1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የኢትዮጵያውያን መተግበሪያዎች በቀጥታ በጉግል ፕሌይ ሊካተቱ ነው

ረቡዕ፣ ኅዳር 4 2017

የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው ጎግል ፕሌይ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጅ አበልፃጊዎችን በቀጥታ መቀበል ጀምሯል። ይህም ኢትዮጵያውያን የሰሯቸውን መተግበሪያዎች ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል ተብሏል። የውጭ ምንዛሬን ለመጠቀም የሚያስችል የክፍያ አማራጭ በሀገሪቱ አለመኖሩ ግን በችግርነት ይነሳል።

Logo Google Play Store
ምስል Harun A–zalp/AA/picture alliance

የኢትዮጵያውያን መተግበሪያዎች በቀጥታ በጉግል ፕሌይ ሊካተቱ ነው

This browser does not support the audio element.


በኢትዮጵያ የዲጅታል ቴክኖሎጅ ፈጠራ እያደገ መምጣቱ ይነገራል።ያም ሆኖ  የፈጠራ ባለሙያዎች  በዓለም አቀፍ ደረጃ ስራቸውን ማስተዋወቅ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ገብቶ መወዳደር ፈታኝ መሆኑ  ተደጋግሞ የሚነሳ ችግር ነው።እንደ ጎግል ፕሌይ ያሉ ዓለም አቀፍ ዲጅታል  መድረኮች እና ዲጅታል የክፍያ አማራጮች ለኢትዮጵያውያን ተደራሽ አለመሆን ደግሞ ለችግሩ አንድ ምክንያት ሆኖ ይቀርባል። የበርካታ ፈጠራዎች ባለቤት የሆነው የአይቬክስ ቴክኖሎጂ እና ፕሮሞሽን መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ  ወጣት ኢዘዲን ካሚል ችግሩ ከገጠማቸው የፈጠራ ባለሙያዎች አንዱ ነው።

«ከዚህ በፊትመተግበሪያ ካበለፀግን በኋላ በዓለም ዙሪያ ሰዎች ከጎግል ፕሌይ ድህንነቱ በተጠበቀ መልኩ አውርደው እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ኢትዮጵያ [ስላልተካተተች} ዩኤስ አሜሪካ እና ሌሎች የጎግል ፕሌይ [የሚቀበላቸው} ሀገሮች ስልክ ቅጥር ያስፈልግ ነበረ።ያ ብቻ ሳይሆን «ፔይመንት»የሚከፈልበት መንገድም ከዚያ ጋር የተያያዘ መሆን ነበረበት።ከዚያ ጋር በተያያዘ እኛ ብዙ ውጭ ሀገር ገደኞች ስለነበሩን እነሱ ከፍተውልን «አፕሌኬሽን ፐብሊሽ» አድርገናል።ከዚያ በኋላ ግን ችግር ሲፈጠር እነዚያን መተግበሪያዎች ባለቤትነታቸው የኛ ሳይሆን አካውንት የከፈቱልን ሰዎች ነው።በድርጅትም መክፈት አንችልም።ብዙ ቻሌንጆች ነበሩ።» በማለት ችግሩን ያስረዳል።

ኢዘዲን ካሚል፤ የበርካታ ፈጠራዎች ባለቤት እና የአይቬክስ ቴክኖሎጂ እና ፕሮሞሽን መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ  ምስል Ezedin Kamil

በዚህ ሁኔታ ኢዘዲን ከብዙ ውጣውረድ ጋር እየታገለ ወደ 14 መተግበሪያዎችን በጎግል ፕሌይ ይፋ አድርጓል።ነገር ግን እንደ እሱ በውጭ ሀገር ዘመድ እና ወዳጅ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የመተግበሪያ አልሚዎች  የጎግል  ፕሌይ አካውንት የመክፈት ዕድል ስለሌላቸው ከፈጠራ ስራዎቻቸው ወደ ኋላ ማለታቸውን ገልጿል።

ኢትዮጵያውያን አልሚዎች የጎግል ፕሌይ አካውንት ይገዙ ነበር 

የቢብሎኪ መተግበሪያ እና የጃሚ  ዲጅታል መድረክ መስራች ናታን ዳምጠው በጎርጎሪያኑ 2016 ዓ/ም ቢብሎኪን በጎግል ፕሌይ ለተጠቃሚ ተደራሽ ማድረጉን ያስታውሳል። ነገር ግን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይህ ዕድል በመዘጋቱ ችግር ማጋጠሙን ገልጿል።ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያውያን የመተግበሪያ አበልፃጊዎች የጎግል ፕሌይ አገልግሎት በሚፈቀድባቸው ሀገራት ከሚኖሩ  ሰዎች እስከ አስራ አምስት ሺ ብር በማውጣት አካውንት መግዛት የተለመደ ነበር ይላል።ይህም አዲስ መተግበሪያ ይፋ ለማድረግ ይከብድ እንደነበር ያስረዳል።ከውሂብ መረጃ ጋር የተያያዘ ችግርም ይፈጥራል።  
«ሁለተኛው ችግር ከ«ዴታ» ጋር የተገኛኘ ነው።ጎግል ፕሌይ ስቶሮች በየሀገሩ ይለያያሉ።ለምሳሌ በዩኤስ ገበያ ጎግል ፕሌይ ላይ ይፋ የተደረገ የሚገለግለው እና የሚተዋወቀው የሚመጣለት ዩ ኤስ ውስጥ ለሚኖር ሰው ነው።ማለት ነው።አውሮፓ ሌሎችም ይለያያሉ።ስለዚህ እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የጎግል« ስቶር» አልነበረም ማለት ለኢትዮጵያ የተሰሩ መተግበሪያዎች በስማቸው ተፈልገው ነው የሚገኙት እንጅ፤እንደ ሌሎቹ ሀገሮች ፊትለፊት አይመጣም።ይህም ለትክከኛው ሰው እንዳይደርስ ያደርጋል።»በማለት አብራርቷል።

ናታን ዳምጠው፤የቢብሎኪ እና የጃሚ መተግበሪያዎች መስራችምስል Privat

ጎግል ፕሌይ የኢትዮጵያውያን ስራ መቀበል መጀመሩ

ከሰሞኑ ግን ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ጥሩ ዜና ተሰምቷል። የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አደረኩት ባለው ጥረት ጎግል ፕሌይ (Google Play) ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጅ አበልፃጊዎችን መቀበል መጀመሩን አስታውቋል። 
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን  እንደገለፁት ጎግል ፕሌይ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጅ አልሚዎችን መቀበል መጀመሩ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው።
በሌላ በኩል በዲጅታል ቴክኖሎጅው ዘርፍ ፈጠራ ላበረከቱ  ኢትዮጵያውያንም መተግበሪያዎቻቸውን በትልልቅ ዲጂታል መድረኮች ለማስተዋወቅ አዳዲስ እድሎችን እንደሚከፍትም ተናግረዋል። 

ኢዘዲን በበኩሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በግልም ሆነ በኩባንያ ደረጃ ለሚበለፅጉ መተግበሪያዎች ከዚህ ቀደም የነበረውን ችግር በመፍታት ጥሩ ዕድል የሚከፍት መሆኑን ይናገራል።  «ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መተግበሪያ ከሰራ አካውንት ከፍቶ መጠቀም የሚችልበት ዕድል ነው የፈጠረው።ይህ ለኩባንያዎችም በጣም ትልቅ ነገር ነው።ለግለሰቦችም ትልቅ ነገር ነው።ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች በጎግል ፕሌይ ይፋ የሚያደርጓቸው መተግበሪያዎች ከኩባንያው ቁጥጥር ውጭ ሆኖ በሌላ ኩባንያ ስር ነበር ይፋ ሲደረግ የነበረው።መተግበሪያዎችን «ዳውንሎድም» ስናደርግም የኩባንያው ስም ሌላ ሆኖ ይታይ ነበር።ምክንያቱም የኢትዮጵያ ንግድ ፈቃድ ተተቀባይነት ስለሌለው ማለት ነው።አሁን ግን ለምሳሌ የኛ ድርጅት አይቬክስ ቴክኖሎጅ እና ፕሮሞሽን «ፐብሊሽ» ሲያደርግ በኛ ስም ነው ይፋ የሚሆነው።በተመሳሳይ ደንበኞችም ይፋ ማድረግ ሲፈልጉ በስማቸው መተግበሪያ ፐብሊሽ ማድረግ፣በድርጅታቸው ፐብሊሽ ማድረጊያ ዕድል ነው የተፈጠረው።» በማለት አብራርቷል።  

ዓለም አቀፍ የክፍያ አማራጮች ችግር

ይህ የጎግል ፕሌይ አገልግሎት በኢትዮጵያ  ተደራሽ መሆኑ፤ የመተግበሪያ አልሚዎች 25 ዶላር በመክፈል ያለ ሁለተኛ አካል ጣልቃ ገብነት  ራሳቸው ሃላፊነት ወስደው በሀገር ውስጥ አካውንት ለመክፈት ያሚያስችል ነው።ያም ሆኖ ናታን  አገልግሎቱ የሚቀረው ነገር አለ ይላል።«ግን አሁንም አላለቀም።የጎግል ፕሌይ ተደራሽ መሆን አንድ ነገር ሆኖ፤ግን የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል።የኢትዮጵያ አልሚዎች 25 ዶላር ክፍያ መክፈል አለባቸው።ይህንን  የውጭ ምንዛሬ ለመክፈል  ክሬዲት ካርድ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች እንዴት አድርገው የጎግል ፕሌይ አካውንት መክፈት ይችላሉ የሚለው አንድ «ስቴፕ» ይቀራቸዋል ማለት ነው።ሌላ ሀገሮች ሩቅ ሳንሄድ ኬንያን መውሰድ ይቻላል።የኬንያ አልሚዎች በኤምፔሳ የጎግል አካውንት መክፈት ይችላሉ።እዚያው ሀገራቸው ውስጥ ማለት ነው።ጉግል በቀጥታ ከአካባቢው ባንኮች ጋር እየሰራ ነው።በኤምፔሳ ከፍለው ቀጥታ ገንዘቡ ለጉግል ይደርሳል።እንደዚህ ሲሆን ብዙ አልሚዎችን ማበረታት ይቻላል።»በማለት ገልጿል።

የጉግል ፕሌይ አካውንት ለመክፈት በኢትዮጵያ እንደ ቪዛ እና ማስተር ካርድ ያሉ ዓለም አቀፍ የክፍያ አማራጮችን መጠቀም አሁንም ችግር ነው።ምስል Artur Widak/NurPhoto/picture alliance

በኢትዮጵያ አብዛኛው ሰው ከአፕል ተንቀሳቃሽ ስልኮች ይልቅ የአንሮይድ ስልኮችን የሚጠቀም ነው የሚለው ኢዘዲን፤ ከዚህ አንፃር  ጎግል ፕሌይ ለሀገሪቱ የቴክኖሎጅ ማኅበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን መደረጉ የተሻለ ጥቅም ያስገኛል።ይህም በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ሰዎች  ኢትዮጵያውያን የሰሯቸውን መተግበሪያዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ  በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።ሆኖም ግን በበይነመረብ ግብይት ላይ የውጭ ምንዛሬን ለመጠቀም የሚያስችል የክፍያ አማራጭ  አለመኖሩ እንደ ኢዘዲን አሁንም ድረስ ያልተፈታ ችግር ነው። 
ይህ መሰሉ የክፍያ ችግር ከተቀረፈ ግን አዲሱ አገልግሎት ለመተግበሪያ አልሚዎች ብቻ ሳይሆን ለኢeትዮጵያም ጥሩ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ኢዘዲንም እና ናታን ይስማማሉ።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW