1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች የጀርመን ቆይታ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 30 2014

ሰዎች ሀኪም ቤት በመሄድ ከህመማቸው የሚድኑበት ዕድል እንዳለ ሁሉ ሀኪም ቤት ሄደው ሌላ በሽታ ሸምተው የሚመጡበት አጋጣሚም ጥቂት አይደለም። ከሀኪም ቤት ንጽህና አጠባበቅ ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያውን የህክምና ባለሙያዎች ጀርመን ውስጥ ለአንድ ወር የልምድ ልውውጥ ያደረጉበት አጋጣሚ አለ።

Deutschland | Vier Ärzte aus Äthiopien in deutschem Krankenhaus
ምስል Shewaye Legesse/DW

«የጋራ ጥምረት በጀርሞች ላይ ፕሮጀክት»

This browser does not support the audio element.

እዚህ ጀርመን ሀገር የተቋቋመው ዶክተሮች ለኢትዮጵያ ይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታልን በህክምና ቁሳቆሶች መደገፍ ከጀመረ 6 ዓመት ሆነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ካደረገው ድጋፍ በተጓዳኝ ለአንድ ወር የሆስፒታሉን ሦስት ዶክተሮች እና አንዲት ነርስን ወደ ጀርመን በመጋበዝ በተለያዩ ሀኪም ቤቶች ተገኝነተው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ አስችሏል። በተለያዩ የጀርመን ከተሞች በመዘዋወር በሀኪም ቤቶች ያለውን አሠራር በመመልከት የበኩላቸውንም ተሞክሮ ያካፈሉት አራቱ የህክምና ባለሙያዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቆይታቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል። በሽኝት መርሃግብሩ ላይ ተገኝቼ በቆይታቸው ያስተዋሉትን እና ስለልምድ ልውውጡ አስተያየታቸውን የጠየኳቸው ዶክተር ጥበቡ አበበ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው። ኔትወርክ አጌይንስት ጀርምስ፤ የጋራ ጥምረት በጀርሞች ላይ የሚለውን መርሃግብር ትኩረት ይገልጹታል።

«ሰዎች ወደ ሆስፒታል ሲመጡ ወይ ኦፕሬሽን ሊደረጉ ይችላሉ፣ ወይ ተኝተው ሊታከሙ ይችላሉ፤ ወይ ሌላ አገልግሎት እያገኙ ከሆስፒታል ፅዱ ባልሆነ አካባቢ ምክንያት በሽታን ሸምተው እንዳይመለሱ፤ እንዳጋጣሚ ሆኖ ሆስፒታል ላይ የሚኖሩ የባክቴሪያ አይነቶች የተለያዩ መድኃኒቶችን የመቋቋም ሁኔታ ስላለ ለዚያ እንዳይዳረጉ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ነው ያተኮረው።»

ሰዎች ለህክምና ሄደው ሌላ በሽታ ሸምተው እንዳይመለሱ የመታከሚያ ክፍሎችና ቦታዎችን ንጽህና መጠበቅ ዋነኛ ሥራ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ጥበበ እንደተመለከቱት በቀላሉ መስተካከል የሚችሉ መኖራቸውን ነው የሚናገሩት።

በቆይታና ጉብኝታቸው ብዙ ነገር በማስተዋላቸውም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የሀኪም ቤታቸውን ንጽህና በማረጋገጥ በኩል የተሻለ ነገር ለመሥራት እንደሚረዳቸውም እምነታቸውን ገልጸውልናል። ዶክተሮች ለኢትዮጵያ የተባለው በጀርመን ሀገር የተቋቋመው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሀኪም ቤት ንጽሕና አጠባበቅን አስመልክቶ ከዚህ ቀደምም ይርጋለም ሆስፒታል ውስጥ የስልጠና መርሃግብር ያካጌደ ሲሆን የተለያዩ የህክምና መሣሪዎች በቀላሉ የሚጠገኑበትን ስልትንም ማሳየቱንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሃኪም ቤቶች የተለመደ ጠረን አለ። ይኽ በጀርመን አይታሰብም። የአቅም ጉዳይ አንዳለ ሆኖ ንጽህናን መጠበቅ ግን በተለይ በሀኪም ቤቶች ሊደረግ ከሚገባው ጥንቃቄ ዋናው ነውና ይኽን ጠረን ማስቀረት ይቻል ይሆን? አልኳቸው። ዶክተር ጥበበ ይቻላል ነው መልሳቸው።

ዶክተሮች ለኢትዮጵያ ማሕበር ለይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታል ከላከው ድጋፍ በከፊልምስል Ärzte für Äthiopien e.v.

ዶክተር ጥበበ እንደሚሉት ቀላል መስሎ በሚታየው እጅ መታጠብ ብቻ ከ70 በመቶ በላይ የሚደርሱ ከሀኪም ቤት ይዘናቸው ልንመጣ የምንችል በጀርም ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን መከላከል ይችላል። ይኽን ጽንሰ ሀሰብ ለህክምና ባለሙያዉም ሆነ ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ የማስተማር ጥረት በመኖሩ በማመልከትም አሁን መሻሻል ይታያልም ባይ ናቸው። በዚህ የልምድ ልውውት ከተሳተፉት መካከል የውስጥ ደዌ እና የልብ ከፍተኛ ሀኪም የሆኑትና የይርጋለም አጠቃልይ ሆስፒታል የቀድሞ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ድንቅዬ አበበ ይገኙበታል። በነበራቸው የአንድ ወር ቆይታ ለእሳቸው ከምንም በላይ ከባለሙያዎች ጋር ትስስር መፍጠር መቻሉ ቀዳሚ ጉዳይ ነው። በተሐዋሲያን አማካኝነት የሚፈጠሩ በሽታዎችን መከላከል ሲባልም ከጽዳት አልፎ ሊታይ የሚገባው ጽንሰ ሃሳብ እንደሆነም ያስረዳሉ።

«ኢንፌክሽንን መከላከል የሆስፒታሉን የትኛውንም የማይነካበት አገልግሎት የለም፤ ቆሻሻ ብቻ አይደለም። እኛ ሀኪሞችን ይመለከታል፤ ዕቃዎችንም እንዲሁ፤ አልጋው ፍራሹ ሁሉ የተበጣጠሰ እና የቆሸሸ አልጋ ላይ ታካሚ ማስተኛት፤ ሊጸዳ የማይችል አይነት አልጋ ላይ እና ፍራሽ ላይ ታካሚ ማስተኛት አስቸጋሪ ነው። የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጥባቸው እንደ ኤክስሬይ፤ አልትራሳውንድ የሚሰጥባቸው እያንዳንዱ ዕቃዎች የራሳቸው የንጽህና ስታንዳርድ አላቸው። እናም በየትኛው ቦታ ቢሆን ኢንፌክሽን ይሄዳል በየትኛውም ዓለም ላይ።»

የተሳካ ባሉት የጀርመን ቆይታቸውም ከተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች ጋር የተለዋወጡትን ተሞክሮ እና ልምድ ወደ ሆስፒታላቸው በመውሰድ ተግባራዊ ለማድረግ መነሳሳትን እንደፈጠረባቸውም ሳይገልጹ አላለፉም። በተሐዋሲያን አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ነገር አይደለም የሚሉት ዶክተር ድንቅዬ መሠረታዊው ነገር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ መሆኑን ይገልጻሉ። በጤና ጥበቃ የተገለጹት የእጅ ንጽሕናን የመጠበቂያ ስልቶችን ተግባራዊ ማድረጉ በራሱ ዋነኛ መንገድ እንደሆነም አስታውሰዋል። ዶክተር መሰለ ተገኝ በይርጋለም ሆስፒታል አጠቃላይ የቀዶ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ በበኩላቸው ሰዎች ለኢንፌክሽን ወይም ለተለያዩ ህመሞች ከሚጋለጡባቸው ቦታዎች አንዱ የቀዶ ህክምና ክፍል መሆኑን ነው የገለጹልን።

«እኔ ብዙ ጊዜ ያለሁት ያው ኦፕራሲዮን ክፍል እና እዚያ አካባቢ አንድ ኢንፌክሽን ተፈጠረ ሲባል ምክንያቱን ለማወቅ ሁሉንም ሂደት ማየት አለብን። ዕቃዎች እንዴት ታጠቡ? ባለሙያዎቹ እንዴት ነው የያዙት? እና ከዚያ በኋላ ኦፕራሲዮን ሲደረግ ሀኪሙ ትክክለኛውን ሁኔታ ጠብቆ ሠርቷል ወይ? ከቀዶ ህክምናው በኋላ ደግሞ በሽተኛው ወደ መኝታ ክፍል በትክክል ነው የተወሰደው? ቁስሉ ተነካክቷል? ባልተፈለገ ጊዜ ቁስሉ ተነካክቶ ከሆነ ደግሞ ያም አንድ ምክንያት ነው። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ሂደቶች የት ጋር ችግር እንዳለ ለማወቅ ሁሉን ነገር ለማወቅ ጥናት ማድረግ አለብን።»

ለአንድ ጀርመን የቆዩት የህክምና ባለሙያዎች ከአስተናጋጆቻቸው ጋር ምስል Shewaye Legesse/DW

እንዲህ ያለውን ነገርም በመከታተል ምን ያህል ትክክለኛው የጽዳት ጥንቃቄ እንደተደረገ መመልከት ይቻላልም ባይ ናቸው። ብዙዎች ሀኪም ቤት ውስጥ ለጤና እክል ሊሆኑ ስለሚችሉ ተሐዋስያን ጉዳይ እውቀቱ ቢኖራቸውም ጥንቃቄ ለማድረግ የሚያውቁትን ሥራ ላይ ካላዋሉት ውጤት እንደሌለውም አመልክተዋል። በጀርመን ሀገር ሃኪም ቤቶች የቀዶ ጥገና ክፍል እንደሚቆለፍ፤ የሀኪሞቹም መግቢያ እና መውጫቸው የተለያየ መሆኑ ቀላል ሆኖ ነገር ግን እኛ ጋር አናስተውለውም ያሉት ዶክተር መሰለ፤ ይኽን ማድረጉ ግን ከባድ እና ወጪ የሚጠይቅ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። አስታማሚ ነርሶች በጀርመን የጤና ጥበቃ ዘርፍ ትልቅ ሚና አላቸው። የይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ኂሩት ፍሰሀም በቆይታቸው ይህን አስተውለዋል። ምንም እንኳን የነርሶቹ የሥራ ኃላፊነት ቀላል የሚባል ባይሆንም የሚሠሩበት ሁኔታ የተቀናጀ እና የተመቻቸ በመሆኑ በተዘዋወሩባቸው ሀኪም ቤቶች ሁሉ ባለሙያዎቹ ደስተኛ ሆነው ሲሰሩ እንዳስተዋሉ ገልጸውልናል።

«እኛ ሀገር ደግሞ ስንሄድ ብዙ ያልተመቻቸልን ነገር አለ። ግን ባይኖርም እንኳን ነገሮችን እኛ ራሳችን እያስተካከልን የምንሠራባቸው ነገሮች ደግሞ ይበልጥ እኛ ከዚህ በላይ የተመቻቸ ነገር ቢኖር ደግሞ ከእነሱ ጋር የሚስተካከል አገልግሎት እንሰጣለን ብዬ አስባለሁ።»

ነርሶች አስታማሚዎች እንደመሆናቸው ከታማሚው ጋር ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ አስታማሚዎች ጋርም በቀጥታ የሚገናኙት እነሱ ናቸው። በጀርመን ሀኪም ቤቶች የቤተሰብ አስታማሚዎች ቁጥር ውሱን እከመሆኑ ሌላ ለማደር ፈቃድ የለም። ኢትዮጵያ የሚታየው ከዚህ ይለያል። ሲስተር ኂሩት፤

«ንጽሕናቸውን በጠበቀ ሁኔታ አገልግሎታቸውን በጥራት የሚሰጡት አስታማሚ ስለማይገባ ነርሶቹ ራሳቸው ናቸው የሚያስታምሙት። እኛ ሀገር ላይ ስንሄድ ደግሞ የባለሙያ እጥረትም ስላለ የጤናው ስርዓት የተስተካከለ ነገር ስለሌለው አሁን ለአንድ ታማሚ ክብካቤ ለማድረግ ቤተሰብ ነው እኛን እያገዘን የምንሠራው።»

አቅመ ደካሞች ሲሆኑ አሳታሚዎች የሚያስፈልጉት አጋጣሚ መኖሩን ያመለከቱት የህክምና ባለሙያዋ ካለው የባለሙያ እጥረት ሙሉ ለሙሉ ይቅር ባይባል እንኳን ቁጥሩን መቀነስ እንደሚቻል ግን ያምናሉ። አንድ ሀኪም ቤት ጽዱና ምቹ ለማድረግ ቴክኒዎሎጂ የግድ አይስፈልግም ያሉት ሲስተር ኂሩት ዋናው ከልብ ተነሳሽነት ኖሮ የሰዎችን አመለካከት መቀየር መቻል መሆኑንም ገልጸዋል። የህክምና ባለሙያዎቹ ወደ ጀርመን መጥተው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያመቻቸው የዶክተሮች ለኢትዮጵያ መሥራች ወይዘሮ ትዕግሥት ላቀው ኔትወርክ አጌንስት ጀርምስ ፕሮጀክት ከጀርመን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጂአይዜድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚካሄድ ገልጸውልናል።

ወይዘሮ ትዕግሥት ላቀው፤ ዶክተሮች ለኢትዮጵያ ማሕበር መሥራችምስል Ärzte für Äthiopien e.v.

ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ አራት የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ጀርመን በመጋበዝ የተጀመረው ይኽ የልምድ ልውውጥም በቀጣይ በመጪው ጥር እና የካቲት ወር ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ እንደሚቀጥልም ገልጸውልናል። ዶክተሮች ለኢትዮጵያ እስካሁን ስድስት ኮንቴይነር ለህክምና የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታል መላኩን የተናገሩት ወይዘሮ ትዕግሥት እንዲህ ያለው ትብብር እንዲቀጥል የተለያዩ ጀርመናውያን የህክምና ባለሙያዎች፤ ሃኪም ቤቶች እና በጎ ፈቃደኞች ከጎናቸው እንዳሉም አመልክተዋል። በነገራችን ላይ  ሲዳማ ክልል የሚገኘው ይርጋዓለም ሆስፒታል በዓመት እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ ታማሚዎችን በተመላላሽነት ያስተናግዳል። በዓመት በድንገተኛ ክፍሉ እስከ ሰባት ሺህ፤ እስከ ስምንት ሺህ ለሚገመቱ ተኝተው ታካሚዎችም አገልግሎት ይሰጣል። ከዚህም ሌላ ሆስፒታሉ በአንድ ዓመት ከ1,400 እስከ 1,500 የቀዶ ህክምና እንደሚያካሂድ የሀኪም ቤቱ ሜዲካል ዳይሬክተር ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሆስፒታሎች አሠራር አንድ ትልቅ ሀኪም ቤት በሥሩ የመጀመሪያ ደረጃ እና አነስተኛ ሆስፒታሎች እንደሚኖሩት የገለጹት ዶክተር ጥበበ አበበ ይርጋዓለም ሆስፒታልም በዕቃም ሆነ ክትትል በማድረግ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ሦስት ሆስፒታሎች እና አራት ጤና ጣቢያዎች በስሩ እንዳሉም ተናግረዋል። ሀኪም ቤቱ በሚችለው መጠን አገልግሎቱን አስፍቶ ለማዳረስ እየሞከረ መሆኑን ያመለከቱት ሜዲካል ዳይሬክተሩ እንደ ዶክተሮች ለኢትዮጵያ ሌሎች ወገኖችም በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉለትም ጠይቀዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW