1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዉያን የድረሱልን ጥሪ ከሳዉዲ አረቢያ እስር ቤት

ማክሰኞ፣ ጥር 30 2009

ሳዉዲ አረብያ የመን ድንበር አዋሳኝ ላይ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ወደ ሃገራቸዉ የሚመለሱበት መንገድ እንዲፈለግ እየተማፀኑ ነዉ። ጂዛን በተባለች የሳዉዲ አረብያ ከተማ ዳርቻ ላይ ባለ እስር ቤት ዉስጥ የሚገኙት እነዚሁ የሳውዲ መንግሥት ሕገ-ወጥ የሚላቸው ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በቁጥር ከአምስት ሺህ እንደሚበልጡ ተናግረዋል።

Symbolbild Gefangenschaft Gefängnis
ምስል picture-alliance / dpa

M M T/ Illegale äthiopische Flüchtlinge in Jazan_Saudi - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

በሪያድ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ ጂዛን ከተማ በሚገኘዉ እስር ቤት ያሉት ኢትዮጵያዉያን በወንጀል የታሰሩ በመሆኑ ደሕንነታቸዉ እንዲጠበቅና እስራቸዉ እንዲቀል ለማድረግ እና ወደ ሃገር ቤት እንዲላኩም ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጾአል።  

ሳዉዲ አረብያ ጂዛን ከተማ ከሚገኘዉ እስር ቤት ወደ ጣብያችን መልክት ያደረሱንን ሕገ-ወጥ ተብለዉ የተያዙ እስረኞችን ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት ቀናቶች ወስደዉብናል። ምክንያቱ ከቀትር በፊት ብቻ ስልኩን የሚያገኙት እዛዉ ታስረዉ ከሚገኙት ሱዳናዉያን ሶርያዉያን፤ ጋናውያን አልያም የመናዉያን በመሆኑ ነዉ ። ከመካከላቸው ያገኘነዉ የመጀመርያዉ ሰዉ ብርሃን ይባላል፤ ባላወቅነዉ ነገር ነዉ ለእስር የተዳረግነዉ ወደ ሃገራችን አስመልሱን ሲል ይማፀናል፤ 

ብርሃን ይህን ካለ በኋላ ስልኩን ለሌላ ባልንጀራ ሰጠዉ፤ በእስር በትንሹ 4000 ሺህ ኢትዮጵያዉያን እንሆናለን ከዚያ መካከል 300 የሚሆኑት ሴቶች ናቸዉ ይላል፤  

«ኢትዮጵያዊዉ የሚሄድበት መንገድ ብዙ ነዉ። ኑሮን ለማሻሻል ነበር እዚህ ከገባን በኋላ ደግሞ አልተሳካልንም። ድንበር ላይ ያላሰብነዉን ነገር አሸከሙን እና ይዘን ገባን በመጨረሻ ወታደሮች ያዙን ቢያንስ ቢያንስ አራት ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን እስር ቤቱ ዉስጥ ይገኛሉ።» ጂዛን እንዴት ልትገቡ ቻላችሁ ለሚለዉ ጥያቄ በመቀጠል፤

«ጂዛን የገባነዉማ በጅቡቲ አድርገን በየመን አድርገን ነዉ። ድንበር ላይ የመኖቹ እፅ አሸክመዉን እና ምን እንደሆን አናዉቀዉም። ወታደሮቹ ደግሞ ይዘዉ ወደ እስር ቤት አስገቡን። የሚሲዙን እፅ ቴምር የሚመስል ነዉ እናም በአንድ እጃችን ቴምር ያሲዙናል አስር እንደቴምር እፅ ያሲዙናል። ያዉ እና ቴምር ነዉ ብለን ስንገባ ወታደሮቹ እጽ መሆኑን ያዉቃሉ፤ ወድያዉ ይይዙናል። ከኛዉ ጋር አንድ ሦስት መቶ አራት መቶ የሚሆኑ ሴቶች አሉ ብዬ እገምታለሁ»   

በእስር ቤት ስንት ጊዜ ሆንዋችኋል? ለሚለዉጥያቄ በመቀጠል « አምስት ዓመት የሞላዉ አለ ያለፍርድ ሰባት ስምንት ዓመት የተቀመጠ ሁሉ አለ። አብዛኛዉ ወደኛ አካባቢ ያለዉ ደግሞ ሁለት ሦስት ዓመት ሆኖታል»

ምስል DW

አሁን ጥያቅያችሁ ፍላጎታችሁ ምንድን ነዉ?«የናፈቀን የአገራችን መሬት ነዉ የፈረዱብን መልሱ ማለት አንችልም ግን በአገራችን ምንታሰር የተሻለ ነበር።  በማናዉቀዉ ነገር ሃያ፤ ሃያ አምስት፤ ሠላሳ ዓመት ነዉ የሚፈርዱብን። አብዛኛዉ ታሳሪ እዚህ ያለዉ ከ 18 ዓመት በታች ነዉ።» ከኢትዮጵያ ኤምባሲን ለማግኘት ጥረት አላደረጋችሁም?« አይ ነገሩ ከኤምባሲዉ ጋር ዉኃ ቅዳ ዉኃ መልስ ነዉ ምንም የሚለዉጥልን ነገር የለም። ከአራት ቀናት በፊት መጥተዉ ነበር አነጋገሩን ምንም የሚቀይሩልን ነገር የለም፤ አይዞአችሁ ብቻ ነዉ በርግጥ አይዞአችሁም ሞራል ነዉ»  

የታሰሩት ኢትዮጵያዉያን በርግጥ እንደተባለዉ ብዙ ናቸው ያሉን በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቆንስላና የዲያስፖራ ተሳትፎና የቆንስላ ጉዳዮች ዘርፍ ሃላፊ ቆንስላ ጀነራል ፈይሰል አልይ ኢትዮጵያዉያኑን ሕገ-ወጥ ተግባር እንዲፈፅሙ ያስገደዳቸዉን ማግኘቱ ከባድ ነዉ ብለዋል። «ኢትዮጵያዉያኑ ታሰሩ በተባለዉ ቦታ ክቡር አምባሳደር አሚን ብዱር ቃድር የኛ አምባሳደር ሄደዉ ጎብኝተዋል። ቆንስላ ጀነራሉ አምባሳደር ዉብሸት ደምሴም በተለያየ ጊዜ ሄደዉ አይተዋቸዋል። ግን የተፈረደባቸዉ የእስር ጊዜያቸዉን እያገለገሉ ናቸዉና በኛ ደረጃ መብታቸዉ ተጠብቆ፤ እና ሳይጣስ የሚጎዱበት ሁኔታ እንዳይኖር ነዉ የኛ ከስዑድ አረብያ መንግሥት አካላት ጋር እየሰራን ያለነዉ» የኢትዮጵያዉያኑ ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው በሁለቱ መንግሥታት ውይይት በመሆኑ ኤምባሲው በዚህ ረገድ  እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ቆንስላ ጀነራል ሕገ ወጥ ሆኖ ከአንድ ሃገር በተለይ የሚኬድበት መንገድ ችግሮች ይደርሳሉ። በነዚህ መንገዶችም የተለያዩ ሕገ-ወጥ ቡድኖች ይኖራሉ። እነዚህ ደግሞ በየትኛዉም መንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ አይደሉም ስለዚህ ከኢትዮጵያ ተነስተዉ በዚህ መንገድ ሲሄዱ የተለያየ ችግር እንደሚደርስባቸዉ፤ የታወቀ ነዉ እንደሚታወቀዉ። ስደተኛ ሲኮን ለተለያየ ጥቃት መጋለጥም አለ። በኛ በኩል ዞሮ ዞሮ ስደተኞቹ እዚህ አገር ጥፋት ካጠፉ የሃገሪቱ ሕግ በሚፈቅደዉ መሰረት ጥፋታቸዉን ከተቀበሉ በኋላ በኛ በኩል እንደመንግሥት ማድረግ የምንችለዉ እነዚህ ረጅም ጊዜ እንዳይታሰሩ ለትዉልድ ሃገራቸዉ እንዲበቁ የሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የማጠናከር ጉዳይ ነዉ። አንዱ ማዕቀፍ የእስረኛ ልዉዉጥ ነዉ በሥራ ላይ ያለ ጉዳይ ነዉ»  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW