1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያና የሶማሊያ-ግብፅ ዉጥረት

ሐሙስ፣ መስከረም 2 2017

በቅርብ ዓመታት ሊቢያ፣የመን፣ ሱዳንና ፍልስጤም በቀጥታም በተዘዋዋሪም ከተነከሩበት እልቂት ከኪሳራ ባለፍ ምናሚኒት ያላገኙት የካይሮ ገዢዎች የሞቃዲሾ-አዲስ አበቦችን ጠብ ማራጋቡን ለኪሳራ ሽንፈታቸዉ ማበሻ ያደረጉት መስለዋል።የካይሮ መሪዎች ሶማሊያን ከማስታጠቅ፣አልፈዉ ጦራቸዉ ከሶማሊያ ብጤዉ ጋር ወታደራዊ ልምምድ እንዲያደርግም እያዘጋጁት ነዉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትርዒት አዲስ አበባ 2016።ከታጠቃቸዉ ሚሳዬሎች አንዱ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትርዒት አዲስ አበባ 2016።ከታጠቃቸዉ ሚሳዬሎች አንዱምስል Solomon Muche/DW

የኢትዮጵያና የሶማሊያ-ግብፅ ዉጥረት

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት እዉቅና ከሌላት ሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር የመግባቢያ ሥምምነት በመፈራረሟ ሰበብ ከሶማሊያና ሶማሊያን ከምትረዳዉ ግብፅ ጋር የገጠመችዉ ዉዝግብ ወደ ወታድ,ራዊ ፍጥ|ጫ እየናረ ነዉ።የሶማሊያና የግብፅ ወታደሮች የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ መስማማታቸዉ ተዘግቧል።የግብፅ ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አል ሲሲ ትናንት አንካራ-ቱርኩን ሲጎበኙ የሶማሊያን የግዛት አንድነት ለማስከበር እንደሚጥሩ አስታዉቀዋል።የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች በበኩላቸዉ ጦራቸዉ የሚሰነዘርበትን ጥቃት በሚገባ ለመምታት ዝግጁ መሆኑን አስታዉቀዋል።

ግብፅ ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ከጀመረችካለፈዉ ሳምንት ዉዲሕ የአዲስ አበባ፣ ሞቃዲሾ፣ካይሮ የቃላት እንኪያ ሰላቲያ፣ ተቃራኒ ፉከራ ቀረርቶዉም ንሯል።የዉጊያ ዝግጅቱም እየተቀለጣጠፈ ነዉ።የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ (ሞቃዲሾ) መሪዎች ከዉጪ የዲፕሎማሲ ከዉስጥ ሕዝባዊ ድጋፍ ለማግኘት እየባተሉ ነዉ።

በቅርብ ዓመታት ሊቢያ፣የመን፣ ሱዳንና ፍልስጤም በቀጥታም በተዘዋዋሪም ከተነከሩበት እልቂት ከኪሳራ ባለፍ ምናሚኒት ያላገኙት የካይሮ ገዢዎች የሞቃዲሾ-አዲስ አበቦችን ጠብ ማራጋቡን ለኪሳራ ሽንፈታቸዉ ማበሻ ያደረጉት መስለዋል።የካይሮ መሪዎች ሶማሊያን ከማስታጠቅ፣ሶማሊያ ዉስጥ  ጦር ለማሥፈር ከማቀድም አልፈዉ ጦራቸዉ ከሶማሊያ ብጤዉ ጋር ወታደራዊ ልምምድ እንዲያደርግም እያዘጋጁት ነዉ።

መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት የዓረቡ ዓለም «ጠንካራ ኃይል» የሚባለዉ የግብፅ ጦር በአፍሪቃ ሐገራት ጦር ድጋፍ ከሚንከላወሰዉ የሶማሊያ ጦር ጋር በያዝነዉ መስከረም ልምምድ ያደርጋል።

የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ የኢትዮ-ሶማሊያ መንግስታትን የምታደራድረዉን ቱርክንም ከጎናቸዉ አሰልፈዉ ከዉዝግብ፣ ዉጥረቱ ለመዶል ሞክረዋል።አል ሲሲ ትናንት አካራ ዉስጥ ከቱርኩ አቻቸዉ ሬሰፕ ጠይብ ኤርዶኻን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ «የሶማሊያ አንድነትና የግዛት ሉዓላዊነት መከበር እንዳለለባት» ተስማምተናል ብለዋል።ቱርኮች አለረጋገጡም።የኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ኮሎጅ ረዳት ፕሮፌሰርና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ እንደሚሉት ግን ቱርክ ካንዱ ወይ ከሌላዉ ትወግናለች ብለዉ አያምኑም።ምክንያትም አላቸዉ።

ከግራ ወደ ቀኝ የግብፅ ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አል ሲሲና የቱርኩ አቻቸዉ ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንምስል Turkish Presidency/Mustafa Kamaci/Anadolu/picture alliance

«የቱርክ መንግሥት በሁለቱ ሐገሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለዉ።ምናልባትም በአፍሪቃ ቀንድ ዉስጥ የቱርክን ያክል ከፍተኛ የሆነ የኤኮኖሚ፣የፖለቲካ ዘርፍ በታሪክም ጭምር ከፍተኛ ትስስር ያለዉ መንግስት ነዉ።»

ለሶማሊና ለግብፅ ፉከራና የዉጊያ ዝግጅት ከኢትዮጵያ የሚሰነዘረዉ አፀፋም ቀላል አይደለም።የኢትዮጵያ ጦር የምሥራቅ ዕዝ የተመሠረተበት 47ኛ ዓመት በዓል ዛሬ ጂጂጋ ዉስጥ በከፍተኛ ድግስና ወታደራዊ ሥርዓት ተከብሯል።በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ምክትላቸዉ፣ የልዩ ልዩ ኃይል አዛዦችና የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልልባለስልጣናት ተገኝተዋል።

ከመታሰቢያ ድግስነቱ ይልቅ ኃይል የማሳያ ትርዒት የመሰለዉ ዝግጅት ሲከበር የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሌትናንት ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እንዳሉት ጦራቸዉ የዉጪ ይሁን የዉስጥ ጠላቱን ለመምታት ዝግጁ ነዉ።

በሶማሊያ የአፍሪቃ ሕብረት ተልዕኮ አካል ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት በከፊልምስል AMISOM

«በሌላ ቦታ ላይም እንደዚሁ ግዳጁን በሚገባ እየፈፀመ ያለ ዕዝ ነዉ።ሥለዚሕ በዉስጥም ሆነ በዉጪ ለሚመጣዉ ጥቃት በሚገባ መምታት በሚያስችል ቁመናና ዝግጅነት ላይ ያለ ዕዝ መሆኑን ነዉ መግለፅ የሚቻለዉ።»

ጄኔራሉ እንዳሉት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በተደረገ ሥምምነት መሠረት ከሶማሊያ የወጣዉ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ከነ ሙሉ ትጥቁ ከሶማሊያ ጋር በሚዋሰነዉ  ምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዛት ሠፍሯል።የኢትዮጵያና የሶማሊያ-ግብፅን ጠብን ለማርገብ ጁቡቲ ባለፈዉ ሳምንት ሥለአቀረበችዉ የአማራጭ ወደብ ፍቃድ ከአዲስ አበባ፣ ከሞቃዲሾም ሆነ ከካይሮ የተሰማ ነገር የለም።ዉጥረቱ ግን በርግጥ ንሯል።ቀጥታ ዉጊያ ማስከተሉን ግን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW