1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሓት ድርድር ተግዳሮቶች

እሑድ፣ ነሐሴ 1 2014

ህወሓት ከድርድሩ አስቀድሞ ሊሟሉ ይገባቸዋል ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በቅርቡ በድጋሚ አስታውቋል። ፓርቲው ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ፣ የትግራይ ሠራዊት ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብ ከድርድሩ አስቀድሞም በትግራይ ከጦርነቱ በኋላ የተቋረጡት የባንክ ቴሌኮምኒኬሽን የኤሌክትሪክና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲቀጠሉ የሚሉት ይገኙበታል።

Infografik Karte Äthiopien EN

የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሓት ድርድር ተግዳሮትና የሰላሙ ተስፋ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለማብቃት ፈቃደኛ መሆናቸውን ካሳወቁ  ቆይተዋል። ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ይፋ ካደረጉም  ውሎ አድሯል። በየበኩላቸው ተደራዳሪዎችንም መሰየማቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በድርድሩ የሚወክሉትን ባለሥልጣናት ማንነት ሲያሳውቅ ህወሓት ግን ተደራዳሪዎችን መሰየሙን ገልጾ ማንነታቸውን ግን ከማሳወቅ ተቶጥቧል። ይሁንና ከወራት በፊት በተናጠል የግጭት ማቆም ውሳኔዎችንም ያሳለፉት ሁለቱ ወገኖች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚሰጧቸው መግለጫዎች ድርድሩን በሚሸመግለው ወገን ማንነት ላይ የተለያየ አቋም የያዙ ይመስላል። የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሮች በሙሉ በአፍሪቃ ኅብረት ሸምጋይነት መመራት አለበት ሲል ፣ህወሓት ደግሞ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ድርድሩን እንዲያስተባብሩ እንደሚፈልግ ተናግሮ ነበር። ሁለቱን ወገኖች በተናጠል ሲያነጋግሩ የቆዩት የአፍሪቃ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ለኢትዮጵያ መንግሥት ያደላሉ ያለው ህወሓት አደራዳሪነታቸውን አለመፈለጉን አስታውቋል። ከዚህ ሌላ ህወሓት ከድርድሩ አስቀድሞ ሊሟሉ ይገባቸዋል ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎችም በቅርቡ በድጋሚ አስታውቋል።  የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በዚሁ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ካስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ፣ የትግራይ ሠራዊት ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብ ከድርድሩ አስቀድሞም በትግራይ ከጦርነቱ በኋላ የተቋረጡት የባንክ ቴሌኮምኒኬሽን የኤሌክትሪክና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲቀጠሉ፣ የሚሉት ይገኙበታል። የሰላም ሂደቱ በዚህ ደረጃ ላይ በሚገኝበት በዚህ ሳምንት የአሜሪካንና የአውሮጳ ኅብረት ልዩ ልዑካን  በአፍሪቃ ኅብረት አስተባባሪነት ድርድር እንዲጀመር ለማበረታታት በሚል አዲስ አበባም መቀሌም በመሄድ የሁለቱን ወገኖች ባለሥልጣናት አነጋግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትንና ህወሓትን ለማደራደር የተጀመረው ጥረት፣  ተግዳሮቶቹና የሰላሙ ተስፋ የዛሬው እንወያይ ትኩረት ነው ።በዚህ ርዕስ ላይ የሚወያዩ ሦስት እንግዶች ጋብዘናል እነርሱም ዶክተር ኬረዲን ተዘራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ   የስነ ሰብና የሕግ ብዝሀነት ተመራማሪ ፣ አቶ ሞገስ ዘውዱ  የሕግ ዲፕሎማሲና  የግጭት አፈታት ምሁር በአሁኑ ጊዜ ቭየና ኦስትሪያ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የሰላም ተቋም ተመራማሪ እንዲሁም  ፕሮፌሰር ሙሉጌታ   ገብረ እግዚአብሔር   በሳውዝ ካሮላይና ዩኒቨርስቲ የኅብረተሰብ  ጤና ተመራማሪ እና  «የትግራይ ፍትህና ፀጥታ» የተባለው ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማኅበር ም/ፕሬዝዳንት ናቸው ። 

ምስል Eduardo Soteras/AFP

ሙሉውን ውይይት ለማዳመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማዕቀፍ ይጫኑ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW