የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ላይ ግጭት
ሰኞ፣ ሰኔ 6 2008የኤርትራ የማስታወቂያ ሚንስቴር በደረ-ገፁ ላይ ባሰፈረዉ ጋዜጣዊ መግለጫ በትላንትናዉ ዕለት የፆረና ማሕከላዊ ግንባር ተብሎ የሚጠራዉ ቦታ የሰፈረዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላክያ ሠራዊት ኤርትራ ላይ ጥቃት ማድረሱን አመልክቷል።
እንደ ጋዜጣዊ መግለጫዉ ከሆነ በሕወሓት የሚመራዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ኃይል ይህን ርምጃ የወሰደበት አላማ ግልፅ ባይሆንም የኤርትራ መንግሥት ጉዳዩን ተከታትሎ መረጃ እንደሚያቀርብ ገልጿል። ይህን አስመልክቶ ከኤርትራ መንግስት በኩል ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደርገነዉ ሙከራ ለጊዜዉ አልተሳካም።
የተለያዩ የዜና አዉታሮች በድንበር አካባባቢ የሚኖሩ ወገኖችን ዋቢ አድርገዉ እንደዘገቡት በፆረና አካባቢ ከእሁድ ጥዋት ጀምሮ ከባድ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ ነበር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ወታደሮች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችም በቦታዉ ላይ ሲንቀሳቀሱ ተመልክተዋል። ይህም ክስተት በሁለቱ ሃገራት መካከል አዲስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋት አሳድሯል።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም ጉዳዩን እየተከታተሉ እና የኤርትራን ዉንጀላ የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን በመንግስት ኮሙኒኬሸን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። ግን ለግዜዉ ማለት የሚቻለዉ ይላሉ ሚንስትሩ «አንድ አንድ የትንኮሳ ሙከራዎች በኤርትራ በኩል እንደ ነበሩ እና በተለይም በተባባሩት መንግስታት የተጣለባት ጫና ትኩረት ለማዞር እንደሆነ ይጋመታል » ብለዋል።
ኤርትራ በ1983 ሉአላዊ አገር ከሆነች በኋላ ከ1990 እስከ 1992 በድንበር ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ከባድ ጦርነት አካሄዳ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ጦርነት ከ70,000 የሚበልጡ ወገኖች መሞታቸዉ ይነገራል።
መርጋ ዮናስ
ሸዋዬ ለገሠ