የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኞች ከሚጠበቀው የደመወዝ ጭማሪ ለምን ተስፋ አጡ?
ረቡዕ፣ መስከረም 15 2017በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኘው የመሐል ሜዳ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ከመስከረም 1 ቀን 2017 ጀምሮ ታሳቢ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የደመወዝ ጭማሪ የበረታባቸውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ያግዛቸው እንደሁ እርግጠኛ አይደሉም።
“በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብሎ ሲነገር ነጋዴው ሒሳቡን ሲያሰላ ነው ያደረው። ግማሹም ያለውን መከዘን ነው የያዘው” የሚሉት የመሐል ሜዳ ነዋሪ በከተማቸው የሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን ታዝበዋል። “ደመወዝ ተጨመረ ሲባል 45 ብር የነበረው ሳሙና 55 ብር ገባ፤ 50 የነበረው 60 ብር ገባ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
ሠራተኛው “እስካሁን ድረስ እጁ ላይ የገባ የተጠቀመው ነገር የለም። ተስፋ የሚያደርገው እና የተወራው የደመወዝ [ጭማሪ] እንዳሰበው አይደለም” ሲሉ የመንዝ ጌራ ወረዳ ጽህፈት ቤት ባልደረባ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ የሚያስከትለውን ጫና ለማገዝ የደመወዝ ጭማሪ ይፋ ሲያደርግ በአፋር ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች የአንዱ ባልደረባ የሆኑት ነርስ ተስፋ ነበራቸው። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ነርስ የደመወዝ ጭማሪው “በአንጻራዊነት” የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ያግዛል የሚል ተስፋቸው ግን በሒደት መንምኗል። ጉዳዩ ገበያውን እንዳናረው የታዘቡት የዱብቲ ነዋሪ ደመወዝ ጭማሪው ቀርቶ “ገበያው ቢስተካከል” ይመርጣሉ።
“[ደመወዜ] ለምግብ ለራሱ አይሆንም እኮ፣ በቀን 200 ብር ገደማ ነው” የሚሉት ነርስ ምሳ እና እራት ሽሮ ቢመገቡ በቀን 200 ብር እንደሚያወጡ አስረድተዋል። ደመወዛቸው ልጆች ማሳደጊያ እና መጓጓዣን ጨምሮ በኑሯቸው የሚያስፈልጓቸውን ሌሎች ወጪዎች መሸፈን የሚችል እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉትን ነርስ ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎች፣ መምህራን እና ሌሎች በቋሚ ገቢ የሚተዳደሩ ሠራተኞች ባለፉት ዓመታት እስከ 38 በመቶ ባሻቀበው የዋጋ ግሽበት በኃይል ሲፈተኑ ቆይተዋል።
መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር የብድር ድጋፍ ተግባራዊ የሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ በጥር 2017 ገደማ የዋጋ ግሽበት ከ30 እስከ 35 በመቶ ሊያደርሰው ይችላል።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ወርሐዊ ደመወዛቸው የወጪያቸውን “20 በመቶ ይደጉማል” የሚል ዕምነት የላቸውም። የሚከፈላቸው ደመወዝ “ፍጹም በቂ አይደለም” የሚሉት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ መምህራን “ከድሕነት ወለል በታች” ለመኖር መገደዳቸው በሙያቸው ላይ ትኩረት አድርገው እንዳይሰሩ ጭምር ማድረጉን ይናገራሉ።
“አብዛኞቻችን ከዋናው የማስተማር ሥራችን ይልቅ ወደ ሌላ ተጨማሪ ገቢ የምናገኝባቸው ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገናል” የሚሉት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ “መምህርነት እንደ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ተደራቢ ሥራ” የመሆን አዝማሚያ መታየቱ እጅግ ያሳስባቸዋል።
“ይኸ በዋናነት የምናገኘው ገቢ አመርቂ ሆኖ ኑሯችንን ለመደጎም በቂ ባለመሆኑ የተከሰተ ነው” የሚሉት መምህር “ኤኮኖሚው በጦርነት የታመሰ፣ ምርታማነቱ እየቀነሰ፣ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ” መሔዱ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ተገንዝበዋል።
“የመንግሥት የኤኮኖሚ አስተዳደር ያሉበት ውስንነቶች በፈጠሯቸው ጉድለቶች ግሽበቱ እያደገ ነው የሔደው” የሚሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ለመምህራን “የቤት ኪራይ ማግኘት፤ ልጆችን ማስተማር፣ የትምህርት ቤት እና የትራንስፖርት መክፈል ከባድ” መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከመስከረም 1 ቀን 2017 ጀምሮ የሚታሰብ የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ ቢዘጋጅም የመንዝ ጌራ ወረዳው ነዋሪ፣ የዱብቲው ነርስም ይሁኑ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲው ባልደረባ ይኸ ነው የሚባል ፋይዳ ያመጣል የሚል ዕምነት አጥተዋል። እምነታቸው የተሸረሸረው በመንግሥት የተዘጋጀው የደመወዝ ጭማሪን የሚያሳይ ሰነድ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተሰራጭቶ ከተመለከቱት በኋላ ነው።
በገንዘብ ሚኒስቴር እና በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን “ተጠንቶ እና ተደግፎ” በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ የቀረበው ሰነድ ትክክለኛ መሆኑን ሁለት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የመንግሥት ባለሙያዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ዶይቼ ቬለ ከሁለቱ የመንግሥት ተቋማት ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
በሰነዱ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ለ2.4 ሚሊዮን ሠራተኞች “የኑሮ ውድነት ጫና መደጎሚያ” የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ 91.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ያስፈልገዋል። የደመወዝ ጭማሪው ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ባገኘችው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና ዕርዳታ የሚሸፈን ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ለደመወዝ ጭማሪ የሚመደበውን ጨምሮ 551 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ ባለፈው ሐምሌ ወር አስታውቀዋል። አቶ አሕመድ ሽዴ በጻፉት ደብዳቤ አባሪ ተደርጎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተላከው ሰነድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚመሩት ማክሮ ኤኮኖሚ ኮሚቴ የታየ ነው።
የብርን የመግዛት አቅም በኃይል ባዳከመው የኤኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት “የመንግሥት ሠራተኞች በተለይም ዝቅተኛ የደመወዝ ተከፋይ ሠራተኞች በኑሮ ውድነት እንዳይጎዱ” የደመወዝ ጭማሪው እንደሚደረግ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የተጻፈው ደብዳቤ ይጠቁማል።
አቶ አሕመድ በደብዳቤው የደመወዝ ጭማሪው የመንግሥት ሠራተኞች “ሊደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና በመጠኑም ቢሆን ለመቋቋም እንዲችሉ” ይረዳል የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል።
የተዘጋጀው ሰነድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔን ይሁንታ አግኝቶ ከጸደቀ 1,100 ብር የሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች 3,660 ብር ተጨምሮላቸው ደመወዛቸው ወደ 4,760 ብር ከፍ ይላል። ዐቢይ “በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም” ያሉት 332% ጭማሪ የሚደረገው በደረጃ 1 ለተደለደሉ የደመወዝ ስኬል ተከፋዮች ነው።
ጭማሪው በመንግሥት የደመወዝ ስኬል ለ22 የሥራ ደረጃዎች የሚደረግ ነው። የሠራተኞች ነባር ደመወዝ እየጨመረ በሔደ ቁጥር ጭማሪው ይቀንሳል። ከ1 እስከ 6 ባሉት የሥራ ደረጃዎች በመንግሥት የተቀጠሩ ሠራተኞች ከ332 እስከ 94% የደመወዝ ጭማሪ ያገኛሉ።
በመንግሥት የደመወዝ ስኬል 11ኛ የሥራ ደረጃ ላይ የተመደቡት የአፋር ክልል ነርስ 36.7 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ይደረግላቸዋል። በነርሲንግ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁት ባለሙያ የሚደረግላቸው የደመወዝ ጭማሪ 2,277 ብር ይሆናል።
ገንዘቡ “እጅ ላይ ሳይገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ [ደመወዝ] ይጨመራል ስላለ ብቻ [በገበያ] ሁሉም ነገር እዚያ ላይ ወጣ” የሚሉት ነርስ “የጤና ባለሙያም ሆነ ሌላው [የመንግሥት ሠራተኛ] አሁንም እዚያው ፈተና ውስጥ ነው ያለው” የሚል አቋም አላቸው።
ከፍተኛው 20,468 ብር የሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ 5 በመቶ ብቻ ነው። በሰነዱ መሠረት በደመወዝ ስኬል 22ኛ የሥራ ደረጃ ላይ የተደለደሉ ሠራተኞች 1,023 ብር ጭማሪ ይደረግላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ የወሰነው የብርን የመግዛት አቅም በከፍተኛ መጠን እየተዳከመ እንዲሔድ ያደረገ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ገቢራዊ ባደረገ ማግሥት ነው። በማሻሻያው መሠረት መንግሥት የኤሌክትሪክ ታሪፍን በየሦስት ወሩ ቢያንስ በ10 በመቶ ይጨምራል። ይኸ የፖሊሲ ለውጥ ከአዲስ አበባ እስከ አሶሳ፤ ከመቐለ እስከ ጅግጅጋ የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።
በመንዝ ጌራ ወረዳ የሚኖሩት ሠራተኛ የመንግሥት ገበያውን የማረጋጋት “አቅም የመነመነ ነው” ሲሉ ይነቅፋሉ። የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መዳከም እና ሀገሪቱን የሚያብጡ ግጭቶች ያስከተሉት ዳፋ የመንግሥት “ሠራተኛው በችግር አረንቋ ውስጥ እንዲማቅቅ” አድርገውታል የሚል ዕምነት አላቸው።
“ደመወዝን በመጨመር ብቻ ገበያን ማረጋጋት አይቻልም። ይኸን ገበያ ማረጋጋት የሚቻለው ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር ነው። አሁን ባለው ነባሪዊ ሁኔታ ግን የአገሪቷ ምርት ጨምሯል የሚል ዕምነት የለኝም” ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን በገበያው የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ለመቋቋም 10,000 ብር የሚከፈላቸው ሠራተኞች ደመወዝ ከ18,000 እስከ 19,000 ብር ከፍ ማለት ነበረበት ሲሉ የሚሞግቱት የመሐል ሜዳ ነዋሪ “ሁሉም በተስፋ ነበር የሚጠብቀው። አሁን ግን በአጠቃላይ ተስፋው የተሟጠጠ ነው” ሲሉ አቋማቸውን አስረድተዋል።
መንግሥት ያዘጋጀው የደመወዝ ጭማሪ ለዝቅተኛ ተከፋይ “ሠራተኛ የተወሰነ የተስፋ ጭላንጭል የሰጠ” እንደሆነ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲው መምህር ይስማማሉ። የደመወዝ ልዩነትን “ለማቀራረብ” እና “ድሕነትን ለመቀነስ” መሞከሩ በበጎ የሚያነሱት ነው።
መካከለኛ እና ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች በአንጻሩ ፋይዳ ያለው ጭማሪ እንደማያገኙ የሚጠቅሱት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ለመምህራን “ችግሩን የሚያባብስ እንጂ መፍትሔ የሚሆን አይደለም” ሲሉ ይተቻሉ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ከሁለት ወራት በፊት ከመምህራን ጋር ፊት ለፊት ባደረጉት ውይይት የመምህራንን ደመወዝ ለማሻሻል በሲቪል ሰርቪስ የሚመራ ጥናት እየተከናወነ እንደሆነ መናገራቸውን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው ያስታውሳሉ።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ጥናቱ በህዳር ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ መናገራቸውን የገለጹት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ “መምህራን የሚፈልገውን ያህል የደመወዝ ለውጥ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቀው በትምህርት ሚኒስቴር እና በሲቪል ሰርቪስ ተጠንቶ ይመጣል በተባለው መዋቅር ነበር” ሲሉ አስረድተዋል።
መምህሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያደርገዋል ተብሎ የሚጠበቀው የደመወዝ ጭማሪ በትምህርት ሚኒስቴር እና በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እየተከናወነ ነው የተባለውን ጥናት አቋርጦታል የሚል ዕምነት አላቸው። “ይኸኛው ደግሞ ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም። የምንጠብቀው ለውጥ እየተከናወነ አይደለም። ስለዚህ በዚህኛው መንገድ ላይ ተቋርጧል እንደማለት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥት ለደመወዝ ጭማሪ ከመደበው 91 ቢሊዮን 439 ሚሊዮን ገደማ ብር መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው ለሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የታቀደው ነው። የመንግሥት 2 ሚሊዮን 304 ሺሕ 78 ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ 71.8 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ ይጠይቃል።
መንግሥት የደመወዝ ጭማሪውን ሥራ ላይ ካዋለ ለክልል ፖሊስ ሠራዊት 9.5 ቢሊዮን፣ ለመከላከያ ሠራዊት 6 ቢሊዮን፣ ለፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን 1.7 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ይጠይቀዋል። በፌድራል እና በክልል ለሚገኙ 56, 023 ተሿሚዎች እና የሕዝብ ተመራጮች የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ በዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ የሚያስከትል ነው። ከ25,000 ብር በላይ የሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ አይደረግላቸውም።
ለመንግሥት ሠራተኞች የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ እና በገበያው የሚያስከትለው አንዳች ለውጥ የግሉ ዘርፍ ተቀጣሪዎችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚጫን ይሆናል። መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የመወሰን ሥልጣን የተሰጠውን ቦርድ እንዲያቋቁም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ግፊት እያደረገ ይገኛል። ከ800 እስከ 2000 ብር የሚከፈላቸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የግል ፋብሪካዎች የተቀጠሩ ሠራተኞች በገበያው በተፈጠረ የዋጋ ጭማሪ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አያሌው አሕመድ “የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከተጨመረላቸው የእነዚህኞቹ ደግሞ ደመወዝ ሳይጨመር በመካከል የሚመጣው ጉዳት ከፍተኛ ስለሚሆን፤ ገበያው ዕኩል ስለማያስተናግዳቸው የእነዚህኞቹም ሠራተኞች በጣም ፈጠን ባለ መልኩ ውሳኔ ሊያገኝ የሚችልበትን መንገድ እንደ ኮንፌዴሬሽን በእኛ በኩል አስፈላጊውን የሆነ ግፊት እያደረግን ነው ያለንው” ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ከደመወዝ ላይ የሚቆረጠው የታክስ መጠን ማሻሻያ እንዲደረግበት ለሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጥያቄ እንዳቀረበ አቶ አያሌው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። መንግሥት ጥያቄውን ተቀብሎ ነባሩን የደመወዝ ተከፋይ የገቢ ግብር ቢያሻሽል “ለኑሮ ውድነቱ ማስተንፈሻ ሊሆን እንደሚችል” የኮንፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝደንት እምነት አላቸው።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ