የኢትዮጵያ መንግሥትና የIMF ድርድር ያለዉጤት አበቃ
ረቡዕ፣ መጋቢት 25 2016የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ባለሙያዎች አዲስ አበባ ዉስጥ ለተከታታይ ቀናት ያደረጉት ድርድር ያለሥምምነት አበቃ። ሁለቱ ወገኖች ሲደራደሩ የነበረዉ ኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ አበዳሪ ድርጅት በጠየቀዉ የ3.5 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ድርጅቱ ባቀረባቸዉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ነበር። የድርድሩ መክሸፍ ኢትዮጵያ የገጠማትን የኤኮኖሚ ችግር ለማቃለል ይረዳል የተባለዉን ብድር ከማዘግየቱ በተጨማሪ «የፓሪስ ክለብ» የተባለዉ የአበዳሪ መንግሥታት ስብስብ የሰጣትን ዕዳ የመክፈያ እፎይታ ሊያቋርጠዉ ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ ዶክተር አብዱል መናን መሐመድን ፣ ተደራዳሪዎች ከተፋረሱባቸዉ ምክንያቶች አንዳዶቹን «የሚጠበቅ» ይሏቸዋል።
የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው IMF ለኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ምርሃግብሮችን እንዴት ሊደግፍ እንደሚችል ባሄዱት ውይይት ትርጉም ያላቸው መሻሻሎች መኖራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። በሚያዝያ ወርም ቀጣይ ውይይት ዋሽንግተን ላይ እንደሚኖርም አስታውቋል። የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ጋር እስከ ያለፈው እሑድ ድረስ ሥምምነት ላይ መድረስ ማግኘት ካልቻለ በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ዕዳ ክፍያውን ለማዘግየት የተደረሰው ስምምነት ሊሰርዙ እንደሚችሉ ሮይተርስ አመልክቷል። እንዲያም ሆኖ የፓሪስ ክለብ አባላት የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ስለማራዘማቸው የተነገረ ነገር የለም። ከቻይና ጋር ግን ኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ ማራዘሚያ ስምምነት ባለፈው ዓመት ተፈራርማለች። ኢትዮጵያ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ዕዳቸውን በወቅቱ መክፈል ካልቻሉ የአፍሪቃ ሃገራት ሦስተኛዋ መሆኗ ተነግሯል።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ