1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ አራት ጄኔራልነትን ጨምሮ ለ66 ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር መኮንኖች ማዕረጎች ሰጠች

ቅዳሜ፣ መስከረም 10 2018

የኢትዮጵያ መንግሥት አራት ጄኔራልነትን ጨምሮ ለ66 ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር መኮንኖች ማዕረጎች ሰጠ። ሉቴናንት ጄኔራል አለምሸት ደግፌ፣ ሉቴናንት ጄኔራል ደስታ አብቼ፣ ሉቴናንት ጄኔራል ይመር መኮንን እና ሉቴናንት ጀኔራል ድሪባ መኮንን ሙሉ ጄኔራል ሆነዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት
የኢትዮጵያ መንግሥት አራት ጄኔራልነትን ጨምሮ ለ66 ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር መኮንኖች ማዕረጎች ሰጠምስል፦ Solomon Muchie/DW

ኢትዮጵያ መንግሥት አራት ጄኔራልነትን ጨምሮ ለ66 ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር መኮንኖች ማዕረጎች ሰጠ። ወታደራዊ መኮንኖቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅራቢነት በፕሬዝደንት ታዬ አጽቀሥላሴ የማዕረግ ዕድገት የተሰጣቸው ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2018 እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

በጽህፈት ቤቱ በኩል ይፋ በሆነው ዝርዝር መሠረት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኃላፊ የሆኑት ሉቴናንት ጄኔራል አለምሸት ደግፌ የሙሉ ጄኔራል ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።

የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሉቴናንት ጄኔራል ደስታ አብቼ፣ የመከላከያ ትምህርት እና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሉቴናንት ጄኔራል ይመር መኮንን፣ እንዲሁም የመከላከያ ኢንስፔክተር ጀኔራል ቢሮ ኃላፊ ሉቴናንት  ጀኔራል ድሪባ መኮንን በተመሣሣይ የጄኔራል ማዕረግ አግኝተዋል። 

ሌሎች ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ከሜጀር ጄኔራል ወደ ሉቴናንት ጄኔራል ከፍ ብለዋል። የሜካናይዝድ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለዉ አምዴ እና ሜጀር ጄኔራል ማዕረግ የነበራቸው የባህር ኃይል አዛዥ ሪል አድሚራል ክንዱ ገዙ ወደ ሉቴናንት ጄኔራል ማዕረግ አድገዋል። 

የብርጋዴር ጄኔራል ማዕረግ የነበራቸው አስራ ሰባት ወታደራዊ መኮንኖች ወደ ሜጀር ጄኔራል ከፍ ሲሉ፤ ሌሎች 43 ወታደራዊ መኮንኖች ከኮሎኔል ወደ ብርጋዴየር ጄኔራል ማዕረግ አድገዋል። 

ለመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ማዕረግ የተሰጠው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ውስጥ ባለፉት ቀናት የባለሥልጣናት ሹም ሽር ከተካሔደ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝን የብሔራዊ ባንክ ገዥ አድርገው ሾመዋል።ምስል፦ Eshete Bekele/DW

ትላንት አርብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝን የብሔራዊ ባንክ ገዥ አድርገው ሾመዋል። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያን ከሚያስፈጽሙ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት እዮብ ከመንግሥት ኃላፊነታቸው የተሰናበቱት ማሞ እስመለዓለም ምህረቱን ይተካሉ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩት እናትዓለም መለሰ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሆነው ዶክተር ለገሠ ቱሉን በመተካት መስከረም 9 ቀን 2018 ተሾመዋል። ለአራት ዓመታት ገደማ የመንግሥት ኮምዩንኬንሽ አገልግሎት ሚኒስትር የነበሩት ለገሠ ቱሉ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነዋል። 

 

አርታዒ ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW