የኢትዮጵያ መንግሥት በትራምፕ 10% ታሪፍ ላይ ከአሜሪካ እንዲደራደር ባለሙያዎች መከሩ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 7 2017
ቻይና፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገራት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጣሉባቸው ታሪፍ ላይ ድርድር በማካሔድ ላይ ይገኛሉ። ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ ሀገራት በአንጻሩ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ባደረጉት ድርድር ሥምምነት ላይ ደርሰዋል።
በፕሬዝዳንቱ ውሳኔ መሠረት የኢትዮጵያ ሸቀጦች ከነሐሴ 1 ቀን 2017 ጀምሮ ወደ አሜሪካ ሲገቡ 10 በመቶ ታሪፍ ይከፈልባቸዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ጉባኤ የማምረት አቅም እና ዘላቂ ልማት መምሪያ የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ ሙሴ ደለለኝ (ዶ/ር) እና የሙያ ባልደረቦቻቸው የኢትዮጵያ መንግሥትም የትራምፕ አስተዳደር በሀገሪቱ የወጪ ንግድ ሸቀጦች ላይ የጣለውን ታሪፍ እንዲገመግም በመረጃ ላይ የተመሠረተ ድርድር ሊያደርግ ይገባል የሚል አቋም አላቸው። ዶክተር ሙሴን ጨምሮ አራት ባለሙያዎች የዩናይትድ ስቴትስ ታሪፍ በኢትዮጵያ የንግድ እና የልማት ዕድሎች ላይ ያለውን አንድምታ የሚፈትሽ ጥናት አሳትመዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው 10 በመቶ ታሪፍ “ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ መንግሥት ከአሁኑ ንቁ የሆነ ድርድር ከአሜሪካ ጋር ማድረግ አለበት” የሚሉት ዶክተር ሙሴ “ጥናቱ ለንግድ ድርድር መንግሥት እንዲጠቀምበት ተብሎ የተሠራ እና የተዘጋጀ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ ሲጥሉ በአሜሪካ እና ሌሎች ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ማስተካከል የሚል ማመካኛ ቢያቀርቡም ይህ ለኢትዮጵያ አይሰራም። ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ ሚዛን ወደ አሜሪካ ያደላ ነው። ዶክተር ሙሴ እንዲያውም “ኢትዮጵያ ከማንኛውም ከበለጸጉ ሀገሮች ጋር ትርፍ የንግድ ሚዛን ኖሯት አያውቅም” ሲሉ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ሸቀጦችን “በዐይነት እና በብዛት ያላዘጋጀች” መሆኗ ትራምፕ በጣሉት ታሪፍ ምክንያት ለከባድ ተጽዕኖ ተጋላጭ ያደርጋታል። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከሀገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት (GDP) ያለው ድርሻ 8% እንኳ እንዳልሞላ የሚናገሩት ዶክተር ሙሴ የ2023 መረጃ እያጣቀሱ 21 በመቶ ከደረሰው ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ ሀገራት አኳያ የሚያንስ እንደሆነ ይሞግታሉ።
የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የወጪ ንግድ “ከ30 ዶላር አይበልጥም” የሚሉት ዶክተር ሙሴ ይህ ከጋና፣ ግብጽ፣ ናይጄሪያ እና ኬንያ በታች እንደሆነ ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር እና የቆዳ ስፋት አንጻር የወጪ ንግድ በሀገሪቱ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርትም ይሁን በልማቷ ውስጥ “ያለው ሚና በጣም የቀነጨረ ነው ማለት ይቻላል” ሲሉ ይተቻሉ።
የትራምፕ 10 በመቶ ታሪፍ በኢትዮጵያ ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ሌላው ምክንያት ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸው ሸቀጦች ዐይነት በቁጥር ትንሽ መሆኑ ነው። ዶክተር ሙሴ እንደሚሉት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 95 በመቶው ከ10 ምርቶች የሚገኝ ነው። ይህ በአማካኝ እስከ 250 የሚደርሱ ምርቶች በዓለም ገበያ ከሚሸጡ ታዳጊ ሀገሮች በታች ነው።
በዓለም ገበያ ኢትዮጵያ የምትሸጣቸው የወጪ ንግድ ሸቀጦች ቁጥር ውስን በመሆናቸው “ትንሿ ለውጥ በንግዳችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ሲሉ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ታሪፍ የሚያስከትለው ዳፋ ቀላል እንደማይሆን ዶክተር ሙሴ ገልጸዋል።
በጎርጎሮሳዊው 2024 ኢትዮጵያ እና አሜሪካ 4.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንግድ ልውውጥ እንደነበራቸው የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ተወካይ ቢሮ መረጃ ያሳያል። ዶክተር ሙሴ እንደሚሉት በሀገር ደረጃ በዋጋ ከስዊትዘርላንድ እና ኔዘርላድስ በመቀጠል አሜሪካ ሦስተኛዋ የንግድ አጋር ናት።
“ሌሎች ሀገሮች እስከ 100 ሀገሮች ነው ኤክስፖርት የሚያደርጉት። ከአምስት እና ከስድስት የማይበልጡ ሀገሮች አይደሉም ከ80 እስከ 90 ኤክስፖርታችንን የሚቀበሉት። ስለዚህ አንዷ ሀገር ላይ የሚከሰተው ለውጥ በማናቸውም በምናቀርባቸው ምርቶች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከፍ ያለ ነው የሚሆነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የምትልከው የወጪ ንግድ በዓመት በ4.8 በመቶ እያደገ መምጣቱን የባለሙያዎቹ ጥናት አሳይቷል። ቡና፣ የቅባት እና የጥራጥሬ እህሎች እንዲሁም ጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶችን ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ገበያ ትልካለች። ቡና ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው የወጪ ንግድ ሸቀጦች እስከ 35 በመቶ ድርሻ አለው።
አሜሪካ ከዓለም ገበያ ከምትሸምተው ቡና ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ቪየትናም እና ሖንዱራስ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ለአሜሪካ ገበያ ቡና በማቅረብ ቀዳሚ የሆነችው ብራዚል በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር 50 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባታል። ቪየትናም 20 በመቶ ታሪፍ ሲጣልባት የኮሎምቢያ እና የሖንዱራስ ሸቀጦች እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ወደ አሜሪካ ገበያ ሲገቡ 10 በመቶ ቀረጥ ይጠብቃቸዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ዋናው ባይሆንም ጠቃሚ ገበያ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ሙሴ የትራምፕ ታሪፍ ተጽዕኖ እንደሚያርፍበት ያስረዳሉ። “ታሪፉ ዋጋ ይጨምራል፤ ፍላጎቱን ይቀንሳል። የአቅርቦት እና የፍላጎት ሚዛን ያዛባል። ኢንቨስተሮች ወደዚያ ሀገሮች እንዳይሔዱ ያደርጋል” የሚሉት ዶክተር ሙሴ “ተጽዕኖው ብዙ ነው። ድሕነት ይመጣል፤ ሥራ አጥነትን ያስከትላል። በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል” የሚል ሥጋት አላቸው። “ቡና ራሱ ከዚህ [ከታሪፍ] ተጎጂ ነው። ከሌሎቹ ጋር የመወዳደር አቅማችን በጣም ጠንካራ ስላልሆነ ገበያ የምናጣበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2017 በዓለም ገበያ 470 ሺሕ ቶን ቡና ሸጣ ከ2.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳገኘት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይፋ አድርጓል። የአሜሪካ ገበያ ከዚህ ውስጥ ወደ 36 ሺሕ ቶን ወይም ስምንት በመቶ ገደማ ብቻ ድርሻ እንዳለው የገለጹት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ “ለብቻህ የመጣ ዕዳ ቢሆን 10% ታሪፍም ይጎዳናል እንላለን። ግን ለብቻ የመጣ ዕዳ ስላልሆነ፤ እኛን በተለየ ሁኔታ ከነበርንበት ቦታ አያወርደንም” የሚል እምነት አላቸው።
“ይኸ ታሪፍ የሚጎዳው የአሜሪካንን ሸማቾች ነው። ምንክንያቱም ይገዛ የነበረውን አንድ ፓውንድ ቡና ወይም አንድ ኪሎ ቡና ታሪፍ በመጨመሩ ለሸማቹ ተወዶ ነው የሚጠብቀው” የሚሉት አቶ ግዛት በእርግጥ ዋጋ ሲጨምር ፍላጎት ሊቀንስ እንደሚችል ይስማማሉ። “ለእኛ ግን ለሻጩ ወደ አሜሪካ ገበያ ከብራዚል እና ከሌሎች ጋር ተወዳድረን እንገባ የነበረው እነሱ ከፍ ያለ ታሪፍ ስለተጣለባቸው ለእኛ የተሻለ፤ ሰፋ ያለ ዕድል ነው የተከፈተልን” ሲሉ ተናግረዋል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የጣለው ታሪፍ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ገበያ በምትሸጣቸው የቅባት እህሎች እና አበባ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የዶክተር ሙሴ እና የሙያ ባልደረቦቻቸው ጥናት ይጠቁማል። ይሁንና ጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶች ለሚያመርቱ የኢትዮጵያ ፋብሪካዎች በአንጻሩ የተከፈተ ዕድል ሊኖር ይችላል። አሜሪካ ከዓለም ገበያ ከምትሸምተው የጨርቃ ጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ምርቶች ጣልያን፣ ቻይና፣ ቪየትናም እና ጀርመን እስከ 90 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ዶክተር ሙሴ ይናገራሉ።
ቻይና እና ቪየትናምን የመሳሰሉ ሀገራት የተጣለባቸውን ከፍተኛ ታሪፍ ተደራድረው ማስቀነስ ካልቻሉ የኢትዮጵያ “ታሪፍ ከተወዳዳሪዎቹ አንጻር ሲታይ 10% ብቻ ስለሆነ እዚያ ውስጥ ዕድል ሊኖረን ይችላል” የሚሉት ዶክተር ሙሴ “ግን ብዙ ነገሮች መስተካከል አለባቸው” የሚል አቋም አላቸው። “ንግዳችን ቀልጣፋ መሆን አለበት። የንግድ ወጪያችንን መቀነስ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።
ወደብ አልባ በሆነችው ኢትዮጵያ “ትልቁ ወጪ ከ30 እስከ 40% የሚደርሰው የትራንስፖርት ወጪ ነው” የሚሉት ዶክተር ሙሴ የንግድ ሎጂስቲክስ አገልግሎትን “ማፋጠን እና ቀልጣፋ ማድረግ፤ የምርቶችን ጥራት መጨመር” እንደሚያስፈልግ ይወተውታሉ። “ከሁሉም የማምረት አቅማችንን አዳብረን ከተገኘን በተለይ በጨርቃ ጨርቅ እና በቆዳ ንግዶች ላይ ጥቅም ለማግኘት” ዕድል ሊኖር እንደሚችል ተስፋ አላቸው።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ፋብሪካ የከፈተው ሬይሞንድስ የተባለ የሕንድ ኩባንያ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከሚልኩ አንዱ ነው። ኩባንያው በጎርጎሮሳዊው 2025 የመጀመሪያ ሦስት ወራት በአሜሪካ ገበያ ከሸጠው የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በሐዋሳ ያቋቋመው ሲልቨር ስፓርክ ፋብሪካ 30 በመቶ ድርሻ እንደነበረው ባለፈው ሣምንት የሬይሞንድስ ዋና የፋይናንስ ሥራ አስፋጻሚ አመት አግራዋል ኤንዲቲቪ (NDTV) ለተባለ የሕንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው የትራምፕ 10 በመቶ ታሪፍ “አነስተኛ” መሆኑን የገለጹት አመት አግራዋል ይህ የሐዋሳውን ፋብሪካ “የበለጠ ለማሳደግ እምቅ አቅም” እንደሚሆን ተስፋ አላቸው። ሕንድ የተጣለባትን ታሪፍ በድርድር ቅዝ ማድረግ ተስኗት ተጽዕኖው ከቀጠለ ግን ሬይሞንድስ የተወሰኑ የማምረቻ ማሽኖቹን ወደ ኢትዮጵያ ሊያዘዋውር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
ጎካልዳስ ኤክስፖርትስ የተባለ ሌላ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች አምራች ኩባንያ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ታሪፍ ምክንያት በኢትዮጵያ እና በኬንያ የሚገኙ ፋብሪካዎቹን ማጠናከር ላይ ሊያተኩር እንደሚችል አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከእንዲህ አይነት የኩባንያዎች ውሳኔ ለመጠቀም ግን በርካታ ጋሬጣዎች ያሉባት ሀገር ሆና ትታያለች። ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት የአፍሪካ ሀገሮች ያለ ቀረጥ ሸቀጦቻቸውን በአሜሪካ ገበያ እንዲሸጡ ከሚፈቅደው አጎዋ የገበያ ሥርዓት የተባረረችው በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰ ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ነበር። ባለፉት ወራት ያንዣበበው የሌላ ጦርነት ሥጋትም ይሁን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች ኢትዮጵያ ለምትሻው የቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ ሳቢ አይደሉም።
ኩባንያዎች ለገበያ ዕድል ብቻ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው እንደማይዘዋወሩ የሚናገሩት ዶክተር ሙሴ መፍትሔ ያልተበጀለት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መረጋጋት እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ፣ መሠረተ-ልማት እና ኩባንያዎቹ ትርፍ ወደ ሀገራቸው የሚወስዱበት ሥርዓትም በውሳኔዎቻቸው ላይ ሚና ይኖራቸዋል።
“ፖለቲካዊ መረጋጋት ካለን፤ ዘላቂ የሆነ ሰላም ካለን ኢንቨስተር የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ሠራተኛ ኃይል ያለበት ሀገር ነው። ትልቅ ፍላጎት ያለበት ሀገር ነው። ብዙ ነገር እናሟላለን” የሚሉት ዶክተር ሙሴ ኢትዮጵያ መፍትሔ ልታበጅላቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ግን አላጡትም። “ተስፋ አለኝ የህንዱ ብቻ ሳይሆን ከቻይናም ብዙ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ እንደሚሔዱ እንጠብቃለን። ግን ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙት የተረጋጋ የኢንቨስትመንት እና የፖሊሲ ከባቢ ያላቸው ሀገሮች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
አርታዒ ጸሀይ ጫኔ