የኢትዮጵያው መሬት መንቀጥቀጥ ነዋሪዎችን እንዳሰጋ ነዉ
ረቡዕ፣ ጥር 7 2017
አፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢ ደጋግሞ እየመታ ያለው መሬት መንቀጥቀጥ ትናንት ማምሻውን ደግሞ ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎችን የሚያወስነውን ፈንታሌ ተራራ ንዶታል።ከዚህ በፊት በአፋር በኩል ያለው የተራራው ጫፍ የተናደ ሲሆን ትናንት በሬክተር መለኪያ 5.2 በተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ከኦሮሚያ ክልል መታሐራ ከተማ ትይዩ ያለው የተራራው አናት እንደ ጭስ በሚቦነው አቧራ ተሞልቶ ታይቷል፡፡የአከባቢው ነዋሪዎችም አሁን ስጋታችን ከፍቷል እያሉ ነው፡፡
የመታሃራ ከተማ ነዋሪው መስፍን መርጊያ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት የትናንት ምሽቱን የፈንታሌ ተራራን የናጠውን መሬት መንቀጥቀጥ ክስተትን በማብራራት ነው፡፡ “እንቅስቃሴው ትንሽ ከበድ ያለ ነው፡፡ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ተራራው ላይ ትንሽ የአፈር መናድም ነበር፡፡ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ተራራው ተሰነጣጥቆ በጨሰው ጭስ መሳይ አቧራ ሰውም ተረብሷል” ብለዋል፡፡
ትናንት ምሽት ፈንታሌ ተራራን የናደው የመሬት መንቀጥቀጥ በተለይም ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ ከተራራው ስር የሚገኙትን እንደ ቆቦ ያሉ ቀበሌዎችን ያሰጋ ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ አስቀድሞ ግን ሰዎችን ከዚያ የማንሳት ስራ በመሰራቱ በዚያ ሰው ላይ ጉዳት ይደርሳል የሚል ስጋት ለጊዜው ቀንሷል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም በአከባቢው ያሰጋው የመሬት መንቀጥቀጥ የሰፋ ስጋት ይደቅን ይሆን የሚለው ሀሳብ ከወዲሁ አስግቷል፡፡
የትናንት ምሽቱ 2 ሰኣት እና ሌሊት 7 ሰዓት ግድምከፍ ብሎ የተሰማው የመሬት መንቀጥቀጥ በዚህ በመታሃራ ዙሪያ ብቻ አልተወሰነም፡፡ አፋር ክልል አዋሽ 07 ከተማም የተሰማው ከፍ ባለ ስሜት ነው፡፡ አብደላ የተባሉ የአዋሽ 07 አስተያየት ሰጪ ህይወታችን ስጋት ላይ ነው ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ያካፈሉን፡፡ “ትናንት ምሽት 2 ሰኣትና ሰባት ሰዓት ግድም ከፍ ያለው መንቀጥቀጥ ነበር የተሰማው፡፡ ፈንታሌ ተራራ የሆነ ጩኸት ነገር ነበረው ግን በታም ያስፈራል” ሲሉ እረፍት አልባ ያሉት የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጋቱን አስረድተዋል፡፡
ሌላው የአዋሽ 07 አስተያየት ሰጪ መሬት ከመንቀትቀጥም አልፎ እያነጠረችን ነው ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተውናል፡፡ “አዋሽ አከባቢ የነበረው መንቀጥቀጥ የማንጠር ያህል ነበር፡፡ በወረብ በአንኮበር ወደ ደብረብርሃን የሚወስደው መንገድም እስካሁን አልተጎዳም ነበር በትናንቱ ግን መሰንጠቅ አሳይቷል፡፡ የመሬት መነቃነቁ ከቀጠለ የትራንስፖርት ጉዞንም ሊያቋርጥ ይችላል” ሲሉነ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን፡፡
እንደ እኚህ አስተያየት ሰጪ ሰዎችን ከአከባቢው የማሸሽ ስራ ብጀመርም አሁንም ድረስ ግን ሁሉም ሰው ከስጋት ቀጠናው ወጥተው አልቀዋል ለማለት እንደማያስደፍር አስረድተዋል፡፡
በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጥዳፋው ከሚያሰጋቸው ወረዳዎች ሁለቱ የሚገኙበት የክልሉ ዞን 03 (ገቢረሱ) ከአዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች በርካታ ዜጎችን ከስጋት ነጻ ወደ ተባሉ አከባቢዎች ማንቀሳቀሱን ከዚህ በፊት ገልጾ ነበር፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዶ አሊ አሁንም ነዋሪዎቹን ከቀበሌዎቹ የማራቅ ተግባር እንዳልተጠናቀቀና ስራው ግን ተጠናክሮ መቀጠሉን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ “ከአዋሽ ፈንታሌ 5 ቀበሌዎች ላይ የተፈናቀሉትን በተዘጋጁ ሁለት ሳይቶች ላይ አስፍረናቸዋል፡፡ ከዱለቻ ወረዳም በዋናነት ከሁለት ቀበሌዎች ሰዎች እንዲነሱ አድርገናል፡፡ ግን አሁንም ድረስ ሰዎቹን የማንሳት ተግባሩ የሚቀጥል ነው የሚሆነው አልተጠናቀቀም፡፡ እንደ ጥሩ ነገር ሚወሰደውም ከተቋማት ውጪ ሰው ላይ ደረሰ ጉዳት አለመኖሩ ነው” ብለዋል፡፡
የትናንትናውን ጨምሮ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ በተሰማው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ሳቢያ ከእልቅልፋችን እየቀሰቀሰን ሰላም አሳጥቶናል በማለት የሚያማርሩ የህብረተሰብ አካላት ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ በስምጥ ሸለቆው አዋሽ ዙሪያ እየተደጋገመ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ምናልባትም እንደ አዲስ አበባ ያሉ ህንጻዎች የሚበዙበት ራቅ ያሉ ከተሞች ላይ ጉዳት የማድረስ እድል ይኖረዋልን በሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ ጂኦፊዚክስና የመሬት መንቀትቀጥ ባለሙያው ፕሮፈሰር አታላይ አየለ፤ “የመሬት ምንቀጥቀጡ ከፍ ወዳለው ከ6 በላይ ሊከት ላይ ስደርስ ተወሰነ ጉዳት ያደርስ እንደሆን እንጂ የከፋ ይሆናል የሚል ግምት የለንም፡፡ ግን ከዚህ በፊት ተመሳሳ ነገር ሌላ ቦታ ተከስቶ ስለሚያውቅ ህዝቡ እንዲጠነቀቅ ማንቃት ስፈልጋል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ በስምጥ ሸለቆ አከባቢ ተደጋግሞ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በማስጋቱ ከ80 ሺህ በላይ ዜጎችን በማንሳት ከስጋት ቀጠናው ለማራቅ መወጠኑን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ