1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያን የስኳር ፋብሪካዎች እየፈተነ ያለው የፀጥታ ችግር

ሰኞ፣ መጋቢት 18 2015

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኦሮሚያ ያሉትን የስኳር አምራች ፋብሪካዎችን እየፈተነ የሚገኘው የፀጥታ ችግር በምርቱ የገበያ ላይ እጥረት ካስከተሉ አበይት ምክኒያቶች ናቸዉ፡፡ በዚሁ ችግር በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶበት ሁለት ጊዜ ስራ ያቆመዉ የአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግሩ መፈተኑ ይጠቀሳል፡፡

Äthiopien Amhara | Zuckerfabrik
ምስል Xinhua/picture alliance

በኢትዮጵያ እንደ ሌላው የቤት ውስጥ መሰረታዊ የፍጆታ ግብዓቶች አሁንም አልቀመስ ባለው የዋጋ ንረቱ ከግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ አንዱ የስኳር ምርት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ስኳር ከሚያመርቱ ፋብሪካዎች የፀጥታ ችግርን ዋነኛ የማምረት ሂደቱ ተግዳሮት አድርገው የሚያነሱ አሉ፡፡

የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚያስከትለው የማሽኖች ትገና መጓተት እና የአገዳ ማዳበሪያ እጥረቶችም እንደ ሌላውና ትልቅ ችግር ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንደስትሪ ግሩፕ መረጃ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ባለው የፀጥታ እና ሌሎችም ተግዳሮቶች የስኳር ፋብሪካዎቹ ማምረት ከሚችሉት ግማሹን ያህል ብቻ እያመሰረቱ መሆኑን ያመለክታል፡፡

“አንድ ኪሎ ግራም ስኳር በሸማች ደረጃ 60 ብር ነው የሚሸጠው፡፡ ሱቅ ደግሞ ከዚያ እጥፍ ይጨምራል፡፡ ገዝቶ መጠቀም ከባድ እየሆነ ካሉ ምርቶች አንዱ ሆኗል አሁን ስኳር፡፡” በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ የምግብ ምርቶች እጥረት፤ በተለይም በስኳር ዋጋ ጭማሪ እና በምርቱ ከገቢያ መጥፋትን በማስመልከት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ያጋሩን አስተያየት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኦሮሚያ ውስጥ ያሉትን የስኳር አምራች ፋብሪካዎችን እየፈተነ የሚገኘው የፀጥታ ችግር በምርቱ የገበያ ላይ እጥረት ካስከተሉ አበይት ምክኒያቶች ይባልለታል፡፡ በዚሁ ችግር በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶበት ሁለቴ ምርት ያቆመው በምዕራብ ኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ እና ቡኖ-በደሌ ዞኖች አዋሳን አከባቢ ከመዲናዋ አዲስ አበባ 395 ኪ.ሜ. ርቆ የሚገኘው የአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግሩ ከተፈተኑት ይጠቀሳል፡፡ አሁን ላይ ግን ይህ ፋብሪካ ወደ ምርት መመለሱን ስራ አስከያጁ አቶ ሚጀና ቢቂላ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ “የፀጥታ ችግሩ ያጋጠመን ነሃሴ እና ጥቅምት ላይ ነበር፡፡ አሁን ግን ሰራተኛም ተረጋግቶ የጥገና ስራም ተከናውኖ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ እነዚህ ወራት የምርት ጊዜ ሳይሆን የጥገና ወራት ነበሩ፡፡ በዚያም የጥገና ጊዜ በመጓተቱ ቆይቶ ነው ፋብሪካው ወደ ስራ የተመለሰው፡፡ በወቅቱም ታጣቂዎች በፋብሪካው ንብረት ላይ አነጣጥረው በፈፀሙት ጥቃት የደረሰውን ጉዳት በብር ባንተንምንም ከሞተር ሳይክል እስከ ኢሳት አደጋ ማጥፊያ ተሸከርካሪ፣ ከባድ ማሽኖች፣ አምቡላንስ፣ ዶዘር፣ ስካቫተር፣ ሲኖትራክ እና ቀላል ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ 17 የሚሆኑ ማሽኖች ናቸው በቃጠሎ የወደሙት፡፡ የፀጥታ ችግሩ የጥገና ጊዜውን ከማራዘሙ ሌላ ዋናው ፋብሪካው ላይ ግን ያደረሰው ጉዳት ስላልነበረ ወደ ምርት ተመልሷል” ብለዋልም፡፡ 

ከፀጥታ ችግሩ በተጨማሪ በተለያዩ ተግዳሮቶች ቀድሞውኑም ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ የማምረት ደረጃ ላይ አለመድረሱን የሚያነሱት ስራ አስከያጁ፤ “ፋብሪካው ቀድሞውኑም ከመስኖ መሰረተ ልማት ጉድለትና ከሃይል እጥረት የተነሳ ወደ ሙሉ አቅሙ ምርት አልገባም ነበር፡፡ የተወሰነ የአገዳ መሬት ስለሆ ያለው በዚያው ስለሆነ የሚያመርተው ያን ያህል የተስተጓጎለ የምርት ጊዜ የለም፡፡ ፀጥታውም አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ነው ባይባልም የተሸለ ነው” ይላሉ፡፡

ስድስት ሺህ ቶን የሸንኮራ አገዳን በቀን የመፍጨት አቅም ያለው የአርጆ ዴዴደሳ ስኳር ፋብሪካ በዝናብ ወቅት ብቻ የሚለማውን ሸንኮራ አገዳ በመጠቀም ነው በውስን አቅም ብቻ የሚሰራው፡፡ በሙሉ አቅሙ ለማምረት ከ13 ሺህ ሄክታር ያላነሰ የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚፈልገው ፋብሪካው አሁን ላይ በዚህ ዓመት ወደ 1 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ሸንኮራ አገዳ በማልማት 50 ሺህ ኩንታል ስኳር ብቻ ያመርታል፡፡

ከአርጆ ዴዴሳ በተጨማሪ በፊንጫ እና በመታሃራ ስኳር ፋብሪካዎችም የምርት ሂደቱን ያስተጓጎለ የፀጥታ ችግር ማጋጠሙን የነገሩን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንደስትሪ ግሩፕ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ ኢንደስትሪውን በተለይም ላለፉት ሁለት ዓመታት የፈተነው የፀጥታ ችግር ቀላል ጉዳት አላደረሰም ይላሉ፡፡ “ከፀጥታ ችግሩ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ዘርፉ በሚፈለገው መጠን ውጤታማ እንዳይሆን ፈተና ደቅኗል” ይላሉም፡፡

ችግሮቹ ፋብሪካዎቹ ከአቅማቸው ከግማሽ በላይ ባልሆነ ደረጃ ብቻ እንዲያመርቱም ማድረጉን በመጠቆም፤ በቀጣይ ዓመታት ግን ፋብሪካዎቹን ያጋጠመውን ፈተና በመቅረፍ ወደ ተሻለ ምርት ለመግባት ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡ “ በዘንድሮ ዓመት በፋብሪካዎቹ 2 ሚሊየነን 2 መቶ 70 ሺህ ኩንታል ስኳር ነው ለማምረት የታቀደው፡፡ ይህ ደግሞ ከሌላው ጊዜ አንጻር እንኳ ሲሰላ በእጥፍ ያነሰ ነው፡፡ ከአራት ሚሊየን በላይ ነበር ከዚህ በፊት ሲታቀድ የነበረው፡፡ እንደ ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ያሉ ደግሞ በአገዳ አቅራቢ ማህበራት ስራ ማቆም ምክኒት ማምረት ላይ አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁሉ መፍትሄ እያገኙ ስለሆነ በቀጣይ የተሻለ ነገር እንጠብቃለን፡፡” ከነዚህ በተጨማሪ እንደጣና በለስ ያሉ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካም ሰኔ 2013 ዓ.ም. ብመረቅም ወደ ምርት እየገባ ያለው ገና አሁን በቅርቡ ነው ተብሏል፡፡

 

ሥዩም ጌቱ 

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW