደነበር የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል።

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ሽልማታቸዉን ተቀበሉ

በዋናነትም "ተፈላጊ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድ፣ ለመወዳደር ፈቃደኝነት፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ መሆን እና ሥነ ምግባር" መመዘኛ መስፈርቶች እንደነበሩ ተገልጿል።

በኢሰመኮ ሥራ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች 

ለመሆኑ ኢሰመኮ ባለፉት አምስት ዓመታት በሥራው ምን መልክ ነበረው። የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ። "ዶክተር ዳንኤል በቀለ ኃላፊነት ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ኢሰመኮ እየሠራ ያለው ሥራ አንቱ ከሚባሉ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው"

ቅድሚያ ለሰብአዊነት የተባለው የሲቪክ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ ግጭቶች የበዙበት ጊዜ ስለነበር "ፈተና የበዛበት ዘመን ነበር።" ያም ሆኖ ግን ኢሰመኮ የተሻለ እንቅስቃሴ ካደረጉ የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል አንዱ ሆኗል። ብለዋል

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ከሃላፊነታቸው ተሰናበቱ

"በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገራችን በሁሉም ጫፍ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍተው እና እጅግ በአደጋ ውስጥ ነው የሚገኙት። እና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከእነ ችግሮቹም ቢሆን ምርመራዎችን በየጊዜው ማውጣቱ የሚበረታታ እና መቀጠል ያለበት ነው።"

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የቀድሞ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሥራ ዘመን ባለፈው ዓመት መጠናቀቁን ተከትሎ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ በተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነርነት ሲመራ ቆይቷል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው ሌላኛው ባለሙያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ናቸው።

"በገለልተኝነት አቋማቸው የሚታወቁ፣ ከፓርቲ ወገንተኝነት የራቁ ሰዎች ነበሩ ኮሚሽኑን እስከዚህ ደረጃ ያደረሱት። ብለዋል።

ኮሚሽኑ በቀጣይ ምን ሊሠራ ይገባል ?

በቀጣይ ይህ ተቋም ምን ቢሠራ ይበጃል? እንዲሰራስ ይጠበቃል የሚለውንም ባለሙያዎቹን ጠይቀናል። አቶ ታደለ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥል ይሻሉ።

"ምንም እንኳን መንግሥት ቢያቋቁማቸውም ነፃ፣ ገለልተኛ፣ በሕዝብ ዘንድ ታማኝ መሆናቸውን ሕዝብ ሊመሰክርላቸው እንዲችል የተጀመረው ሥራ የበለጠ ሊጠናከር ይገባል።"

አቶ ያሬድ እንደሚሉት ደግሞ አዲሱ ሹመት በመንግሥት በኩል ተቋሙንም፣ መስኩንም የመቆጣጠር ፍላጎት ማሳያ ነው። 

"አሁን የተሾሙት ሰው የፓርቲ አባል የነበሩ፣ በቀድሞ ኃላፊነታቸውም በበጎ ስማቸው የማይጠራ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር ምንም አይነት አስተዋፅዖ እና አበርክቶ በግልጽ የሚታይ ያልነበራቸው ሰው ስለነበሩ ተቋሙንም፣ መስኩንም የመቆጣጠር ዝንባሌ በመንግሥት በኩል መኖሩን" ያሳያል ብለዋል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር የነበሩት ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በመስከረም 201 የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል። ምስል፦ Deutsche Afrika Stiftung

ከመንግሥት የሚመጡ ጫናዎች መኖራቸውን የገለፁት አቶ መብርሂ በበኩላቸው፣ በኮሚሽኑ ምርመራ የተደረገባቸው ሥራዎች እንዳይወጡ መደረጋቸውን በመጥቀስ ተቋሙ ከፍተኛ ጫና ይጠብቀዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ

አዲሱ የኢሰመኮ ኃላፊ ከ15 ዓመታት በፊት የመንግሥት ተሿሚ የነበሩ መሆናቸው ተጠቅሶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የገለልተኝነት ጥያቄ የቀረበባቸው ሲሆን በሌላ በኩል ኢሰመኮ በአንዳንድ ሪፖርቶቹ ይጎድለው ነበር የተባለ የገለልተኝነት ሁኔታ ተጠቅሶ ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነትን ባስጠበቀ ገለልተኝነት እንዲሰራ ተጠይቋል። አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ሀገሪቱ በቀጣይ ከሚጠብቋት ኹነቶች እንፃር በተቋሙ ዙሪያ ጥንቃቄ እንዲኖር ጠይቀዋል።

"ቀጣይ ምርጫም እየመጣ ነው፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ሀገሪቱ ልታካሂድ ፖሊሲ ነድፋለች። ከፍትሕ ሚኒስቴር ጀምሮ ወሳኝ የሚባሉ ተቋማት በመንግሥት አባላት እና ታማኝ የሚባሉ ሰዎች የሚያዙበት ሁኔታ ከወዲሁ እየተመቻቸ መምጣቱ ቀጣዩን ጊዜ ከባድ ዩሚያደርገው ይመስለኛል።"

ተቋሙን ላለፉት ስድስት ወራት በተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተርነት የመሩት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ሹመቱን አስመልክቶ ለአዲስ ተሿሚ ባስተላለፉት የመልካም ሥራ መልዕክት "ወቅታዊ የሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ጠንካራ አመራር እና ውጤታማ የሰብአዊ መብቶች ሥራ የሚጠይቅ" መሆኑን በአጽንዖት አስታውሰዋል። 

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ጸሀይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW