የኢትዮጵያና የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ማቋቋም ስምምነት
ሰኞ፣ ነሐሴ 12 2006 የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር አብዱል ራሂም ሞሃመድ ሁሴን፤ በበኩላቸዉ የጋራ ጦር ኃይል መቋቋሙ፤ ቀደም ሲል በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረዉን የሰላምና የፀጥታ ትብብር የበለጠ ያጠናክረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአንድ እዝ ሥር የሚንቀሳቀስ ጥምር የመከላከያ ኃይል ለመቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸዉን ያሳወቁት ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ፤ አዲስ አበባ ላይ 11ኛዉን የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ ካጠናቀቁ በኋላ ባሳለፉት ዉሳኔ እንደሆነ ተመልክቶአል። የሁለቱ ሃገራት ጥምር የመከላከያ ኃይል ከፊታችን መስከረም ወር ጀምሮ እንደሚቋቋም መረጃ መዉጣቱን የሚገልፁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ጉዳይ መምህር አቶ ደመቀ አጭሶ፤ ስምምነቱ ለአካባቢዉ ሃገራት ፋይዳ አለዉ ሲሉ ገልፀዋል።
ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የድንበር ላይ ግጭትን ለማቆም በየግዜዉ ሥምምነት ላይ ቢደርሱም ገቢራዊነቱ አሁንም አጠያያቂ እየሆነ ነዉ። የኢትዮጵያ እና የሱዳን የጋራ የመከላከያ ኃይል መቋቋም በደቡብ ሱዳን እንዴት ይገመገም ይሆን መምህር ደመቀ፤ እንደሚሉት የሁለቱ ሃገሪት መቀራረብ ምናልባትም በአፍሪቃዉ ቀንድ ላሉት ሃገራት መቀራረብ ምሳሌ ይሆናል። እንዲያም ሆኖ በደቡብ ሱዳን ላይ የሚያመጣዉ ጫና አይኖርም፤ በሃገራቱ ድንበር አካባቢ የሚታየዉን የፀጥታ ጉዳይ ከማስጠበቅ በቀር።
ኢትዮጵያ አባይ ላይ እየገነባች ያለዉን ግድም ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአባይ ዉኃ አጠቃቀም ከሁነኛ ስምምነት ላይ አልደረሰም። ጉዳይ በቃላት እየተጣዘጠዙ ይገኛሉ። የሱዳን እና የኢትዮጵያ የጋራ የመከላከያ ኃይል መቋቋም ግብፅን ስጋት ላይ አይጥል ይሆን፤በተለይ በዉኃ ፖለቲካ ላይ ትኩረታቸዉን ያደረጉት አቶ ደመቀ አጭሶ፤ ግብፅ፤ ከዚህ በፊት የያዘችዉን የዉኃ መርህ ሊያስቀይራትና ወደ ትብብሩ ጎራ እንድትቀላቀል ያደርጋታል ሲሉ ተናግረዋል።
ሙሉዉን ቃለ ምልልስ የድምፅ ማእቀፉን በመጫን ያድምጡ!
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ