1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓትና ከኤርትራ ሲወዛገብ ለእውነተኛ ንግግር ከትግራይ ጥሪ ቀረበ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 1 2018

የትግራይ ሲቪል ድርጅቶች “የፖለቲካ ችግሮች ወደ ከፋ ሁኔታ ሳይሸጋገሩ በውይይት እንዲፈቱ” ጠይቀዋል። ድርጅቶቹ “እውነተኛ ንግግር” እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓትና ከኤርትራ በኃይል ሲወዛገብ ነው።የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ ሊቀ-መንበር የሚመለከታቸው ኃይሎች “ፍላጎታቸውን በኃይል ሳይሆን በንግግር” እንዲያስፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል

በትግራይ ጦርነት ወቅት የተገደሉ ሰዎች መርዶ የተነገራቸው ቤተሰቦች በለቅሶ ላይ ይታያሉ
ከ2013 እስከ 2015 በተካሔደው ጦርነት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ይታመናል። ምስል፦ Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት እና ከኤርትራ ሲወዛገብ እውነተኛ ንግግር እንዲደረግ ከትግራይ ጥሪ ቀረበ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት የሚያረግብ እውነተኛ እና ሁሉ አካታች ውይይት እንዲጀመር ጥሪ አቀረቡ። ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በበኩሉ በአፍሪካ ቀንድ እየታየ ያለው የተካረረ ፖለቲካዊ ውጥረት ወደከፋ ሁኔታ እንዳያመራ ዓለማቀፍ ማሕበረሰብ ሚናው ይወጣ ብሏል።

ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት መካከል እንዲሁም በኤርትራ እና ኢትዮጵያ መንግስት መካከል እየታየ ያለው ውዝግብ ባየለበት በዚህ ወቅት ትላንት የሰላምና ውይይት መልእክት በማለት መግለጫ ያወጡት በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ስምንት ሲቪል ማሕበራት እየታዩ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ወደከፋ ሁኔታ ሳይሻገሩ በውይይት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

በተለይም በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ክፍፍል አሳሳቢ ሆኖ እንዳለ ሲገልፁ የቆዩት እነዚህ ሲቪል ተቋማት፥ በሰላም እና አንድነት የተባሉ መድረኮች እየተካሄዱ መሆኑ ብንታዘብም ሁሉ አካታች አይደሉም ብለዋል።

የተለየ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው የፀጥታ እና ፖለቲካ ሐይሎች፣ ሲቪል ማሕበራት እንዲሁም የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍል የሚወክሉ አካላት ያሳተፈ እውነተኛ ንግግር እንዲደረግ ጥሪ እናቀርባለን ሲሉ እነዚህ ስምንት ሲቪል ተቋማት በጋራ መግለጫቸው አስታውቀዋል።

ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች፣ በሴቶች ጉዳይ የሚሰሩ ጎርዞ እና ይኾኖ የተባሉ ተቋማት ጨምሮ ሌሎች በዚሁ መግለጫቸው ሁሉም አካላት ለሰላም እና ውይይት ዝግጁነታቸው ያሳዩ ብለዋል።

የሳልሳይ ወያነ ሊቀ-መንበር አሉላ ኃይሉ “የትግራይ ሕዝብ የመዋጊያ ቦታ እና አውድ እንዳይሆን” ፓርቲያቸው ሥጋት እንዳለው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ Million Haileselassie Brhane/DW

የዳግም ጦርነት ስጋት

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ ያወጣው በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በበኩሉ ትግራይን ከዛም አልፎ አፍሪካ ቀንድን መልሶ ወደ ግጭት ሊያስገባ የሚችል ሁኔታ መኖሩ በመግለፅ ለዚህ ትኩረት እንዲሰጥ አመልክቷል።

አቶ አሉላ ሃይሉ የትግራይ ህዝብ ካለፈው ጦርነት ጠባሳ አላገገመም ያሉ ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ ከጦርነቱ በኃላ ጭምር ወደ ቀዬው ሳይመለስ ባለበት ዳግም ግጭት እንዳይከሰት የበለጠ ጥንቃቄ ያሻል ብለዋል።

የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ሚና

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አሉላ ሃይሉ በህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት መካከል የቆየ ልዩነት እንዲሁም መነሻው የተለያዩ ፍላጎቶች ያደረገ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስት ፍጥጫ ወደለየለት ጦርነት የሚገባ ከሆነ የትግራይን ህዝብ ለከፋ ሁኔታ የሚዳርግ በመሆኑ አስቀድሞ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ ያነሳሉ። 

ከዚህ በተጨማሪ ዓለምቀፉ ማሕበረሰብም የሚጠበቅበት ሐላፊነት ይወጣ ሲሉም አቶ አሉላ ሃይሉ ጨምረው ይገልፃሉ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW