1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያና የሱዳን ግጭት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 21 2014

ካርቱም በአዲስ አበባ የሱዳን አምባሳደርን «ለምክክር» እንደምትጠራ አስጠንቅቃለችም።የኢትዮጵያ ጦር የተማረኩ የሱዳን ወታደሮችን «ገድሏል» የሚለዉን ወቀሳ ኢትዮጵያ አስተባብላለች።የኢትዮጵያ መንግስት እንዳስታወቀዉ የሱዳን ወታደሮች የተገደሉት ኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥ ዘልቀዉ ገብተዉ ባካባቢዉ ከሰፈረ የኢትዮጵያ ሚሊሺያ ጋር ባደረጉት ግጭት ነዉ።

Äthiopien  West Gondar und Metema
ምስል፦ DW/Alemenew Mekonnen

የኢትዮጵያና የሱዳን ግጭት ዳግም አገርሽቷል

This browser does not support the audio element.

 

በድንበር ግዛት ይገባኛል የሚወዛገቡት ኢትዮጵያና ሱዳን ሰሞኑን አዲስ እሰጥ አገባ ገጥመዋል።የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ ጦር የማረካቸዉን 7 የሱዳን ወታደሮችና ሲቢሎች  ገድሏል በማለት ኢትዮጵያን ይወቅሳል።ካርቱም በአዲስ አበባ የሱዳን አምባሳደርን «ለምክክር» እንደምትጠራ አስጠንቅቃለችም።የኢትዮጵያ ጦር የተማረኩ የሱዳን ወታደሮችን «ገድሏል» የሚለዉን ወቀሳ ኢትዮጵያ አስተባብላለች።የኢትዮጵያ መንግስት እንዳስታወቀዉ የሱዳን ወታደሮች የተገደሉት ኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥ ዘልቀዉ ገብተዉ ባካባቢዉ ከሰፈረ የኢትዮጵያ ሚሊሺያ ጋር ባደረጉት ግጭት ነዉ።ኢትዮጵያ መንግስት የሰዉ ሕይወት በመጥፋቱ ሐዘኑን ገልጧልም።ሱዳን በሚያዋስኑት የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እንደሚሉት ደግሞ የሱዳን ታጣቂዎች ሰሞኑን ጥቃት እያደረሱ ነዉ።

 በኢትዮጵያ ሚሊሺያዎችና በሱዳን መደበኛ ጦር መካከል ግጭቶች መከሰታቸውን የየአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፤ የግጭቱ መነሻ የሱዳን ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ተጨማሪ የእርሻ መሬት ከመዝረፍ ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩት፣ የኢፌድሪ መንግስት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ሙሉ ፍላጎት እንዳለው ገልፆ ያ ካልሆነ ግን የኢትጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሙሉ አቅምና ዝግጅት አለው ብሏል፡፡ ሱዳን ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብላ ባሰበችበት ጊዜ ሁሉ ትንኮሳ እንደምትሰነዝር ልምዷ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በ1969 በወቅቱ ከነበረው በሲያድ ባሬ ከሚመራው የሶማሌ መንግሰት ጋር ጦርነት በነበረችበት ወቅት አጋጣሚውን ተጠቅማ በምዕራብ ኢትዮጵያ የወረራ ሙከራ ማድረጓን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁንም በእዛው እሳቤ ትንኮሳ መጀመሯን ያምናሉ፡፡ 
ሰሞኑን ከሁመራ ጫፍ እስከ መተማ በሚዘረጋው በሁለቱ አገሮች ድንበር የሱዳን ኃይሎች በተለይ ከሰኔ 15/2014 ዓ ም ጀምሮ የኢትዮጵያን አካባቢዎች በከባድ መሳሪያ እደበደቡ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ አንድ ሁመራ አካባቢ የማይካድራ ከተማ ነዋሪ ትናንት በረከትና ምድረ ገነት በተባሉ አካባቢዎች ከጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት ድብደባ ፈፅመዋል፣ የደረሰ ጉዳት ግን እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ 
ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ የከፋ ችግር ከመድረሱ በፊት መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ 
አቶ እያዩ ፈቃዴ በመተማ ወረዳ የሽንፋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የሱዳን ታጣቂዎች ካላቸው የመሬት ፍላጎት አንፃር በሚወስዷቸው ትንኮሳዎች በርካታ አርሶ አደር ባለሀብቶች ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ ነው ብለዋል፡፡ 
የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪው አቶ ሲሳይ አሸብር የሱዳን ወታደሮችና “ጁንታ” ያሏቸው ኃሎች ከ2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ትናንት ገላል ውሀ በተባለ አካባቢድብደባ ሲፈፅሙ እንደዋሉ አስረድተዋል፣ አመሻሹንና ዛሬ ጠዋትም ከባድ መሳሪያዎችን ተኩሰዋል ነው ያሉት፡፡ 
የኢፌድሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ደሲሳ የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ በመግባቱ በአካባቢው ሚሊሺያ ጥቃት እንደደረሰበት አረጋግጠዋል፡፡ 
ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት እንደሌላቸው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ያ ካልሆነ ግን የአገራችን ሉዓላዊት ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም አለን ብለዋል፡፡ 
የሱዳን ጦር በጦር አውሮፕላን ይታገዛል ስለሚባለው አቶ ከበደ ሲመልሱ፣ 
‘የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን የአየር ክልል በመጣስ የጦር ሄሌኮፕተር እየተጠቀመ ነው’ እየተባለ ስለሚነገረው ስሞታ ሲመልሱ፣ “ መረጃው የለንም መረጃው ካለን አጠናቅረን … የኢትዮጵያ አየር ክልል ሙሉ ጥበቃ ይደረግለታል፣ ገብቶ መውጣት አይቻልም በቂ አቅም የገነባ ተቋም ነው፣ ጠፍቶና እንዳይኖር ተደርጎ የነበረው በወያኔ መሰሪ ድርጊት ነው፣ አሁን የአየር ኃይላችን በሙሉ ቁመና ላይ ነው ያለው፣ መሬቱንም አየሩንም ሰማዩንም የመጠበቅ አቅምና ቁመና ያለው ተቋም ነው፣ ይህ በጣም የሚያሰጋን ጉዳይ አይደለም” ነው ያሉት፡፡ 
የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያውያን ሚሊሺያዎችና በሱዳን በደበኛ ጦር መካከል በተደረገው ግጭት ህይወታቸው ላለፈ ለሁለቱም አገር ዜጎች ማዘኑን ገልፆ ጉዳዩ በፍጥነት የሚጣራ ይሆናል ብሏል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ
      
      

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW