1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አመቺነት ኹኔታ "ፈታኝ ነው"፦ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ መስከረም 20 2018

አሜሪካ መንግሥት ሰሞኑን ባወጣው መረጃ "የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኹኔታ "ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ ነው" ሲል አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞች የመንገድና የዳርቻ ወይም የኮሪደር ልማት የባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት "ገድቧል" ሲል ነው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሪፖርቱ ያመለከተው።

USA Washington 2023 | Logo des US-Außenministeriums
ምስል፦ Celal Gunes/AA/picture alliance

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመን ኹኔታ ያወጣው መግለጫ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አመቺነት ኹኔታ የተመለከተው የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት

የአሜሪካ መንግሥት ሰሞኑን ይዞት በወጣው መረጃ "የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኹኔታ "ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ ነው" ሲል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞች የመንገድና የዳርቻ ወይም የኮሪደር ልማት የባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት "ገድቧል" ሲል ነው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሪፖርቱ ያመለከተው።

ዝርዝር ሪፖርቱ "የውጭ ይዞታዎችን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና የንግድ ድርጅቶች ንብረታቸው ያለ በቂ ማስጠንቀቂ መፍረሱን ተከትሎ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ይጠቅሳል።

ግጭት በሚካሄድባቸው አማራና ኦሮሚያ ክልሎች የመንቀሳቀስ ሁኔታ ገደብ መኖሩን የጠቀሰው ይህ ሪፖርት ባለሥልጣናት ወይም ታጣቂ ቡድኖች በተደጋጋሚ የግል ንብረቶችን እንደሚነጥቁ፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች በቂ ጥበቃ እያገኙ እንዳልሆነ ጭምር አመልካቾችን ጠቅሷል።

ለዚህ ድምዳሜ መነሻ የተባሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባወጣው የሀገራት ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ኹኔታ መግለጫ የኢትዮጵያን ኹኔታ "ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ" ያለው ሲሆን፣ በምክንያትነት ካስቀመጣቸው ጭብጦች መካከል የውጭ ይዞታዎችን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ያላቸው ነዋሪዎች እና ንግዶች በትንሽ ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ ንብረታቸውን ያጡበት መንገድ ወይም የኮሪደር ልማት አንዱ ነው። ይህም እንደ ሪፖርቱ የባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የማረግ ፍላጎት "ገድቧል"።

በዚህ የልማት ሥራ ምክንያት የደረሱ "መፈናቀሎች የተወሰኑት ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ወይም መሣሪያ ተደቅኖ" ስለመፈፀሙ የጠቀሰው ሪፖርቱ ይህም የባለሃብቶችን የማልማት ፍላጎት በጉልህ ገድቧል ይላል።

የልማት ሥራው "ንግድን የማይቻል" ያደረገበት አጋጣሚ መከሰቱን የሚያትተው ይህ ዘለግ ያለ ጽሑፍ "የንግድ ሥራዎች ከሥራ እንዲወጡ" ማስገደዱንም ይጠቅሳል። ይህም የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን "ለድንገተኛ እና ከፍተኛ የግብር ግመታ" እንዳጋለጣቸው ይዘረዝራል።

"የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከሕግ በተቃረነ መልኩ የግንባታ ተቋራጮች ለጨረታ አልቀረቡም ሲልም ይልቅ "ከባለሥልጣናት ጋር ቅርበት ወይም ግንኙነት ላላቸው ድርጅቶች ተሰጥተዋል" በማለት ለድምዳሜው ተጨማሪ ያለውን "የሙስና ድርጊት" አስፍሯል።

በዚህ የልማት ሥራ ምክንያት የደረሱ "መፈናቀሎች የተወሰኑት ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ወይም መሣሪያ ተደቅኖ" ስለመፈፀሙ የጠቀሰው ሪፖርቱ ይህም የባለሃብቶችን የማልማት ፍላጎት በጉልህ ገድቧል ይላል።ምስል፦ Solomon Muche/DW

በጉዳዩ ላይ የባለሙያ አስተያየት

ለመሆኑ አንድ ሀገር የሌላን ሀገር የኢንቨስትመንት ምቹም ይሁን አስቸጋሪነት እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ የሚጠቀማቸው መመዘኛ መፈርቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን የጠየናቸው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

"የመጀመርያው የሰላም ጠቋሚ - ሰላምና ፀጥታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ግልጽነት እና ተጠያቂነት። ለምሳሌ አንድ ምርት ወይም አገልግሎት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ምን ያህል ዋስትና አለው? የሚለው ነገር ይታያል። ዋስትና ብቻም ሳይሆን ደግሞ ለዚያ ለንብረትህ ሕጋዊ ጥበቃ የሚያደርግ የመንግሥት የአሠራር ሥርዓት ጥብቀቱ ምን ያህል ነው? የሚለውም ነገር ይጠናል"።

በክልሎች ውስጥ ያሉ ግጭቶች የፈጠሩት ተጨማሪ ችግር

የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሪፖርት በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲኖር ከማድረጋቸው ባሻገር "የመንግሥትን ጣልቃ የመግባት አቅም መገደባቸውን" ጭምር እንደሚያሳዩ አመልክቷል። በትግራይ ክልል ያለው ዳግም "ወደ ግጭት የመመለስ ሥጋት" እና "እየጨመረ የመጣ" ያለው የክልሉ የፖለቲካ ውጥረት የኢትዮጵያን ለአሜሪካ የኢንቨትመንት ምቹ አለመሆን ተጨማሪ ማሳያ አድርጎ አቅርቧል።

አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ "የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ሪፖርት ለእያንዳንዱ ጉዳይ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል" ብለዋል። አክለውም "ጉዳዩ ከፍተና ተጽዕኖ የሚኖረው በመሆኑ፣ አስፈላጊ ከሆነም መግለጫ ሊሰጥበት ይገባል" ሲሉ ጠቅሰዋል። በሪፖርቱ "እውነት የሆነም እውነታም የሌለው መረጃ አለ" ያሉት ባለሙያው ያም ሆነ ይህ ለውጭ አልሚዎች "ጥሩ ምልከታ አይሰጥም። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አልሚዎች - ኢንቨስተሮች ከአሜሪካ ይልቅ የሌሎች ሀገሮች ቢሆኑም" ሲሉም ገልፀዋል። አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በበኩላቸው መፍትሔ ያሉትን ለዶቼ ቬለ አጋርተዋል። ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ምንጊዜም የኢንቨስትመንት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም።

"በሕብረተሰብ እና በመንግሥት መካከል ያለ የመተማመን ደረጃ ሁልጊዜ መታየት ያለበት ግዙፍ የፖለቲካ ኢኬኖሚ አጀንዳ ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ መንግሥታት በጥሩ ኹኔታ እየመሩ እንደሆነ ነው የሚያስቡት ግን ደግሞ ሕብረተሰብ ዝም ስላለ ችግር የለም ማለት እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል።"

የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ ደካማ ያለው የንብረት መብት መኖር፣ በባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመን እና በትይዩ ገበያ መካከል እንደገና እየተስተዋለ ነው ያለው የዋጋ ክፍተት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከልክ ያለፈ እና አጠራጣሪ ግብር እና ሌሎችም በኢትዮጵያ ላይ ላቀረበው ዘገባ ድምዳሜ ተጨማሪ ምክንያት ናቸው ይላል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ 

ነጋሽ መሐመድ 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW