1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወቅታዊ ስጋት

ዓርብ፣ ነሐሴ 20 2014

ጀርመን ውስጥ በቅርብ ጊዜ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዩክሬን ጦርነት እና የጀርመን የወደፊት እጣ ፈንታ ጀርመን ያሉ ወጣቶችን የሚያስጨንቋቸው ጉዳዮች ናቸው። ኢትዮጵያውያን ወጣቶችንስ? የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚያስጨንቁ ጉዳዮች ናቸው።

Äthiopien Tigray Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/Getty Images/AFP

የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወቅታዊ ስጋት

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት  በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች  የሚያስጨንቁ ጉዳዮች ናቸው። ጤና ይስጥልኝ የተከበራችሁ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች፤ ጀርመን ውስጥ በቅርብ ጊዜ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው ግማሽ ዓመት የሆነው የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት 57 በመቶ ያህሉን በመጠይቁ የተሳተፉ ወጣቶች ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል። ወጣቶቹ ይህ ድንበር ሊሻገር የሚችል ጦርነት ወደ ጀርመንም እንዳይመጣ ይሰጋሉ።  ሌላው ስጋታቸው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጡ ነው። ለሳምንታት  ዝናብ አለመጣሉ ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የወንዞች ውኃ መቀነሱ ፤ ድርቅ እና ሰደድ እሳት መከሰቱ የበጋውን ሙቀት በደስታ ብቻ እንዳያዩት አድርጓቸዋል። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ወጣት ዘሪሁን ብርሃኑ «ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ የበለጠ የሚያሳስቡን ነገሮች አሉ» ይላል። « የአየር ንብረት ለውጡ የሁሉም ሰዎች አለም አቀፍ ስጋት ነው። ግን ደግሞ ከሱ በላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። የምንኖረው ግጭቶች ባሉበት ቀጠና፤ ምስራቅ አፍሪቃ ውስጥ ነው የምንኖረው፤ ከዚያም በላይ ደግሞ ጦርነት ባለበት ሀገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ዳግም ወደ ጦርነት የገባንበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። እና እሱ ያሳስበኛል።» ይላል ዘሪሁን ሲቀጥል ደግሞ ድርቅ እና ሀገር ውስጥ የተፈናቀሉት ሰዎች ጉዳይ ሰላም እንደማይሰጡት ይናገራል። 

የደሴ ከተማ ነዋሪ እንደሆነ የገለፀልን አብዱ ሦስት ነገሮች ይበልጥ ስጋት ላይ ጥለውኛል ይላል። ቀዳሚው በሰሜኑ ክፍል ዳግም ያገረሸው ጦርነት ነው፤ « የመጀመሪያው ጦርነት ጊዜ አካባቢውን ለቀው ካልሄዱት ውስጥ ነኝ እና ያሳለፍነው ነገር መልሶ ሊመጣብን ነው የሚል ፍርኃት አለኝ። የአማራ ክልል ፖለቲካ እንዲሁ ያሳስበኛል። እና ወሎ አካባቢ ተወልዶ እንዳደገ አንድ ወጣት ደሞ እሱ ሌላ የግጭት መነሻ ይሆን ይሆን የሚል ስጋት አለኝ።» ይላል። ሌላው አብዱን የሚያሳስበው የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ፖለቲካ ነው። አብዱ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን በምሳሌነት ያነሳል።  « ይሔ ወዴት አቅጣጫ ነው የሚወስዳደች። ሱዳንም ወደ ሌላ ሶማሊያነት ወደ የመንነት ትሄድ ይሆን? የሱስ ጫና እኛ ላይ ምንድን ነው የሚያመጣው? የደቡብ ሱዳንን አለመጠንከር ስናይ ያውም ረዥም ድንበር እንዋሰናለን። አሁን ድንበር አለበሚባልበት ሁኔታ ዘረፋ፣ የልጆች መታገቶች አሉ ይባላል። እና ጎረቤቶቻችን ወደ መንግሥት አልባነት ከተመለሱ እኛ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ጫና። ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው...እነዚህ ነገሮች አንድ የጭንቀት ምንጭ እንደሆነ ይሰማኛል። አብዱን በሦስተኛ ደረጃ የሚያሳስበው የአየር ንብረት ሁኔታው ነው። እሱ በሚኖርበት ደሴ ከተማ ዘንድሮ የጣለው ዝናብ በጣም ከባድ እንደነበር የሚናገረው አብዱ ፤ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ደሴ ውስጥ ሰዎች እየተፈናቀሉ፤  ቤቶች እየፈረሱ እና ድልድዮች እየሞሉ እንደሆነ በቅርብ የታዘበውን ገልፆልናል። ከሁሉም የሚያሰጋው ግን ከከባድ ክረምት ወደ ድርቅ እንደሚገባ የተተነበየው የአየር ንብረት ባለሙያዎች አስተያየት ነው።
መንግሥቱ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚኖር የኮንሶ ተወላጅ ነው። እሱንም ቀደም ሲል ከተነሱት ጉዳዮች በተጨማሪ የሚያሳስቡት በርካታ ነገሮች አሉ። « አንደኛ በብሔር ላይ የሚደረግ ፌደራሊዝም፤ የእኔ ብሔር ይበልጣል ፤ የእኔ ብሔር የተሻለ ነው፤ የእኔ ብሔር ተጎድቷል የሚባልበት ሁኔታን ፈጥሯል። ሲቀጥል ደግሞ የክልል ልዩ ኃይሎች የሰላም ጠር ናቸው። ሌላው ኢትዮጵያን እየበጠበጠ ያለው ደግሞ አንቀፅ 39 ነው። ሁሉም መገንጠል ይፈልጋል።» ሌላው ሀሳቡን ያካፈለን አብራሃለይ ተስፋይ ይባላል። በተለይ ለትግራይ ወጣት በጣም ከባድ ጊዜ ነው የሚለው አብረሃለይ የትግራይ ተወላጅ ነው። « ወደ ጦርነት የሚማገደው ወጣቱ ነው። በተለይ ደግሞ የእርስ በእርስ ጦርነት በሚካሄድበት ጊዜ ከሌላው ወገን ጋር የተዋለደ፤ ቤተሰባዊነት፣ ጎደኝነት ሁኔታ ስላለ ስነ ልቦናዊ ቀውስ ይፈጥራል። በተለይ ደግሞ ለትግራይ ወጣት አሁን፤ አብዛኛው ቤተሰቡ ትግራይ ነው ያለው። አዲስ አበባ የሚኖሩ ስለ ቤተሰቡ በጣም ይጨነቃል። ቤተሰቡ አብዣኛው እዛ ነው ያለው። እና የእነሱ ሁኔታ ያሳስባል፣ ምን ይበሉ ይሆን ? እንዴት ይሆኑ ይሆን የሚለው ያሳስባል። አሉ ወይ በህይወት የሚለው ያሳስባል። የአንዳንዶቹ ወደ ዳር እየመጡ እንደሚደውሉ እንሰማለን። የእኛ ቤተሰቦች ግን አልደወሉም» የሚለው አብራሃለይ አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ጊዜ መታሰሩን እና ያስሩኝ ይሆን የሚል ስጋት እንዳለው ለዶይቸ ቬለ ተናግሯል።
የሀገሪቱ ሰላም ማጣት አስተያየቱን ያካፈለን የሬድዋን መሀመድም ቀዳሚ ስጋት ነው። ሲቀጥል ደግሞ ሥራ አጥነትን እና ኑሮ ውድነትን ያነሳል። በአሁኑ ሰዓት በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ተቀጥሮ እየሠራ የሚገኘው ሬድዋን እሱም ሥራውን እንዳያጣ ይሰጋል። « ምናልባት እኔ የምሰራባቸው ፕሮጀክቶች ይቆማሉ የሚል ስጋት አለኝ።» የሚለው ወጣት የዩክሬን ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በእሱ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ያምናል። ሥራዬ ከአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው የሚለው ሬድዋን በመጨረሻ ዘንድሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ድርቅ ለስጋቱ በምሳሌነት ያነሳል። « ድርቁ በከፍተኛ ደረጃ ነው ያለው። በተለይ በምስራቅ እና በደቡብ። ያ ደግሞ ብዙ ሰዎች እንዲራቡ አድርጓል። ዝናቡ በአሁኑ ሰዓት ጥሩ አይደለም። በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ መካከለኛው ኢትዮጵያ ላይ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ነው የምኖረው እና ዝናብ ስለሌለ በቂ ምርት አይገኝም የሚል ስጋት አለኝ።»

የመቀሌ ነዋሪዎች ከኢንተርኔት ሱቅ በር ላይ ቆመው ዜና ሲያዳምጡምስል Million Hailessilassie/DW
ኮንሶ፦ አንድ ገበሬ በድርቅ የተጎዳ ሰብሉን ሲመለከትምስል Konso Development Association
በጦርነቱ ምክንያት በከባድ መሣሪያ የተደበደበው ደሴ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

በቴሌግራም አስተያየቱን ያካፈለን DA« እኔን እንደ ወጣት የሚያስጨንቀኝ ነገር ኋላ-ቀር የሆነ የአስተራረስ ዘዴያችን እስከ መቼ ድረስ ይቀጥላል የሚለው ነው።» ይላል።
ሜላት እኔን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊት ወጣት የሚያሳስበኝ   «የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ዕድል አለመኖር፣ የምፈልገውን አለመሆን፣ ሰላም ማጣት... ናችው በዚህ አካሂድ ወደፊት ምንድነው የሚሆነው ‘’ነገ’’ የሚለው ያሳስበኛል። » ብላናለች።
ከንቲባው ደግሞ «የቤት ኪራይ እና ሥራ ያሳስበኛል ብሎናል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW