የኢትዮጵያውያን የኪነ-ጥበብ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ 2ኛ አመት ክብረ በዓል
እሑድ፣ ነሐሴ 2 2013
የኢትዮጵያውያን የኪነ-ጥበብ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ በአሜሪካ የሚኖሩ የጥበብ ሰዎችንና አፍቃሪዎችን ያካተተ ሃገር አቀፍና ሁሉንም የጥበብ ዘርፎች ያሰባሰበ ነው:: በሥነ ግጥም በድርሰት በሙዚቃ በስዕል በቅርፃቅርፅ በፊልምና በዳይሬክቲንግ ሙያዎች ዙሪያ የተሠማሩ ባለሙያዎችን እንዲሁም ፍላጎቱ ያላቸውን ግለሰቦች ወይም በደፈናው የጥበብ አድናቂዎችን ሁሉ አቅፏል:::
የማኅበሩ ምሥረታ ዐሣብ እዚህ አትላንታ ውስጥ በፀሐፊ ቴዎድሮስ ታደሰ ተጠንስሶ መሠረት ተጣለ::ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አከበረ::በዚሁ ዝግጀት ላይ ላይ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት አንጋፋና ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መካከል አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ትገኝበታለች::
የኢትዮጵያውያን የኪነ-ጥበብ በሰሜን አሜሪካ በመጀመሪያ ዓመታዊ ዝግጅቱ ወቅት ሲያትል ላይ አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆን ነበር ያከበረውና ያወደሰው::የዘንድሮው በዓል ባለተራ ደግሞ አንጋፋው የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ኘሮፌሰር አዱኛው ወርቁ "ይህ የኪነጥበብ ማዕከል ሲመሰረት አትላንታ ስለነበርኹ እኔም ከመስራቾቹ አንዱ ነኝ::እንኳን ደስ አላችሁ ከማለት እንኳን ደስ አለን ልበል::ጥበብ ለሁሉም የተሰጠች ፀጋ አይደለችም::ለተለዩ በቁጥር ጥቂት ለሆኑ ሰዎች የተሰጠች ነች" ብለዋል።
በስራ በጥበብ ግሎ ለመነሳት
ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደእሳት
የሚል አባባል አለ:ጥበብ እሳት ነች::የጥበብ ሰዎች ደግሞ ቆስቋሾች ናቸው በብዙ አቅጣጫ::እናም ይህ መድረክ ለሁለት ዓመት ፀንቶ በመቆየቱ በጣም ደስ ብሎኛል::
ፀሐፊ ዘመናይ ዘሪሁን ከማኀበሩ መስራቾች መኻል አንዷ ናት "ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጥበብ ማህበረሰቦችንና የቴአትር ድርጅቶችን መርዳት በስልጠና በአልሰባት የፀጉር ሜካአፖችንና ከስተሞችን እንዴት ማድረስ ይቻላል?የመድረክ ቁሳቆሶችን ከትልልቅ ካምፓኒዎችንና ወይም ትምህርት ቤቶች ጋር ተገናኝቶ ተፃፅፎ ማድረስ የሚቻልበት መድረክ ማዘጋጀት ወይም ማመቻቸት ከዓላማዎቹ ውስጥ ነው::እዚህ ላለው ማኀበረሰብ ደግሞ ስልጠና በመስጠት የቴአትር ትምህርትም ቢሆን ለምሳሌ የአፃፃፍ ስልት ከባለሙያዎች ጋር በመገናኘት መድረኩን ያመቻቻል::ከዛ ባሻገር ደግሞ የማዝናናት የማሳተፍ በሙዚቃም ቢሆን በስነ ፅሑፍም ቢሆን የመድረክ ስራዎችን በመስራት ለምሳሌ በዓመት አንዴም ሁለቴም ቢሆን በየከተሞቹ እየተዞረ የመድረክ ባለሙያዎች ስራቸውን ለህብረተሰቡ ማሳየት ሕብረተሰቡ እየተዝናናም አርቱን ይደግፋል ማለት ነው" ብላለች።
ከባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ሥራዎች መኻከል "ሀሁ ወይም ፐፑ "የተሰኘውንና የዛሬ ሰላሣ ዓመት ፅፎት በብሔራዊ ቴአትር ከተዘጋጀው ትዕይንት አምስት የተወሰነውን ክፍል አርቲስት ተስፋዬ ሲማ አቅርቧል::
በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ማኀበርን የዛሬ ሁለት ዓመት የሙያ አጋሮቹን አነሳስቶ ያስጀመረው የአትላንታ ነዋሪ የሆነው ፀሐፊ ቴዎድሮስ ታደሰን ማኀበሩን ለማቋቋም የተነሳህበት ዐሳብ አሁን የት ደርሶ አገኘኸው ብለን ጥያቄ አቅርበንለት ነበር::
"የኢትዮጵያውያን የጥበብ ማኅበረሰብ በሰሜን አሜሪካ ሲጠነሰስ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የጥበብ ባለሙያዎችን አንድ ላይ አሰባስቦ የተሻለ ሥራ ለመስራት ነው::ያው መቼም ሰው ሲደራጅ በግል ከሚደረግ እንቅስቃሴ ይልቅ በጋራ የሚደረግ እንቅስቃሴ ውጤታማ ስለሚሆን እዛም እዚኽ ተበታትኖ ያለ የጥበብ ባለሙያ በአንድ ላይ ቢሰባሰብ በአንድ ላይ ቢደራጅ አይደለም ለራሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ የጥበብ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ድጋፍ ማድረግ ይችላል ከሚል ሃሳብ ነው የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ከጁላይ ወር 2019 ጀምሮ አስካሁን እየተንቀሳቀስን ያለነው::በርካታ ነገሮችን ለመስራት ተሞክሯል እስካሁን::ሁለት ትላልቅ መድረኮችን በአትላንታና በሲያትል አካሄደናል::አውደ ጥናቶችንም በተለያየ መልኩ በዙም ለማድረግ ተሞክሯል::አሁንም የፊታችን ኦገስት 15 ተጨማሪ ወርክሾፕ እያዘጋጀን ነው::ከሃምሣ በላይ የሚሆኑ የጥበብ መድረኮችን በየሣምንቱ በቴሌኮንፈረንስ አካሄደናል::ከተለያዩ አካባቢዎች የጥበብ ሰዎች ሥራዎቻቸውን ለማቅረብ ችለዋል::ከዚህ አኳያ እንደጀማሪ ማኀበር ብዙ ሥራዎችን ሰርተናል ብዬ አስባለሁ::በቀጣይም ማኀበሩ በርካታ ዓላማዎችን አንግቦ ነውና የተፀነሰው እነዛ ትልልቅ ዓላማዎች በሰሜን አሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ አጠቃላይ የጥበብ ዘርፎች ላይ የራሳችንን አሻራ ጥለን ለማለፍ ነው እየሰራን ያለነው::" በማለት መልሷል።
በበይነ መረብ አማካይነት በተካሄደው የማኀበሩ ሁለተኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ሌሎችም በርካታ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን አቅርበውበታል::
ታሪኩ ኃይሉ