የኢትዮጵያውያን የባህልና ስፖርት በዓል በፍራንክፈርት
ሐሙስ፣ ግንቦት 16 2010በዚሁ ዝግጅት በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአጎራባች የአውሮጳ ሃገራት ጭምር መጥተው ታድመዋል:: የበዓሉ ሞቅ ደመቅ ማለት ልዩ የመነቃቃት ሥሜትን የፈጠረባቸው ኢትዮጵያውያን እና ከተለያዩ ከተሞች የመጡ የእግርኳስ ደጋፊዎች ያሰሙት የነበረው ጭፈራ እና ሆታም የሃገር ቤትን ድባብ ከመፍጠሩም ሌላ ለዝግጅቱም የበለጠ ድምቀትን ሰቶታል ::
የዘንድሮውን የኢትዮ- ጀርመን የሥፖርት እና የባህል ክብረ በዓል ልዩ የሚያደርገው ሥፖርታዊ እንቅስቃሴውን የፍራንክፈርቱ ኢትዮ-አዲስ የስፖርት ክለብ ምግብ እና መስተንግዶውን ለኢትዮጵያውያን ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያበረክተው አዳብና የኢትዮጵያ የባሕል ሬስቶራንት እንዲሁም የመዝናኛውን ጉዳይ ደግሞ ለረጅም ዓመታት ከሀገር ቤት የሙዚቃ ባለሙያዎችን ወደ ጀርመን እያስመጡ የመድረክ ዝግጅቶችን በማቅረብ የሚታወቁት አቶ አልያስ የማነ በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ነው ::
በዚህ የባህል እና ስፖርት በዓል ላይ ከስዊትዘርላንድ ዙሪክ እና ከጎረቤት ኤርትራ በእንግድነት የተጋበዙበት እንዲሁም ከመላው ጀርመን 15 ያህል የእግርኳስ ቡድኖች የተካፈሉበት ውድድርም ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነበር :: ለፍጻሜ የደረሱት ዙሪክ እና ሽቱትጋርት በመደበኛው የውድድር ሰዓት ዜሮ ለ ዜሮ በማጠናቀቃቸው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የፍጹም ቅጣት ምት ሽቱትጋርት 5 ለ 4 በሆነ ውጤት አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል :: ከዚህ ሌላ የኮሎኙ እቴሜቴ ኢትዮ-ጀርመን የቤተሰብ እና የባሕል ማሕበር ያሰለጠናቸው ወንድ እና ሴት ሕጻናቶች ያቀረቡት የብሔር ብሔረሰቦች ውዝዋዜ እና የእግርኳስ የሥፖርት ውድድር ተሳትፎም በበዓሉ ታዳሚዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት አግኝቷል ::
የበዓሉ ታዳሚዎችም ይህ ዓይነቱ ዝግጅት የተራራቀን ወዳጅ ከማገናኘት እና ከአዝናኝነቱ ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አኩሪ ባሕሎቻቸውን ቅርሶቻቸውን እና ወጎቻቸውንም ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉ ይረዳል ይላሉ:: በተለይም በውጭ የሚወለዱ ሕጻናት ከደባል ሱሶች ርቀው በሥፖርታዊ የጨዋነት ሥነምግባር እንዲታነጹ ሀገራቸውን እንዲወዱ ብሎም ተሰጥዖ እና ችሎታቸው ለፍሬ እንዲበቃ ትልቅ እገዛ ያበረክታል ሲሉ ገልጸውልናል :: ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ይከታተሉ፤
እንዳልካቸው ፈቃደ
ሸዋዬ ለገሠ