1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ባህልሰሜን አሜሪካ

የኢትዮጵያውያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የስፖርትና ባህል ትርዒት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1 2015

የኢትዮጵያውያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣በዳላስ ቴክሳስ ሲያካሂድ የሰነበተው የስፖርትና ባህል ትርዒት ዛሬ ይጠናቀቃል። አርባኛው ዓመት የፌዴሬሽኑ ክብረ በዓል የተከበረበት የዘንድሮው ዝግጅት፣ ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ መካሄዱን የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዕያዮ ዘነበ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል።

USA | Logo Ethiopian Sports Federation
ምስል ESFNA

የኢትዮጵያውያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የስፖርትና ባህል ትርዒት

This browser does not support the audio element.

መሰንበቻውን በዳላስ ቴክሳስ በሚገኘው የዋይሊ ስቴዲዬም፣ ከመላው ዩናይትድስቴትስ እንዲሁም ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የመጡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያን  ተሰባስበው በድምቀት አሳልፈዋል።

ኢትዮጵያኑና ትውልደ ኢትዮጵያኑ፣ለአንድ ሳምንት የቆየውንና 31 ቡድኖች የተሳተፉበትን የእግር ኳስ ጨዋታ፣ የባህል ትርኢት እና ሌሎች ማህበራዊ መርሐ ግብሮችን ታድመዋል።

ለብዙ ዓመታት ሳይገናኙ የተነፋፈቁም፣ ወዳጆቻቸውን ያገኙበትን መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል።

የዘንድሮው ዝግጅት፣ ፌዴሬሽኑ አርባኛ ዓመት በዓሉን ያከበረበት   እንደመሆኑ፣ ከምንጊዜውም የተለየ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እያዩ ዘነበ።

"በወጣቶች እዚሁ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ፣እዚሁ ተወልደው ያደጉ ልጆች ትልቅ መክፈቻ ዝግጅት ተደርጎ ከዚህ በፊት ዳላስ ውስጥ ሲደረግ መጥቶ ያልነበረ  ህዝብ ነው የመጣው።ያም የሳምንቱ ምን ያህል ሊመጣ የሚችለውን ሊነግረን ችሏል።የሕዝቡ አመጣጥ በጣም ደስ የሚል ዝግጅት ነበር።"

ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በእግር ኳስና በአትሌቲክስ  የላቀ ውጤት ያስመዘግቡና አሜሪካን የመጎብኘት ዕድል ያላገኙ፣አንጋፋና ወጣት ስፖርተኞችን፣ በዓመታዊ ዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት እንዲገኙ ይጋብዛል።

በዘንድሮው ዝግጅቱ፣ ደግሞ ለሃገራቸውና ለፌዴሬሽኑ በጎ አበርክቶ አላቸው ያላቸውን ግለሰቦች አመስግኖ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል።

 በዚህም መሠረት አርቲስት ፋንትሽ በቀለ፣  ላለፉት 20 ዓመታት ፌዴሬሽኑ ለሚያካሂደው ትርዒት የሙዚቃ ባለሙያዎችን በማሠባሠብ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የባህል አምባሳደር ሲል እውቅና ሰጥቷታል።

 "ሮሃ"የተባለው የዩቲዪብ የቴሌቪዥን ጣቢያ መስራችና ባለቤት ጋዜጠኛው መአዛ መሐመድ በበኩሏ፣በጽናት በመቆም ለኢትዮጵያ ባበረከተችው መልካም ተግባር መሸለሟን አቶ ዕያዩ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ መአዛ፣በቅርቡ የዩናይትድስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው፣የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የጀግና ሴቶች ሽልማት አሸናፊ እንደነበረች ይታወቃል።

 በወቅቱ ለዶይቸ ቨለ በሰጠችው አስተያየትም፣ የሚከተለውን ተናግራ ነበር።

"የምትሰራው ሥራ ዓለም ያየዋል።ሁሉም ሰዎች ያዩታል ሐቅ ፊት ቆመህ ስለተበደሉት ስለተጨቆኑት የምትሰራ ከሆነ ሁልጊዜ ዐይኖች ወዳንተ ይመጣሉ ዋጋ አላቸው።ይህ ዋጋ መገኘቱ ደግሞ ሌሎች ሰዎች እንዲበረታቱ ሌሎች ሴቶች  በድፍረት በሐቅ እንዲቆሙ ያደርጋል።"

ሌላዋ ዕውቅና የተሰጣት፣ከፌዴሬሽኑ የዓመታት እንቅስቃሴ ጀርባ አጋር እንደሆነች የተነገረላት፣ ማዕደር  ገብረስላሴ መሆኗን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

"በገንዘብም በዐሳብም በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ፌዴሬሽኑን የምትደግፍ ናት። ላለፉት 34 ዓመታት ያህል ከእኛ ጋር የነበረች እሷንም ዕውቅና ሰጥተናል።ስፖንሰር በማድረግ ምንም ነገር ሳናደርግላት ድርጅቱን ስለምትወደው ብቻ ብዙ ድጋፍ የምታደርግልን ናት።"

በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ቀን ትናንት ማምሻውን በስቴዲየሙ ውስጥ በድምቀት ተከብሯል። በርካታ እንግዶች በባህል ልብስና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቀው ታድመውበታል።

ታሪኩ ኃይሉ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW