1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች መከራ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 2016

በኢትዮጵያ ሞያሌ በኩል ዛሬ ወደ አገራቸው የተመለሱት ከሦስት መቶ በላይ ፍልሰተኞች ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት በእሥር መቆየታቸውን በማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሃድያ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የፍልሰተኞች ባለሙያ አቶ አወል ጀማል ገልጸዋል

በቅርቡ ከ300 በላይ ስደተኞች በሞያሌ ኢትዮጵያ በኩል ከስደት ተመልሰዋል
ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመጓዝ ሲሞክሩ በተለያዩ ሐገራት ተይጠዉ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ስደተኞችምስል privat

የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች መከራ

This browser does not support the audio element.

 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ነዋሪ የሆኑት ወጣት ታደሰ ተመስገን እና ብሩክ ግርማ  በሞያሌ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ከዓመት በፊት ጉዞ መጀመራቸውን  ይናገራሉ ፡፡ ይሁንእንጂ እነታደሰ የተስፋይቱ ምድር ብለው ጉዞ የጀመሩባት ደቡብ አፍሪካ እንዳሰቡት መድረስ አልቻሉም ፡፡ ይልቁንም በተሽከርካሪ ኮንቴይነር ውስጥ ተደብቀው ከኬኒያ ሞምባሳ ወደ ታንዛኒያ በበረሃ በመጓዝ ላይ ሳሉ  አየር ለመውሰድ በወጡበት በአገሬው ፖሊሶች ተይዘው ለእሥር መዳረጋቸውን ተናግረዋል   ፡፡

በስደት ጉዞና በእሥር ቆይታቸው አስቸጋሪ ፈተናዎችን ማለፋቸውን የሚናገሩት ከፍልሰት ተመላሾቹ ታደሰ  እና ቡሩክ “ በርካቶች ህይወታቸው ሲያጡ ተመልክተናል ፡፡ አብዛኞቹ የሞት አደጋ የሚጋጥማቸው በጉዞ ላይ ሲሆን በበረሃ እስርቤቶች ውስጥ በረሃብና በበሽታ የሞቱ ሰዎችንም አይተናል  “ ብለዋል ፡፡

ቅልቅል

በኢትዮጵያ ሞያሌበኩል ዛሬ ወደ አገራቸው የተመለሱት ከሦስት መቶ በላይ ፍልሰተኞች ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት በእሥር መቆየታቸውን  በማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሃድያ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የፍልሰተኞች ባለሙያ አቶ አወል ጀማል ገልጸዋል ፡፡ መንግሥት ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ አገር የገቡት ተመላሾች ወጣቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ባለሙያው ” ወጣቶቹ ወደ አገር ከገቡ በኋላ መልሰው ወደ ሌላ የፍልሰት ጉዞ እንዳይገቡ በጥንቃቄ የማጓጓዝ ሥራ ተከናውኗል ፡፡ አሁን የሥነ ልቦና እገዛ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ይደረጋል “ ብለዋል ፡፡

የፍልሰተኞች መዳረሻዎች  

ዶቼ ቬለ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረገው ህገ ወጥ የፍልሰት ጉዞና በተመላሽ ዜጎች ዙሪያ  የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሥራ ሃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ ተካሄዶ በነበረው 37ኛው የአፍርካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን  የኢትዮጵያና የኬኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከተፈራረሟቸው የትብብር ማዕቀፎች አንዱ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ በጋራ መሥራት የሚለው ይገኝበታል፡፡

ዓለምአቀፉ የስደተኞች ልማትና እኩልነት የተባለ ድርጅት በቅርቡ ባደረገው አንድ ጥናት አሁን ላይ ከ3 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን ከአገር በመውጣት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ ኑሯቸውን እየገፉ እንደሚገኙ ይጠቁማል ፡፡ በተለይም ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሰው ጥናቱ ወጣት ሴቶች በመካከለኛው ምሥራቅ ወጣት ወንዶች ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ዋነኛ የፍልሰት መዳረሻዎች መሆናቸውን በጥናቱ ጠቅሷል  ፡፡

ከተለያዩ የደቡባዊ አፍሪቃ ሐገራት ወደ ሐገራቸዉ ኢትዮጵያ ለተመለሱት ስደተኞች መጠነኛ ርዳታ ተደርጎላቸዋልምስል privat

 ህገ ወጥ ፍልሰትን የመከላከሉ ተግዳሮት

በማዕከላዊኢትዮጵያክልለ የሚገኙት የሃድያ እና የከምባታ ዞኖች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው ፍልሰት በመነሻነት አንደሚጠቀሱ የተናገሩት የሃድያ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የፍልሰተኞች ባለሙያ አቶ አወል ጀማል  “ አብዛኞቹ ሥራና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው እየፈለሱ የሚገኙት ፡፡ ጥቂቶች ወደ ስደት መዳረሻቸው ቢገቡም ያዛኑ ያህል  ለሞት ፣ ለአካል ጉዳት እና ለሥቃይ እየተዳረጉ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም ፡፡በእኛ በኩል የስደትን አስከፊነት በማስተማር ግንዛቤ ለመፍጠር እየሞከርን ነው፡፡ በእርግጥ ማስተማሩ አንድ ነጠላ መፍትሄ ቢሆንም ሂደቱ በሥራ ዕድል አቅርቦት ካልተደገፈ ውጤታማ የመሆን ዕድሉ ጠባብ  ሊሆን ይችላል “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐነስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW