የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገት ዕቅድና የባለሙያ አስተያየት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2017
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ዘንድሮ በ8.4 በመቶ ያድጋል በማለት የሐገሪቱ መንግሥት የነደፈዉ ዕቅድ ገቢር እንደሚሆን ጠቋሚ ምልክቶች መኖራቸዉን አስታወቀ።አንድ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ግን የመንግሥትን ዕቅድና ግምት አልተቀበለቱም።ባለሙያዉ እንደሚሉት ሠላም ሳይሰፍን የምጣኔ ሐብት ዕድገት አይኖርም።"የኢኮኖሚ ዕድገት ሁል ጊዜ ጥሩ እና የተስማማ ፖለቲካ ይፈልጋል" ያሉት ባለሙያው የምጣኔ ሐብት ዕድገት አልሚዎችን የሚስብ ኹኔታ ይፈልጋል በማለትም ይከራከራሉ
መንግሥት በዓመቱ የ 8.4 የኢኮኖሚ ዕድገት እቅድ ይዟል
የኢትዮጵያ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበትት ለመንግሥት የካቢኔ አባላት የሀገሪቱን የዘጠኝ ወራት የምጣኔ ሐብት የሥራ አፈፃፀም ሲያቀርቡ መንግሥት የያዘውን የ8.4 በመቶ የኡኮኖሚ ዕድገት ውጥን ሊያሳካ የሚችልበት ያሏቸው አመላካቾችን ዘርዝረዋል። ከሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት አንፃር "ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት ማደጋቸውን፣ የሀገር ውስጥ ገቢ መጨመሩን፣ የ3.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ሽግሽግ መደረጉ ለዕዳ መከፈል የነበረበት ሀብት ለልማት ሥራዎች ውሎ እገዛ ማድረጉን፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማደጉን" በዐወንታ ጠቅሰዋል።
ይህ የሚሳካ አይደለም - የምጣኔ ሐብት ባለሙያ
የመንግሥትን እቅድ በተመለከተበአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሐብት መምህር ለሆኑት ዶክተር አጥላው ዓለሙ ጥያቄ አንስተናል። ባለሙያው ለውጥ እንዲመጣ የዕድገት ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች - የካፒታል፣ የሰው ሀብት እና የቴክኖሎጂ እድገት ጨምሯል ወይ? ሲሉ መልሰው ይጠይቃሉ። የፖለቲካ፣ የባህል፣ የሰላም፣ የሕግ፣ ደንብ እና የአሠራር ኹኔታዎች ለሥራ አመቺ ኹኔታ ሲፈጥሩ የኢኮኖሚ ዕድገት ይኖራል ያሉት ባለሙያው ይህ ካልሆነ ግን "በምኞት ዕድገት የለም" ሲሉ መልሰዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሩያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ተጨባጭ ኹኔታ "ጤነኛ" ብለውት ነበር።የምጣኔ ሐብት ባለሙያ እና መምህሩ ዶክተር አጥላው ዓለሙ ግን የኢኮኖሚ ዕድገት "ጥሩ እና የተስማማ ፖለቲካ ይፈልጋል" ባይ ናቸው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ ባለፉት ስምንት ወራት 2.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ተናግረዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያ እና መምህሩ ዶክተር አጥላው ዓለሙ እንደሚሉት ግን ዕድገትን በተመለከተ የሚቀርቡ የተለጠጡ ቁጥሮች የተለመዱ ናቸው።የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጦርነት፣ በግጭት፣ ለከተማ ልማት በሚል በቤቶች ማፍረስ፣ መፈናቀል፣ የፀጥታ መናጋት፣ እገታን በመሳሰሉ ችግሮች በተከሰተ የሥራ መቀዛቀዝ እየተፈተነ መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር