1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንጸባራቂ ድል እና የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ

ሰኞ፣ የካቲት 4 2016

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ሀገራት በተከናወኑ የሩጫ ውድድሮች አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል። 34ኛው የአፍሪቃ ገና ከጅምሩ ብዙዎች እንደገመቱት እና እንደጠበቁት ሳይሆን በአዘጋጇ ሀገር ኮትዲቯር አሸናፊነት ፍጻሜውን አግኝቷል።

Fußball | Africa Cup of Nations Finale | Elfenbeinküste Sieger
ምስል FRANCK FIFE/AFP

የየካቲት 4 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

This browser does not support the audio element.

 

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ሀገራት በተከናወኑ የሩጫ ውድድሮች አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል። ለመልስ ጫወታ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተጓዘው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ሴት ብሄራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪቃ አቻው ጋር ያለምንም ጎል አቻ ተለያይቷል። 34ኛው የአፍሪቃ ገና ከጅምሩ ብዙዎች እንደገመቱት እና እንደጠበቁት ሳይሆን በአዘጋጇ ሀገር ኮትዲቯር አሸናፊነት ፍጻሜውን አግኝቷል። ኬንያ በብርቱ ሀዘን ተይዛለች ፤ የዓለማችን የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ገና በለጋ ዕድሜው በ24 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል ፤  የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መሪዎቹ ክለቦች ያሸነፉባቸው ውጤቶች ተመዝግበዋል፤ የጀርመን እና የስፔይን ሊጎች ሰፊ ትኩረት ያገኙ ግጥሚያዎች ዉጤቶች ይዘናል።

ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በፈረንሳይ ሌቪን በተለያዩ ርቀቶች  በተካሄደ የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አሸናፊ የሆኑባቸው ውጤቶች ተመዝግበዋል።። በውድድሩ  የ3 ሺ ሜትር ጉዳፍ ጸጋይ አሸንፋለች ። ጉዳፍ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደባት ጊዜ 8፡17.11 ሲሆን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን ክብረ ወሰን ለማሻሻል 51 ሰከንዶች ብቻ መዘግየቷን ዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል። የጉዳፍ ሰዓት የምንጊዜም ሶስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።

በውድድሩ  የ3 ሺ ሜትር ጉዳፍ ጸጋይ አሸንፋለች ። ጉዳፍ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደባት ጊዜ 8፡17.11 ሲሆን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን ክብረ ወሰን ለማሻሻል 51 ሰከንዶች ብቻ መዘግየቷን ዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል።ምስል INA FASSBENDER/AFP

ጉዳፍ ጸጋይ የ10 ሺ ሜትር የክብረ ወሰን ባለቤት ስትሆን ከፊታችን በሚካሄደው የፓሪስ የኦሎምፒክ ውድድር ከወዲሁ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች ውስጥ ተጠቃሽ መሆን የቻለችባቸውን ውጤቶች በተከታታይ ማስመዝገብ ችላለች ። በርቀቱ ሂሩት መሸሻ ሁለተኛ ወጥታለች። ኬንያዊቷ ቢአትሪክ ቼፕቾክ ሶስተኛ ወጥታለች።  በቅዳሜ ምሽቱ ውድድር በ1,500 ሜትር ርቀት ፍሬወይኒ ኃይሉ ፣ ድርቤ ወልተጂ ፣ ብርቄ ሃየሎም እና ሃብታም ዓለሙ ተከታትለው በመግባት ከ1 እስከ 4 ያለው ደረጃ አሸናፊ ሆነዋል። ፍሬወይኒ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 3:57.24 ወስዶባታል።

በወንዶቹ ምድብ በ3 ሺ ሜትር ውድድር ሰለሞን ባረጋ ፣ ቢኒያም መሃሪ እና ጌትነት ዋለ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመቆጣጠር አሸናፊ ሆነዋል። ሰለሞን ባረጋ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 7 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ ወስዶበታል። በ2 ሺ ሜትር ውድድር የመሰናክል ሩጫ የዓለም የክብረ ወሰን ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ ለክብረ ወሰን የቀረበ ውጤት በማስመዝገብ ጭምር አሸናፊ ሆኗል። ለሜቻ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 4:51.23 ወስዶበታል። ስዊድናዊው ሳሙኤል ፒልስቶርም ሁለኛ ሲወጣ ሉክዘንበርጋዊው ቻርለስ ግሬተን ሶስተኛ ሆኗል። 

በወንዶቹ ምድብ በ3 ሺ ሜትር ውድድር ሰለሞን ባረጋ ፣ ቢኒያም መሃሪ እና ጌትነት ዋለ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመቆጣጠር አሸናፊ ሆነዋል። ሰለሞን ባረጋ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 7 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ ወስዶበታል። በ2 ሺ ሜትር ውድድር የመሰናክል ሩጫ የዓለም የክብረ ወሰን ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ ለክብረ ወሰን የቀረበ ውጤት በማስመዝገብ ጭምር አሸናፊ ሆኗል። ምስል DW/H.Tiruneh

ወደ እግር ኳስ ዜናዎች ስንሸጋገር ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ሴት ብሄራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪቃ አቻው ጋር ከሜዳው ውች ያደረገውን ጫወታ ያለምንም ጎል አቻ ተለያይቷል። ወጣት ቡድኑ አስቀድሞ በሜዳው የደቡብ አፍሪቃ አቻውን 3 ለ 0 አሸንፎ ስለነበር ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል። ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ምንም እንኳ ጎል ባያስቆጥርም በጫወታ ልቆ መታየቱ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ውድድሮች ተስፋ እንዲሰነቅበት አድርጓል። ቡድኑ ትናንት አዲስ አበባ ሲደርስ በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎለታል።

በሌላ የሀገር ቤት ዜና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን የካፍ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ መምረጡን ፌዴሬሽኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። በዚሁ መሰረት አቶ ኢሳያስ ጂራ 24 አባላት ያሉት የካፍ ስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን እንደሚያገለግሉ መረጃዎች ያመለክታሉ ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን የካፍ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ መምረጡን ፌዴሬሽኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

34ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ትናንት ምሽት ፍጻሜውን ሲያገኝ አዘጋጇ ሀገር ኮትዲቯር ናይጄሪያን 2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት ችላለች። በዓለማቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች እጅግ ተቀራራቢ ውጤቶች ያሏቸው ሁለቱ ሀገራት የአፍሪቃ ዋንጫን ሁለት ሁለት ጊዜ በማንሳት ይታወቁም ነበር ። ኮትዲቯር አሁን ለሶስተኛ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የበላይነቷን አረጋጋጣለች። በትናንት ምሽቱ ግጥሚያ በ38ኛው ደቂቃ በተከላካዩ ዊሊያም ትሮስት የጭንቅላት ግብ ቀዳሚ መሆን ችላ የነበረው ናይጄሪያ ስትሆን ኮትዲቯር ከእረፍት መልስ በ62ኛው ደቂቃ በፍራንክ ኬሴ የጭንቅላት ግብ አቻ ሆናለች።

በ81ኛው ደቂቃ ለራሱ በተዓምር ከካንሰር ተርፎ በውድድሩ ላይ የተሳተፈው  የዶርትሙንዱ ኢንተርናሽናል ሴባስትያን ሃለር በግማሽ ፍጻሜ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ የማሸነፊያ ጎል አስቆጠረው ወደ ሀገሩን ወደ ፍጻሜ ማሻገሩ አይረሳም ። በትናንት ምሽቱ የፍጻሜ ጫወታ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ከክንፍ የተሻገረለትን ኳስ በቄንጥ በማስቆጠር ለሀገሩ ሁለተኛውን እና የማሸነፊያውን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

በ81ኛው ደቂቃ ለራሱ በተዓምር ከካንሰር ተርፎ በውድድሩ ላይ የተሳተፈው  የዶርትሙንዱ ኢንተርናሽናል ሴባስትያን ሃለር በግማሽ ፍጻሜ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ የማሸነፊያ ጎል አስቆጠረው ወደ ሀገሩን ወደ ፍጻሜ ማሻገሩ አይረሳም ። ምስል ISSOUF SANOGO/AFP

በእርግጥ ነው ገና ከጅምሩ ለተመለከተ ኮትዲቯር ዋንጫ ታነሳለች ሳይሆን ከመጀመሪያው ዙር ማለፏ በራሱ አጣብቂን ውስጥ ነበረች ። ነገር ግን የቀድሞው ኮከቧ ዲድየር ድሮግባን ጨምሮ የደፊፊጋው ህዝብ ጽናት ፣ ዋናውን አሰልጣኝ ተክተው የገቡት አሰልጣኝ ኢሜርሴ ፋኤ ኃላፊነት በተረከቡ ቅጽበት ታላቁን የአህጉሩቱን ዋንጫ መሳም ችለዋል። በኦሎምፒክ ስታዲየም በመገኘት ጫወታውን የተከታተሉት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አላሳኔ ኦታራ የጫወታውን መጠናቀቅ ተከትሎ ከተጫዋቾችቹ ጋር ወርደው በመጨፈር ጭምር ደስታቸውን ገልጸዋል። በውድድሩ የናይጄሪያው ተከላካይ እና አምበል ዊሊያም ትሮስት የኮከብ ተጫዋችነት የወርቅ ዋንጫ ሲሸለም የኢኳቶሪያል ጊኒው አጥቂ ኤሚሊዮ ንሱኤ በአምስት ጎሎች የኮከብ ጎል አግቢ እንዲሁም የደቡብ አፍሪቃ በረኛ ሮንዌይ ዊሊያምስ የውድድሩ ምርጥ በረኛ በመሆን የወርቅ ጓንት ተሸላሚ ሆኗል። ደቡብ አፍሪቃ ባለፈው ቅዳሜ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በመለያ ምት አሸንፋ ውድድሩን በሶስተኛ ደረጃ አጠናቃለች ። የአፍሪቃ ዋንጫን ሰባት ጊዜ በማንሳት ግብጽ ቀዳሚ ስትሆን ካሜሩን አምስት ጊዜ በማንሳት ትከተላለች። 35ኛውን የአፍሪቃ ዋንጫ ለማዘጋጀት ሞሮኮ ኃላፊነቱን በይፋ ተረክባለች።

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መሪዎቹ ክለቦች አሸናፊ የሆኑባቸው ውጤቶች የተመዘገቡበት ሆኖ አልፏል።  ከአስቶን ቪላ በስተቀር ከፊት ያሉት ሁሉም ባሸነፉበት የሳምንቱ ውድድር ትናንት እሁድ አርሴናል ዌስት ሐምን 6 ለ 0 ያሸነፈበት  ውጤት ተጠቃሽ ሲሆን ወደ ቪላ ፓርክ ያቀናው ማንችስተር ዩናይትድ አስቶን ቪላን 2 ለ 1 አሸንፎ የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል። ባለፈው ቅዳሜ መሪው ሊቨርፑል በርንሌይን አስተናግዶ 3 ለ ሲያሸንፍ ተከታዩ ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ኤቨርተንን አሰተናግዶ 2 ለ 0 አሸንፏል። ቶተንሃም ሆትስፐርም  በተመሳሳይ በራይተን ኤንድ አልብዮንን አስተናግዶ 2 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል። ሊጉን ሊቨርፑል በ54 ነጥቦች ሲመራ አንድ ተስተካካይ ጫወታ የሚቀረው ማንችስተር ሲቲ በ52 ነጥቦች በሁለተኛነት ሲከተል ከሲቲ ተመሳሳይ 52 ነጥብ እና ተመሳሳይ የ31 ጎል ልዩነት ያለው አርሴናል ብዙ በተሸነፈ በሶስተኛነት ይከተላል። ቶተንሃም ሆትስፐር በ47  ነጥቦች አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሼፊልድ ዩናይትድ ፣ በርንሌይ እና ኤቨርተን ከኋላ ወደ ፊት በቅደም ተከትል ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ።

ከአስቶን ቪላ በስተቀር ከፊት ያሉት ሁሉም ባሸነፉበት የሳምንቱ ውድድር ትናንት እሁድ አርሴናል ዌስት ሐምን 6 ለ 0 ያሸነፈበት  ውጤት ተጠቃሽ ሲሆን ወደ ቪላ ፓርክ ያቀናው ማንችስተር ዩናይትድ አስቶን ቪላን 2 ለ 1 አሸንፎ የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል።ምስል John Walton/empics/picture alliance

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት እሁድ በተደረጉ ጫወታዎች ፍራይቡርግን በሜዳው ያስተናገደው ቦሩሽያ ዶርትሙንድ 3 ለ0 ሲያሸንፍ ወደ ሊቨርኩሰን ያቀናው ባየር ሙኒክ 3 ለ0 ተሸንፎ ለመመለስ ተገዷል። ማይንዝን በሜዳው ያስተናገደው ሽቱትጋርት ደግሞ 3 ለ 1 በማሸነፍ ለዋንጫው የሚያደርገውን ፍልሚያ አጠናክሯል።

ሊጉን ሊቨርኩሰን በ55 ነጥቦች ሲመራ ባየር ሙኒክ ሽቱትጋርት እና ዶርትሙንድ በ50፣43 እና 40 ነጥቦች ይከተላሉ ። ዳርምሽታት፣ ማየንዝ እና ኮሎኝ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ይገኛሉ ።

በስፔይን ላሊጋ ትናን ከተደረጉ የሳምንቱ መቸረሻ ቀናት ጫወታዎች ውስጥ ሴቪያ አትሌቲኮ ማድርዲን 1 ለ 0 ያሸነፈበት ጫወታ ተጠቃሽ ነው። ግራናዳን ያስተናገደው ባርሴሎናም 3 አቻ በመውጣት ነጥብ ጥሏል። ቅዳሜ ዕለት ከተደረጉ ጫወታዎች በሊጉ ተከታዩ ጊሮናን ያስተናገደው ሪያል ማድሪድ 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን ያሰፋበትን ድል አስመዝግቧል። ሊጉን ሪያል ማድሪድ በ61  ነጥቦች ይመራል። ጊሮና በ56 ነጥቦች ይከተላል፤ ባርሴሎና እና እና አትሌቲኮ ማድሪድ በ51 እና 48 ነጥቦች ሶስተና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አልሜሪያ ፣ ግራናዳ እና ካዲዝ በወራጅ ቀጣና ውስጥ ጸንተዋል።

በስፔይን ላሊጋ ትናን ከተደረጉ የሳምንቱ መቸረሻ ቀናት ጫወታዎች ውስጥ ሴቪያ አትሌቲኮ ማድርዲን 1 ለ 0 ያሸነፈበት ጫወታ ተጠቃሽ ነው። ግራናዳን ያስተናገደው ባርሴሎናም 3 አቻ በመውጣት ነጥብ ጥሏል።ምስል imago images/Cordon Press/Miguelez Sports

የቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ከነገ ምሽት ጀምሮ በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ይስተናገዳሉ ። ነገ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ኮፐንሃገን ማንችስተር ሲቲን ሲያስተናግድ  የጀርመኑ አር ቢ ላይፕሲች በተመሳሳይ ሰዓት ሪያልማድሪድን ያስተናግዳል። ረቡዕ ምሽት በሚደረጉ ጫወታዎች ደግሞ የፈረንሳዩ ፓሪሰንዤርሜ የስፔይኑ ሪያል ሶሴዳድን ሲያስተናግድ የጣልያኑ ላዚዮ ባየር ሙኒክን ያስተናግዳል። ቀሪ አራት ጫወታዎች ደግሞ ሳምንት ማክሰኞ እና ረቡዕ ይከናወናሉ።

ዜና ህልፈት

ኬንያ ከትናንት ምሽት ጀምሮ በብርቱ ሃዘን ተይዛለች ። ወርቃማ ልጇን ገና በለጋ ዕድሜው በሞት ተነጥቃለች ። አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም የዓለም የማራቶን ርቀት ክብረወሰንን በእጁ ማስገባቱን ሲያረጋጥ ገና አንድ ሳምንቱ ነበር ። ዕድሜው ደግሞ ገና 24 ፤ ዓለምን ያስደመመው ወጣት የዓመቱ የትራክ ላይ የወንዶች  የረዥም ርቀት ሩጫ ኮከብ ተብሎ የተሸለመውም በቅርብ ነበር ።

ኬንያ ከትናንት ምሽት ጀምሮ በብርቱ ሃዘን ተይዛለች ። ወርቃማ ልጇን ገና በለጋ ዕድሜው በሞት ተነጥቃለች ። አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም የዓለም የማራቶን ርቀት ክብረወሰንን በእጁ ማስገባቱን ሲያረጋጥ ገና አንድ ሳምንቱ ነበር ።ምስል Alberto Pezzali/AP Photo/picture alliance

የፓሪስ ኦሎምፒክን ጨምሮ ከዚህ በኋላ በረጅም ርቀቶች ተዓምር ሊያስመለክት እንደሚችል የብዙኃኑ የአትሌቲክ አፍቃሪ ማኅበረሰብ ምኞትም ነበር ። ትናንት ምሽት ከወደ ናይሮቢ የተሰማው ዜና ግን ይህን ሁሉ ህልም ያደረገ ነበር ። ወጣቱ ተስፈኛ ኬልቪን ኪፕቱም ከአሰልጣኙ ጋር ምሽት አምስት ሰዓት ገደማ በደረሰበት የተሽከርካሪ አደጋ ህይወቱ ማለፉን የኬንያ የመገናኛ ብዙሃንን ጠ,ቅሰው ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል ። በወጣቱ አትሌት ህለፈት ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ በርካቶች ሃዘናቸውን እየገለጹ ነው።

ታምራት ዲንሳ 

እሸቴ በቀለ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW