1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ውጥረት ያባባሰው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ

እሑድ፣ የካቲት 22 2018

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ይፋ የተደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ውጥረት አባብሶታል። ዶይቼ ቬለ የሕግ ባለሙያዎቹን አቶ አምደገብርኤል አድማሱ እና አቶ አወት ልጃለም፤ ከሳልሳይ ወያነ ትግራይ አቶ ኪሮስ ኃይለሥላሴ፣ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አቶ ዳምጠው ተሰማን በመጋበዝ በጉዳዩ ላይ ውይይት አካሒዷል።

የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሎጎ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስት ምርጫ ክልሎች “ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ” የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን አሳውቋል።ምስል፦ Ethiopia House of Federation

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ውጥረት ያባባሰው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ

This browser does not support the audio element.

መቐለ፣ አክሱም እና ሽረን ጨምሮ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስት የምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ የሚቃወሙ ሰልፎች ባለፈው አርብ የካቲት 20 ቀን 2018 ተካሒደዋል። 

በመቐለ በተካሔደው የተቃውሞ ሰልፍ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ታደሰ ወረደ፣ የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ባደረጉት ንግግር በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ይፋ የተደረገውን ውሳኔ በጽኑ ኮንነው ነበር።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁመራ፣ አዲረመፅ፣ ኮረም፣ ጠለምት እና ራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች “ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ” የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን ያሳወቀው የካቲት 16 ቀን 2018 ነው። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን ያሳወቀው ጥር 25 ቀን 2018 እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ያሠራጨው ደብዳቤ ይጠቁማል። በደብዳቤው መሠረት ውሳኔው የሚመለከተው “በትግራይ እና በአማራ ክልላዊ መንግሥታት መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩ” የተባሉ አምስት የምርጫ ክልሎችን ይሆናል።

ውሳኔውን ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች አጥብቀው ተቃውመዋል። 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በበኩላቸው ውሳኔውን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔው “ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ” የካቲት 19 ቀን 2018 ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔው ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ የሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካሪ በሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ካቀረበው አቤቱታ በኋላ ነው።  

ዶይቼ ቬለ አራት ባለሙያዎች በመጋበዝ በውሳኔውን አንድምታ እና ሕጋዊነት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሒዷል። በውይይቱ የሕግ ባለሙያዎቹ አቶ አምደገብርኤል አድማሱ እና አቶ አወት ልጃለም፤ ከሳልሳይ ወያነ ትግራይ አቶ ኪሮስ ኃይለ ሥላሴ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አቶ ዳምጠው ተሰማ ተሳትፈዋል። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW