1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በመራዊ ከተማ “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም” ዶክተር ለገሰ ቱሉ

ረቡዕ፣ የካቲት 6 2016

የኢትዮጵያ መንግሥት በመራዊ ከተማ ተፈጽሟል የተባለውን የ45 ሰላማዊ ሰዎች ግድያ አስተባበለ። በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ግጭት እንደነበር ያረጋገጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት በመራዊ ከተማ ተፈጽሟል የተባለውን የ45 ሰላማዊ ሰዎች ግድያ አስተባበለ። በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ግጭት እንደነበር ያረጋገጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥር 20 ቀን 2016 በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ከተደረገ በኋላ “በሲቪል ሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት” ምርመራ እያካሔደ መሆኑን ትላንት ማክሰኞ አስታውቋል።

መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመራዊ ከተማ “ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ‘ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል’ በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ መግደላቸውን” እንዳረጋገጠ ይፋ አድርጓል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን  የካቲት 5 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ “‘የፋኖ አባላት ናቸው’ በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል” ብሏል። 

የአውሮፓ ህብረት በመራዊ ከተማ የተፈጸመው ግድያ እንዲጣራ ጠየቀ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደነበር ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

ታጣቂዎቹ “በተለያዩ አቅጣጫዎች መከላከያ ሠራዊቱ የሰፈረበትን ካምፕ በአራት አቅጣጫ በማፈን መሣሪያ እና ሎጂስቲኩን ለመዝረፍ በመንቀሳቀሳቸው ራሱን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ ነው እርምጃ የወሰደው” ሲሉ ተናግረዋል።  

በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን በምትገኘው መራዊ ከተማ የተፈጸመው የሰላማዊ ሰዎች ግድያ ላይ “ገለልተኛ ምርመራ ተደርጎ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ” በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ጥሪ አቅርበዋል።ምስል Seyum Getu/DW

መከላከያ ሠራዊት ”ራሱን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ እርምጃ ሲወስድ እነዚህ ኃይሎች ተመልሰው ወደ ግለሰቦች ቤት ነው የገቡት” ያሉት ዶክተር ለገሰ “ወደ ግለሰቦች ቤት በሚገቡበት ጊዜ በሕጉ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት አሰሳ ሲያደርግ መልሰው ተኩስ ከፈቱበት” ሲሉ አብራርተዋል።

መከላከያ ሠራዊት “ራሱን ነው የተከላከለው” ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረግም” ሲሉ አስተባብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጡ የመብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በመንግሥት የፀጥታ ኃይላት እርምጃ ከተወሰደባቸው ሰዎች መካከል ከቤት እየተወሰዱ የተገደሉ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንን በተመለከተ የተጠየቁት ሚኒስትሩ "እንደዚያ አይነት እርምጃ ስለመወሰዱ ተረጋግጦ የመጣ መረጃ የለም" ብለዋል። አክለውም "ሲቪል ይቅርና ታጣቂ እንኳን ለማጥቃት ሄዶ እጅ እስከሰጠ ድረስ የሚገደልበት ሥርዓት የለም። ሊሆንም አይችልም" ብለዋል። "እንዲህ ሆኖ ከሆነም ራሱ መከላከያ ተቋሙ እርምጃ ይወስዳል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በቃል አቀባዩ በኩል ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል መራዊ ከተማ የተፈጸመው ግድያ በነጻና ገለልተኛ ቡድን ተጣርቶ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።ምስል Valerio Rosati/Zoonar/picture alliance

በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ በመራዊ ተፈጽሟል የተባለው ግድያ “እጅግ” እንደሚያሳስበው ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ “የሚረብሽ” ያለው በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ በበኩሉ “ሙሉ ምርመራ” እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ መንግሥት በበኩላቸው “ገለልተኛ ምርመራ” እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

 በመራዊው ግጭት ከ80 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ፤ ኢሰመጉ

ዶክተር ለገሰ ቱሉ ግን ጉዳዩ የሚመለከተው በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ እንደሆነ ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ምርመራ የሚያደርግ “ሌላ አካል” እንደማይኖር የገለጹት ዶክተር ለገሰ ጥሪውን ያቀረቡት የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ መንግሥት “ስለ ኢትዮጵያ ሁሌ እንዳሳሰባቸው ነው። ነገር ግን ይኸ ነው የሚባል የሚደረግ ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

“የራሳችን ተቋሞች አሉ። ተቋሞቻችን ለሕዝብ ተጠያቂ ናቸው” ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ “የትኛውም አካል ጥፋት ካጠፋ፤ የትኛውም አካል ጉዳት ካደረሰ ሕጉ እና አሠራሩ በሚፈቅደው መሠረት እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ተናግረዋል። 

በአማራ ክልል ግጭት የተቀሰቀሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት “ልዩ ኃይል” ተብለው ይጠሩ የነበሩ የክልሎች የጸጥታ አስከባሪዎች እንዲፈርሱ ከወሰነ በኋላ ነበር። በግጭቱ ምክንያት ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ጀምሮ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል። 

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW